1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማብቂያ የሌለዉ ጦርነት

ሰኞ፣ ነሐሴ 6 2011

በ1986 ግን 20 ዓመት ያገለገሉትን የያኔዋን የደቡብ የመን ሶሻሊስታዊ መንግስት ከድተዉ ወደ ሰሜን ኮበለሉ።ጥቂት ቆይተዉ መከላከያ ሚንስትር ሆኑ።ወዲያዉ የተወልዱ፣ያደጉ፣የተማሩ፣ ለጄኔራልነት የበቁበትን ደቡብ የመንን ወግተዉ፣ከአለቃቸዉ ከዓሊ አብደላ ሳላሕ ጋር ሁለቱን የመኖች አዋሓዱ።

https://p.dw.com/p/3Nmx2
Jemen Aden Soldaten des Southern Transitional Council (STC)
ምስል picture-alliance/Photoshot/M. Abdo

የመን ማብቂያ የሌለዉ ጦርነት

የመንን ከ2015 ጀምሮ የሚያወድመዉ ጦርነት፣ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚስማሙበት፣ የኢራንና የሳዑዲ አረቢያ የተልዕኮ ጦርነት ነዉ።የየመን «ሕጋዊ» የሚባሉት ፕሬዝደንት ሪያድ ሆነዉ፣ በሪያዶች ትዕዛዝ «በተልዕኮ» ያዋጋሉ።አብድረቦ መንሱር ሐዲ።ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እነ ግብፅን አስከትለዉ የፕሬዝደንት ሐዲ ጠላቶችን ሁቲዎችን ይወጋሉ።የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የሐዲ መንግሥትን የሚቃወሙትን የደቡብ የመን ተገንጣዮችን ትረዳለች።ሳዑዲ አረቢያዎች ኢስላሕ የተባለዉን እስልምና አክራሪ ቡድንን ይደግፋሉ።የመን ታሪካዊት ምድር።የግራ አጋቢ ትብብር፣የግራ አጋቢ ጦርነት፣ምስቅልቅል ሐገር።የድፍን ዓለም ሙስሊም ለኢድ አል-አድሐ በዓል በግ ሊሰዋ ሲዘጋጅ አረባዊቱ፣ሙስሊሚቱ፣ ታሪካዊቱ አደን አርባ ዜጎችዋን ጭዳ አረገች።ቅዳሜ።ግራ አጋቢዉ ምስቅልቅል ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉዩ።

  ሠበብ ምክንያቱ ዕጣ-ፈንታ፤የአርባ ቀን ዕድል፣ ጅልነት፣ ስልት አለማወቅ ብዙ ሊባል ይችላል ሰዉዬዉ ግን ጥሩ ጅምርን እንጂ ፍፃሜን፣ ሙከራ-መከራን እንጂ ስኬት-ድስታን አያዉቁም።አብድረቦ መንሱር ሐዲ።በ2015 ዳሕላን ግዛት ላይ ስማቸዉ ከገነነዉ የሚሊሺያ ጦር አዛዥ ከአይደሩስ ቃሲም አብዱል አዚዝ አል-ዙቤይዲ ጋር ግንባር ሲፈጥሩ ሁቲዎችን ከደቡብ የመን ለማባረር «ዘይዱ» ተብሎላቸዉ ነበር።

Jemen Krieg STC-Kämpfer (Southern Transitional Council) in Aden
ምስል Getty Images/AFP/N. Hasan

ስምምነቱን በጠንካራ ዉል ለማሰርም ወጣቱን የሚሊሻ ጦር መሪ የእዉቋ ጥንታዊ ዉብ የወደብ ከተማ የአደን አገረ-ገዢ አድርገዉ ሾሟቸቸዉ።ሹመቱ፣ የሽማግሌዉ ፕሬዝደንት ጀምበር እያዘቀዘቀች፣የወጣቱ ሚሊሺያ አዛዥ እየበረቀች የመምጣቱ ምልክት መሆኑን ምናልባት ከሪያዶች ይልቅ አቡዳቢዎች አስተንትነዉ ይሆን ይሆናል።

በብዙዎች ዘንድ ግን ከሪያድ በተልዕኮ የሚሾሙ-የሚሽሩት፤በተልዕኮ የሚያዋጉት ሐዲ፣አደንን ለሁቲዎች አሳልፎ ለማይሰጥ ሁነኛ ሰዉ የማስረከባቸዉ ጥሩ ርምጃ ተብሎ ተወድሶ ነበር።ሹመቱ ከማንም ለአዲሱ ተሿሚ በርግጥ እጅግ ጠቃሚ ነበር።አል ዙቤይዲ የአደንን ያዛዥ ናዛዥነትን ስልጣን ከተረኩ በኋላ ለሁቲዎች ቀንደኛ ጠላትነታቸዉን እያሳዩ፣ ሐዲን አልፈዉ የሪያዶች ልብ እያማለሉ፣ የአቡዳቢዎችን ቀልብ ይማርኩ ገቡ።

የጤና እጦት እና እድሜ ባደከመዉ አቅም፣ በስደት ስልጣን፣ የሪያዶችን ትዕዛዝ፣ የሚንስትሮቻቸዉን ጉትጎታ፣ የታማኝ ተዋጊዎቻቸዉን ዉትወታ፣የጠላቶቻቸዉን ጥቃት እኩል ለመመከት የሚጠራወዙት ሐዲ በ2017 ወደ አደን ሲያማትሩ፣ የአደኑ ገዢ ከሪያዶች ሸሸት፣ከአቡዳቢዎችን ልጥፍ ብለዉ አገኟቸዉ።

ሚያዚያ 2017።ፕሬዝደንቱ አል ዙቤይዲን ከአደን አገረ-ገዢነት ሻሩ።ሐዲ መጀመር እንጂ መፈፀም አይሆንላቸዉም።በ2015 ከአል ዙቤይዲ ጋር የጀመሩትን የፖለቲካ ጨዋታ በሁለተኛ ዓመቱ ሲያቋርጡ አልዙቤይዲ ባዲስ ስልት ቀጠሉበት።ግንቦት መጀመሪያ።አል ዙቤይዲ የደቡብ (የመን) የሽግግር ምክር ቤት ያሉትን ድርጅት ወይም የፖለቲካ ማሕበር መሠረቱ።

Erste Parlamentssitzung in Jemen seit vier Jahren
ምስል picture-alliance/dpa

በሁለተኛ ዓመቱ በቀደም ቅዳሜ  አንድ የአልዙቤይዱ ጦር አዋጊ «ደሕናሰንብት» አለ።«ለወንድማማች ፓርቲ ደሕና ሰንብት እንልላለን።አሁን ፕሬዝዳንታዊዉ ቤተ-መንግስት (ማሻክ) አጠገብ ነን።(ደጋፊዎቻችሁ) መዉጪያ መንገድ የላቸዉም።ሐገራችንን እየተቆጣጠርን ነዉ።ከእንግዲሕ የወንድማማቾች ፓርቲ ከደቡብ ደሕና ሰንብት።ድሉ (የኛነዉ)።»

ሌላዉ ቀጠለ።አል ዙቤይዲን ፕሬዝደንት እያለ።«ከደቡብ ለተሰዉት ወገኖቻችን፣ ከዚሕ ቀደም በተደረገዉም፣ በዛሬዉም ዉጊያ መስዋዕት ለሆኑት ሁሉ ፈጣሪ ነብሳቸዉን እንዲምራት እንፀልያለን።የቆሰሉት ፈጥነዉ እንዲፈወሱም እንፀልያለን።ያሁኑ ድል አሸባሪዉን የኢስላሕ ፓርቲን ካሸነፍን ወዲሕ የተቀዳጀነዉ ትልቅ ድል ነዉ።ድሉ የደቡቦች ድል ነዉ።ይሕ ድል የደቡብ የመን ፕሬዝደንት የአይደሩስ አል ዙቤይዲ ድልም ነዉ»

ከአራት ዓመት በፊት የአንዲት ትንሽ ግዛት ሚሊሺያ አዛዥ የነበሩት አል ዙቤይዲ አሁን የአብድ ረቦ መንሱር ሐዲ ተፎካካሪ ምናልባትም የበላይ መስለዋል።በደጋፊዎቻቸዉ ዘንድ ፕሬዝደንት ተባሉ።

አል ዜቤይዲ የሚመሩት የደቡብ የሽግግር ምክር ቤት አላማ የቀድሞዋን የየመን ሶሻሊስት አረባዊ ሪፐብሊክን ከሰነዓ ማዕከላዊ መንግስት አገዛዝ ነፃ ማዉጣት ነዉ።ከተባበሩት የአረብ ኤሚሬቶች ከስልጠና እስከ ዘመናይ ጦር መሳሪያ፣ ከገንዘብ እስከ ስልላ ሙሉ ድጋፍ ይደረግለታል።ኃይሉን እስከሚያጠናክር ድረስ ባንድ በኩል በሳዑዲ አረቢያ ከሚደገፈዉ ኢስላሕ ጋር ተባብሮ ሁቲዎችን እየተዋጋ በሌላ በኩል የሐዲ መንግስት ደጋፊዎችን ይዞታን ለመቆጣጠር ያደባ ነበር።ቅዳሜ ሙሉ በሙሉ ተሳካለት።

ቡድኑ አደንን ጨምሮ በርካታ የደቡብ የመን ሥልታዊ ከተሞችን ይቆጣጠራል።በአቡዳቢ የሚደገፈዉ ቡድን በሳዑዲ አረቢያ ከሚረዳዉ ኢስላሕ ፓርቲ፣ በተለይም ሪያድ ከሚገኙት ከሐዲ መንግሥት ታማኞች ጋር ግልፅ ዉጊያ መግጠሙ፣ ጥብቅ ወዳጆች በሚመስሉት በሪያድና በአቡዳቢ ነገስታት መካከል ያለዉን የጥቅም ሽሚያ በግልፅ የሚያስመሰክር ነዉ።

Jemen Konflikt l Mädchen besucht Friedhof in der Hauptstadt Sana'a
ምስል Getty Images/AFP/M Huwais

የኢትዮጵያ የዉጪ ግንኙነት የስትራቴጂ ጥናት ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ አበበ አይነቴ እንደሚሉት ሰሞኑን አደን ላይ የታየዉ ግራ አጋቢ የኃይል አሰላለፍ የጦርነቱ ዘዋሪዎች የሚከተሉት ፖሊሲን ወይም መርሐ ተደጋጋፊ ሳይሆን ተፎካካሪ መሆኑን አመልካች ነዉ።

 አብድቦ መንሱር ሐዲ ሐገራቸዉንም ሥልጣናቸዉንም የተፎካካሪዉ መርሕ ቤዛ ካደረጉ አምስተኛ ዓመታቸዉ።ለሁሉም ግን እንግዳ አይደሉም።በ1966 ብሪታንያ ከመሰረተችዉ የደቡብ አረቢያ ፌደሬሽን የጦር ትምሕርት ቤት ሲመረቁ ጎበዝ መኮንን፣ ተስፋ ሰጪ አዋጊ ተብለዉ ነበር።ብሪታንያ ከመሰረችዉ የጦር ትምሕርት ቤት በመኮንንነት ተመርቀዉ ለተጨማሪ ኮርስ ወደ ብሪታንያ ሊላኩ ሲሉ እንግሊዝኛ አይችልም ተብለዉ ቀሩ።

የካፒታሊስቷ ብሪታንያ የጦር ትምሕርት ቤት ምሩቅ፣ ብሪታንያ መማር አይችልም በተባሉ በ3ኛዉ ዓመት ሶቬት ሕብረት ሔዱ።እንግሊዝኛ አይችልም የተባለዉ መኮንን በሩሲያኛ አራት ዓመት የታንክ አዋጊነት ተማረ።

ባለፈዉ ቅዳሜ የደቡብ የመን ተገንጣዮች የተቆጣጠሩትን የአደንን ቤተ-መንግሥት እንደ ጄኔራል ተመላልሰዉበታል።በ1986 ግን 20 ዓመት ያገለገሉትን የያኔዋን የደቡብ የመን ሶሻሊስታዊ መንግስት ከድተዉ ወደ ሰሜን ኮበለሉ።ጥቂት ቆይተዉ መከላከያ ሚንስትር ሆኑ።ወዲያዉ የተወልዱ፣ያደጉ፣የተማሩ፣ ለጄኔራልነት የበቁበትን ደቡብ የመንን ወግተዉ፣ከአለቃቸዉ ከዓሊ አብደላ ሳላሕ ጋር ሁለቱን የመኖች አዋሓዱ።

ለዉለታቸዉ ሽልማት ደቡቦችንም ለማማለል ሲባል በ1994 ምክትል ፕሬዝደንት ሆኑ።በ2012 ፕሬዝደንት ዓሊ አብደላ ሳላሕ በሕዝባዊ አመፅ ከስልጣን ሲወገዱ መጀመሪያ ተጠባባቂ፣ ቀጥሎ ሙሉ ፕሬዝደንት ሆኑ።የሰነዓን ቤተ-መንግስት ቅንጦት በቅጡ ሳያጣጥሙ ግን በሁቲ አማፂያን ግፊት ስልጣን መልቀቃቸዉን አወጁ።ጥር 2015።ከሰነዓ ሸሽተዉ ድሮ እንደ ጄኔራል በሚያዉቁት የአደን ቤተ-መንግስት ላጭር ጊዜ ተቀምጠዉ ነበር።ወዲያዉ ግን ወደ ሪያድ ሸሹ።

Jemen Gaszylinder
ምስል DW/J. Abdullah

ፕሬዝደንት አብድረቦ መንሱር ሐዲ።ሪያድ ሆነዉ በሳዑዲ አረቢያዎች ትዕዛዝ፣ በሳዑዲ አረቢያዎች ገንዘብ፣ በሳዑዲረቢያ፤ በአረብ ኤሚሬቶች፣ በግብፅ፤በሱዳን፣በሌሎችም ሐገራት ጦርና ጦር መሳሪያ በኢራን ይደገፋሉ በሚባሉት ሁቲዎች ላይ የከፈቱት ጦርነት ሺዎችን አርግፏል።መቶ ሺዎችን አቁስሏል።ሚሊዮኖችን በረሐብና በሽታ ያሰቃያል።ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ።

ሐዲ ከይስሙላ ባለፍ ጦርነቱን ለማስቆምም ሆነ ለመቀጠል አቅመ ቢስ ናቸዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጀመረዉ ድርድርም በነበረበት እየረገጠ ነዉ።ኃያሉ ዓለምም የመንን፣ የመኖችን ለሚያጠፉት ለሪያድ-አቡዳቢ ገዢዎች ርግፍ አድርጎ የተወዉ መስሏል።ሪያድ አቡዳቢዎችም አደን ላይ እንደሆነዉ ወጥ ራዕይ ያላቸዉ አይመስልም።የፖለቲካ ተንታኝ አበበ አይነቴ ግን ጦርነቱ ግራ እንዳጋባ የቀጠለዉ በጥቅል ዓለም የመደጋገፍ መርሕ በመጥፋቱ ምክንያት ነዉ ባይ ናቸዉ።

የየመኑ ጦርነት መጀመሪያ የርበርስ፣ ኋላ የኢራንና የሳዑዲ አረቢያ የተልዕኮ ጦርነት፣ አሁን ደግሞ የሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የፖሊሲ መላተም እየተባለ አብዛኛዉን አረብ፣ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያንያንም በቀጥታም በተዘዋዋሪም አነካክቷል።የመንን በመልከዓ ምድር አቀማመጥና በምጣኔ ሐብት የሚገናኙ የአፍሪቃ ቀንድ ሐገራትም ከቱጃሮቹ የአረብ ሐገራት ጋር በማበርና ባለማበር መሐል ግራ ቀኝ እየተላጉ ነዉ።

Jemen Konflikt l Jeminitische Flüchtlinge in der Provinz Hadscha
ምስል Getty Images/AFP/E. Ahmed

የፖለቲካ ተንታኝ አበበ አይነቴ እንደሚሉት ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር በየዉስጥ ችግራቸዉ የሚዳግሩት የአፍሪቃ ቀንድ ሐገራትን ለተጨማሪ ቀዉስ ማጋለጡ አይቀርም።

ሰዉ ታሪክ ካለዉ የመንን በጣሙትን አደንን ሳይጠቅስ የሚተርከዉ የለዉም።የመን እየጠፋች ነዉ።ጥፋትዋ ለመጪዉ ትዉልድ ተጨማሪ ታሪክ ይሆን ይሆናል፣ የአጥፊዎችዋ መጥፊያ አይሆንም ብሎ መገመትም የዋሕነት እንዳይሆን ከሁለቴ በላይ ማሰብን ይጠይቃል። 

 

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ