1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመካከለኛው ምሥራቅ የሰላም ይዞታና የሃማስ አቋም፧

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 14 2000

የፍልስጤሙ ሃማስ ድርጅት መሪ፧ ኻሌድ ማሻል፧ ከቀድሞው የዩናይትድ እስቴትስ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር ጋር በመጠኑ ከተወያዩ በኋላ፧ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፧ በ 1959 ዓ ም ግንቦት መጨረሻ እስከ ሰኔ ወር መጀመሪያ ገደማ (ማለትም እ ጎ አ ከሰኔ 5 እስከ 10, 1967 ዓ ም)

https://p.dw.com/p/E86u
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር፧ በቀድሞው የፍልስጤማውያን መሪ ያስር ዐረፋት መካነ መቃብር ላይ፧ ጉንጉን አበባ ሲያስቀምጡ፧
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር፧ በቀድሞው የፍልስጤማውያን መሪ ያስር ዐረፋት መካነ መቃብር ላይ፧ ጉንጉን አበባ ሲያስቀምጡ፧ምስል AP
በእሥራኤልና በዐረቦች መካከል ጦርነት ከመካሄዱ በፊት በነበረው ድንበር የሚመሠረት የፍልስጤም መንግሥት፧ በድርጅታቸው በኩል ተቀባይነት እንደሚያገኝ፧ ሆኖም የእሥራኤልን ኅልውና እንደማይቀበል አስታውቋል። የዶቸ ቨለ ባልደረባ ፔተር ፊሊፕ በሐተታው ላይ እንደሚለው፧ እንዲህ ዓይነቱ አቋም፧ የሰላም ተስፋን የሚያጨልም ቢሆንም፧ በግልጽ በመነገሩ ጥሩ ነው። የፔተር ፊሊፕን ሐተታ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው ያቀርበዋል።
ማንኛውም ሰላም ፈላጊ፧ ከጠላቶቹ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ሆኖ መገኘት ይኖርበታል። ይህን አመለካከት፧ የአሁኑ የእሥራኤል ፕሬዚዳንት ሺሞን ፔሬስና ተባባሪዎቻቸው፧ በድብቅ ከፍልስጤም ነጻ አውጭ ድርጅት ያስር ዐረፋት ጋር ግንኙነት በመፍጠር የተደራደሩበትና የሰላም ውል እስከመፈራረም የደረሱበት ሁኔታ የቅርብ ጊዜ ታሪክ መሆኑ የሚታበል አይደለም። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር፧ እሥራኤል እንደያኔው ሁሉ አሁንም፧ አክራሪ እስላማዊ ድርጅት መሆኑ ከሚነገርለት፧ ከሃማስ ጋር ተመሳሳይ እርምጃ እንድትወስድ የሚጠይቁ ከሆነ ከዐለት ጋር መጋጨት ነው የሚሆንባቸው። ሀማስ፧ አሁንም፧ አንዳች የለውጥ ምልክት ሳያሳይ፧ እሥራኤል እንድትጠፋ የሚያሳስብም ሆነ የሚጠይቅ በመሆኑ፧ ለሰላም ድርድር ፍጹም ዝግጁ አይደለም። ካርተር፧ በትናንቱ ዕለት፧ ደማስቆ፧ ሶሪያ ውስጥ፧ ከሃማስ መሪ ኻሌድ ማሻል ጋር ከተነጋገሩ በኋላ፧ እኒሁ የፍልስጤማውያን ድርጅት መሪ፧ ከእሥራኤል ጋር የሰላም ድርድር ለማካሄድ ዝግጁ ናቸው፧ ይህን ሲያደርጉም፧ የፍልስጤማውያን ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ ከእሥራኤል ጋር የሚያደርጉትን ድርድር ለማጨናገፍ አለመሆኑን ገልጸው ነበር። አነጋጋሪ ጉዳይ ነው። በሦስት ሳምንታት ውስጥ፧ ማሻል፧ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የደገፈውን ሁለት ሉዓላውያን መንግሥታት የሚሰኘውን ማለት ከእሥራኤል ጎን፧ ነጻ የፍልስጤም መንግሥት የሚመሠረትበትን አቅድ ተቀብለውታል።የእሥረኤል አመራር ግን፧ ይህ ቁም ነገር አዘል ጉዳይ አይደለም በማለት ችላ ከማለቱም፧ ካርተርን ተቀብሎ አላነጋገረም። ካርተር፧ ከሃማስ ጋር ተገናኝተው በመነጋገራቸውና የደረሱበትን ድምዳሜ በማሰማታቸው እሥራኤል አልተደሰችበትም። ካርተር፧ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ብቅ ከማለታቸው በፊት ጀምሮ የሃማስ አቋም የታወቀ በመሆኑ፧ በእሥራኤል አመለካከት፧ የካርተር ጥረት፧ አጉል ድካም ነው። ኻሌድ ማሻል፧ እሥራኤል፧ ከ 1959 ዓ ም በፊት ወደነበረው ይዞታዋ በመመለስ፧ ከዮርዳኖስ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻ ወዲህ ያለውን ግዛት ለቅቃ ከወጣች፧ ፍልስጤማውያን ስደተኞች እንዲመለሱ ከፈቀደች፧ ድርጅታቸው፧ ለአሥር ዓመት የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚያደርግ ነው የገለጡት፧ እሥራኤልን በመንግሥትነት ማወቅ ግን አይታሰብም ነው ያሉት። ፔተር ፊሊፕ፧ እንዲህ ዓይነቱ ግልጽ አቋም፧ ተስፋን ቢያጨፈግግም፧ ጥሩ ነው፧ ባይ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ፧ የሚያበሳጨው ይላል ፔተር ፊሊፕ አሁንም፧ ሃማስ፧ ገሐዳዊውን ይዞታ መገንዘብ ያልቻለ በመሆኑ ነው። ብዙ ፈተና ያዩ የድርጅቱ አመራር አባላት እንኳ፧ ሮኬት መተኮሱ፧ አሸባሪ ተግባር መቃጣቱ፧ ከእሥራኤል ይልቅ ይበልጥ የሚጎዳው ፍልስጤማውያኑን መሆኑን አሳምረው ያውቁታል። እሥራኤል፧ አፀፋዊ እርምጃ ስትወስድ ቅጣቷ ያያለ ነውና! በሃማስ ቁጥጥር ሥር ያለው የጋዛ ወሽመጣዊ ግዛት፧ ይበልጥ ወደ መገለል እየተገፋ ከመሄዱም፧ ከባሰ ድህነት ላይ ነው የወደቀው። የውጭው ዓለምም፧ ሃማስ፧ እሥራኤልን ማጥፋት አለብኝ የሚለውን ርእዮት እስካልሰረዘ ድረስ፧ በዚያ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን እርዳታ እንዲያገኙ ለማድረግ ያን ያህል ዝግጁ አይደለም።
የቀድሞው የፍልስጤማውያን መሪ ያስር ዐረፋት፧ ይህን ሁሉ በማሰላሰል ነበረ የሰላም ውል ያአስገኘውን የኦስሎውን ድርድር የመረጡት። ለመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም፧ የኦስሎው ስምምነት አንድ እመርታ ነበረ። ይሁንና በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ገና አልሰፈነም። ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደ, ቡሽ፧ በዚህ ዓመት ውስጥ ሰላም ይገኛል ብለው ተስፋ ቢያሳድሩም፧ መሪሩ ሐቅ እንደማይሳካ ነው የሚያስገነዝበው። ለዚህ ኀላፊዎቹ ደግሞ፧ ራሷ እሥራኤልና የሃማስ ደጋፊዎች፧ ማለት ሁለቱም ወገኖች ናቸው።ይሁንና፧ ሰላም ለማምጣት ከጠላት ጋር መነጋገር የግድ እንደሚል ሃማሶች ማወቅ ይኖርባቸዋል።፧ የምንጊዜም አቋማቸው፧ አይሞከርም! ከሆነ ደግሞ መዘዙን መቻል አማራጭ የሌለው እውነታ ነው።