1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጨረሻዎቹን የኢትዮጵያ አይሁዶች የመወሰድ ውሳኔ

Eshete Bekeleሰኞ፣ ኅዳር 6 2008

እስራኤል በኢትዮጵያ የሚገኙ 9,000 አይሁዶች ለመውሰድ ውሳኔ አሳለፈች። በጎንደር እና አዲስ አበባ የሚገኙት የኢትዮጵያ አይሁዳውያን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ወደ እስራኤል እንደሚጓዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ አስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/1H6mZ
Äthiopien Jüdische Gemeinde Addis Abeba "Kechene"
ምስል Teferawork Esubalew

[No title]

እስራኤል የመጨረሻ ያለቻቸውን 9,000 የኢትዮጵያ አይሁዶች ወደ አገሯ እንዲገቡ የሚፈቅድ ውሳኔ አስተላልፋለች። የጠቅላይ ሚኒትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ «ዛሬ በአዲስ አበባና በጎንደር የሚገኙ ከእስራኤል ጋር ዝምድና ያላቸው የመጨረሻዎቹን ማህበረሰብ ወደ ሀገራችን ለማምጣት ጠቃሚ ውሳኔ አሳልፈናል። ሲሉ ተናግረዋል። ለሁለት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ አይሁዶችን ጉዞ በሀገሪቱ ፓርላማ ቀርቦ ያለምንም ተቃውሞ ጸድቋል። ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ውሳኔው ቤተሰብን ማገናኘት ውሳኔው ከጸደቀባቸው ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ ተናግሯል።

netanjahu israel ministerpräsident regierung
ምስል picture-alliance/dpa

በእስራኤል «የተመላሾች ህግ» መሰረት የአይሁድ ዝርያ ያላቸው ሰዎች አስፈላጊውን ቅድመ-ሁኔታ ካሟሉ በኋላ ዜግነትና የመኖሪያ ፈቃድ ሊያገኙ ይችላሉ። የመጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያ ቤተ-እስራኤላውያን በጎርጎሮሳዊው 1980ዎቹና 1990ዎቹ ነበር የተጓዙት። ጉዞው ኢትዮጵያ በጦርነት በምትታመስበት የመንግስቱ ኃይለማርያም መንግስም ሊወድቅ በሚንገዳገድበት ወቅት ከሱዳን ነበር የተጀመረው። ማጓጓዙን የእስራኤል ጦር፤ የአሜሪካ ማዕከላዊ የስለላ ድርጅትና የሱዳን የደህንነት ተቋም በጋራ ከውነውታል። የኋላ ኋላ ግን እስራኤል ዜጎቼ ያለቻቸውን ከአዲስ አበባ ለማጓዝ ፈቃድ አግኝታ አድርጋዋለች።

በእስራኤል 135,000የኢትዮጵያ አይሁዶችና ልጆቻቸው ይኖራሉ። ከኢትዮጵያ የተጓዙቱም ይሁኑ በእስራኤል የተወለዱት ወጣቶች በአዲሷ ሀገራቸው የመድሎና የዘረኝነት ሰለባ ሆነናል ሲሉ ያማርራሉ። ቤተ-እስራኤላውያኑ በቴል-አቪቭ አደባባዮች ተቃውሞ ወጥተው ከፖሊስ ጋር እስከመጋጨትም ደርሰዋል።ደማስ ፈቃደ የተባለው ወታደር ከነደንብ ልብሱ በእስራኤል ፖሊስ ድብደባ ከተፈጸመበት በኋላ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ የወጣቶችን ቁጣ ቀስቅሶም ነበር።

Jerusalem: Demonstration äthiopischer Juden
ምስል Reuters

ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን የእስራኤል መንግስት «አማርኛ የሚናገሩ 180 የኢትዮጵያ አይሁድ ፖሊሶችን በመቅጠር፤ በወር አንድ ጊዜ በፖሊስና በማህበረሰቡ መካከል ውይይት በማድረግ» ችግሩን ለመፍታት እየሞከረ እንደሆነ ጠቁሟል።

በከፍተኛ ወጪና አደገኛ ተልዕኮ የጽዮናዊነት ህልማቸውን ያሳኩት የኢትዮጵያ አይሁዶች በፖሊስ እና መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከተራ አባልነት ጀምሮ በተለያዩ የአዛዥነት ደረጃዎች ማገልገል ችለዋል። ይሁንና ፣ ከሌሎች እስራኤላውያን አኳያ በጣም ውስን እንደሆነ ይነገራል።የአንድ ኢትዮጵያዊ አይሁድ ገቢ ከሀገሪቱ አማካኝ የገቢ መጠን በ35 በመቶ ያነሰ ነው። የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ወጣቶች ግማሽ ያህሉ ብቻ ናቸው።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ