1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሙሥሊም ወንድማማቾች የሞት ብይን

ማክሰኞ፣ መጋቢት 16 2006

በትናንትናዉ ዕለት የግብፅ ፍርድ ቤት በ529 የሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር አባላት ላይ የሞት ቅጣት በይኗል። ዉሳኔዉ በተሰጠበት በዚሁ ችሎት 147ቱ ብቻ ናቸዉ በስፍራዉ ተገኝተዉ ፍርዱን ያደመጡ ሲሆን ቀሪዎቹ ከሚጠብቃቸዉ ፍርድ ለማምለጥ በሽሽት ላይ መሆናቸዉ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/1BVf7
529 Todesurteile bei Massenprozess gegen Islamisten in Ägypten
ምስል picture-alliance/dpa

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የካይሮ መንግስት የሞት ፍርድ ዓለም ዓቀፍ ሕግን እንደ ሚፃረር በማሳሰብ፤ ሌሎች ተመሳሳይ እጣ ይጠብቃቸዋል ያላቸዉ በሺዎች የሚገመቱ ዜጎች ሁኔታ እንደሚያሳሰበዉ ዛሬ አስታዉቋል።

ትናንት ግብፅ ዉስጥ የተላለፈዉ የሞት ቅጣት ብይን በሀገሪቱ ዘመናዊ ታሪክ የመጀመሪያዉ መሆኑ ነዉ የተገለጸዉ። ብይኑ ሲሰጥ ፍርድ ቤት በአካል የቀረቡት 147ቱ ሲሆኑ ቀሪ 398ቱ በሌሉበት ነዉ የተበየነባቸዉ። የእያንዳንዱ የክስ ሁኔታ ባለመነበቡም ማን በምን ምክንያት የሞት ብይን እንደተላለፈበት ለማወቅ ግልፅ እንዳልሆነ ነዉ የተገለፀዉ። የተከሳሽ ጠበቆች ደንበኞቻቸዉን የማነጋገርና የማግኘት እንድሉ እንዳልነበራቸዉ፤ ፍርድ ቤትም ማስረጃዎችን በማየት ከግምት የማስገባት አዝማሚያ እንዳላሳየ አመልክተዋል። ተከሳሾች በበኩላቸዉ መከላከያቸዉን ለማቅረብ እድል አላገኘንም ሲሉ ቅሬታቸዉን አሰምተዋል። የተመድ የሰብያዊ መብት ኮሚሽን ቃል አቀባይ ሩፐርት ኮልቪሊ ዛሬ ጄኔቫ ላይ በሰጡት መግለጫ በጅምላ የተበየነዉ የሞት ፍርድ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግን የጣሰ መሆኑን አመልክተዋል። በሁለት ቀናት የተካሄደ የፍርድ ሂደትም ተገቢዉ ፍትህ የሰፈነበት የፍርድ አሰጣጥ መስፈርትን አሟልቷል ማለት እንደማይቻልም ገልጸዋል። በዛሬዉ ዕለትም 682 ተጨማሪ የሙስሊም ወንድማማች ፓርቲ አባላትበመሆናቸዉ እዚሁ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ኮልቪሊ በተመሳሳይ ክስ ካለፈዉ ሐምሌ ጀምሮ የተከሰሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እስር ቤት መኖራቸዉን በጠቆም የጉዳዩን አሳሳቢነት አመልክተዋ።

Falgge Ägypten
ምስል Getty Images/AFP/Gianluigi Guercia

ተከሳሾቹ ባለፈዉ ዓመት ነሐሴ ወር ሰሜናዊ ግብፅ ዉስጥ በፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት በሰነዘሩበት ወቅት ለጠፋዉ የፖሊስ ዋና አዛዡ ሙስጠፋ አል አታር ሕይወት፤ እንዲሁም ጉዳት ለደረሰባቸዉ አራት የፖሊስ አባላት ጉዳይ ተጠያቂ ናቸዉ ተብሏል። በተጨማሪም በአካባቢዉ የመንግስት ሕንፃዎች እና የቅብጥ ቤተ ክርስቲያን ላይ ጥቃት በማድረስ ተከሰዋል። የሙስሊም ወንድማማች ማኅበር አባላት ፕሬዝደንት ሞሐመድ ሙርሲ በጦር ኃይሉ ግፊት ከስልጣን መዉረዳቸዉን በመቃወም ካይሮና አሌክሳንደሪያ አደባባይ የከተሙበትን የፀጥታ ኃይሎች ሲበታትኑ በላይኛዉ ግብፅ ግዛት ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ሕይወታቸዉን አጥተዋል። ክሱ ከአንድ ሺህ የሚልቁ ሰዎችን የሚመለከት በመሆኑም በሁለት ቡድን ተከፍሎ መታየቱ ነዉ የተገለጸዉ። ከተከሳሾቹ መካከልም የሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር ሊቀመንበሩን ሞሐመድ ባዲ አንዱ ናቸዉ። ከስልጣን የተወገዱት ሙርሲና ጠቅላይ ሚኒስትራቸዉ የነበሩት ሃሺም ቃንዲልም ተቃዋሚዎችን በመግደል፤ በሀገር ክህደትና በአሸባሪነት ተከሰዋል። የፍርዱ ሂደት ግን ባልተለመደ መልኩ እጅግ ፈጣን እንደሆነ ነዉ የታየዉ።

«የፍርድ ዉሳኔዉ በምንም መልኩ ትክክለኛዉን ሂደት ተከትሎ የተሰጠ አይደለም። እንዲህ ያለ በ1200 ሰዎች ላይ በሁለት ችሎት ፊት ተከላካይ ጠበቆችም የመከላከያ ምስክርነታቸዉን በአግባቡ ሊያቀርቡ በማይችሉበት ሁኔታ የተካሄደ ነዉ።»

Mohammed Badie hinter Gittern
ምስል Ahmed Gamil/AFP/Getty Images

ይላሉ እዚህ ጀርመን ማይንዝ የሚገኘዉ የአረብ ጥናት ማዕከል የግብፅ ጉዳይ ተንታኝ ጉንተር ማየር። እሳቸዉ እንደሚሉትም ከፍርድ አሰጣጡ ጀርባ የሀገሪቱ ወታደራዊ መንግስት ድጋፍ አለበት የሚል ጥርጣሬ ያስከትላል። ግብፅ ዉስጥ ሰዎች የዚህ ቡድን አባል በመሆናቸዉ ፍርድ ቤት ቀርበዉ የሞት ቅጣት እንደሚበየንባቸዉ ከገመቱም በይፋ መንቀሳቀሱ ቀርቶ ህቡዕ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ከወዲሁ ገምተዋል፤

«ይህ ብይን የሚያሳየን ምልክት የግድ ህቡህ መግባት እንደሚኖርብን ነዉ፤ ዓላማችን ግቡ እንዲመታ ከፈለግንም ከፀጥታ ኃይሎች ጋ በስዉር ለመታገል ኃይል መጠቀም ይኖርብናል የሚል ነዉ»

የግብፅ መንግስት ሙስሊም ወንድማማች ፓርቲን በአሸባሪነት ፈርጆ እንቅስቃሴዉን ካገደ ወራት ,ቆጥረዋል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ግብፅ ዉስጥ እንዲህ በጅምላ አይሁን እንጂ የሞት ቅጣት ሲበየን የመጀመሪያዉ አይደለም። ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1981 እስከ 200ዓ,ም ድረስ 709 ሰዎች ላይ ሞት ተፈርዷል፤ ሆኖም 248 ላይ ነዉ ተፈፃሚ የሆነዉ። ከተጠቀሰዉ ዓመት ወዲህ ደግሞ በ2010ዓ,ም ነዉ 185 ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት ተበይኖ አራቱ ላይ ተግባራዊ የሆነዉ።

ዲያና ሆዳሊ/ ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ