1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሙስና ክሶችና ደቡብ አፍሪካ

ዓርብ፣ መስከረም 12 1999

የቀድሞዉ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ጃኮብ ዙማ ተመስርቶባቸዉ ከነበረዉ የሙስና ክስ ነፃ ናቸዉ ተባሉ።

https://p.dw.com/p/E0i7
ዙማ ከስልጣን ሲሰናበቱ
ዙማ ከስልጣን ሲሰናበቱምስል dpa

የዙማ ደጋፊዎች ክሱ የፈጠራ ነዉ ይላሉ። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸዉ ወገኖች ደግሞ ለጊዜዉ ነፃ ቢለቀቁም ተጠያቂነታቸዉን መሸከማቸዉ እንደማይቀር ይናገራሉ።

ከዳኞቹ አንዱም ዙማ በስልጣን ላይ ሳሉ ከገንዘብ ጉዳይ አማካሪያቸዉ ጋር የሙስና ግንኙነት ነበራቸዉ በሚል ዉሳኔዉን ተቃዉመዉ ይግባኝ ጠይቀዋል።

የዙማ የገንዘብ ጉዳይ አማካሪ በሙስና ወንጀል ተከሰዉ 15 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዉ ወህኒ ወርደዋል።

ዙማ ከደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝደንትነት ያስወገዳቸዉ ሁለት ዓይነት ክስ ነበር። ሙስናና አስገድዶ መድፈር።

የኤችአቪ ቫይረስ በደሟ ዉስጥ ካለ ቤተኛቸዉ ጋር ጥንቃቄ የጎደለዉ ወሲብ በግዳጅ ሳይሆን በመፈቃቀድ ፈፅሜያለሁ ብለዉ በአደባባይ ንስሃቸዉን በመናገር ይህ ክስ ከወደቀ ሰነበተ።

ከትናንት ወደያ ደግሞ የሙስና ግንኙነትን ከሚያትተዉ ሁለተኛዉ ክስ የፒተርማሪትዝበርግ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በነፃ አሰናበታቸዉ።

ዳኞዉ ለዉሳኔያቸዉ የሰጡት ምክንያት ዙማ የተጠረጠሩበትንየጉቦ ገንዘብ ክስ የሚያጠናክረዉ ረብ ያለዉ ማስረጃ በወቅቱ አልቀረበም የሚል ነዉ።

ዉሳኔዉን ካልደገፉት መካከል ፕሪቶሪያ የሚገኘዉ የደህንነት ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ጃኬ ሞሎይ አስተያየታቸዉ ይህን ይመስላል።

«አሁን የተገኘዉ ጊዜያዊ ድል ነዉ። ከፍርድ ቤቱ የተሰጠዉ ዉሳኔ ለጊዜዉ የዙማን ደጋፊዎችና ወዳጆች ስሜት በማጠናከር ሊያግዝና ሊያስጨፍር ይችላል። ለዙማም ቢሆን ትልቅ የሚያኩራራ ድል ነዉ። ነገር ግን ደመናዉ በአናታቸዉ ላይ እንዳንዣበበ ነዉ። አንደኛዉ ዳኛ ከቀድሞዉ የገንዘብ አማካሪያቸዉ ጋር የጥቅም ትስስር እንደነበር በይፋ ተናግረዋል።»

ዙማ ከስልጣናቸዉ ሲሰናበቱ ፅህፈት ቤታቸዉ በተፈተሸበት ወቅት የተገኙትን ሰነዶች ለማየት አቃቤ ህግ ከመንግስት ወገን ባለ የህጋዊነት ጥያቄ እንዳልተሳካላቸዉ ተጠቅሷል።

ዳኛ ሄርበት ማሲማንግ አቃቤ ህግ በመንግስት ቁጥጥር ስር ይገኛል የተባለዉን ጠቃሚ መረጃ በተፈለገዉ ሰዓት አላቀረበም በሚል ዉሳኔዉን አሳልፈዋል።

ዳኛዉ ዙማ ነፃናቸዉ የሚለዉን ዉሳኔ በማሳለፍ ብቻም አላበቁም፤ ዙማን ለመክሰስ የተጣደፈ ዉሳኔ ላይ ተደርሷል ያዉሳኔም የፍፃሜዉ መጀመሪያ ሆኗል ካሉ በኋላ። በዚህ ምክንያትም የደቡብ አፍሪካ መንግስት ከአንድ ሰንካላ ነገር ወደሌላ ችግር ዉስጥ ገብቷል ሲሉም መንግስትንም ተችተዋል።

ያም ሆነ ይህ ዙማ ከትናንት በስተያ ፍርድ ቤቱ የሰጣቸዉ የዉሳኔ ፍርድ ከወጥመድ እንዲወጡ አድርጓቸዋል።

የአገሪቱ ብሄራዊ አቃቤ ህግ ባለስልጣን በድጋሚ በክሱ ሊገፋ ያስባል ከቀድሞ የገንዘብ ጉዳይ አማካሪያቸዉ ጋር በመተባበር ለደቡብ አፍሪካ መሳሪያ ከሚያቀርበዉ የፈርሳይ የጦር መሳሪያ ኩባንያ 70,000 ዶላር ወስደዋል በሚል።

ዙማ ግን ክሱን ሁሉ ያገናኙት ቀደም በለዉ በግንባር ቀደምትነት ታስበዉበት ለነበረዉ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት የመሆን እድላቸዉን ለማጨናገፍ ከሚደረጉ ደባዎች ጋር ነዉ። ይህን አመለካከት ደግሞ የዙማ ደጋፊዎች ይጋሩታል።

ብዙዎች እንደሚሉት ክሱ ዉድቅ መደረጉ ዙማ በፕሬዝደንታዊ ምርጫ ለመወዳደር መንገድ ይከፍትላቸዋል።

የፕሬዝደንት ታቦ ምቤኪ ሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸዉ የሚያበቃዉ ደግሞ በአዉሮፓዉያኑ 2009 ይሆናል።

በመጪዉ የአዉሮፓያኑ ዓመት ደግሞ ፓርቲያቸዉ ANC መሪዉና በቀጣይ ለፕሬዝደንትነት የሚወዳደረዉን ሰዉ ይመርጣል።
ምክትል ፕሬዝደንታቸዉ የሆኑት ወይዘሮ ፉምዚለ ምላምቦ ናጉካ ስልጣኑን የመከብ ፍላጎት እንዳሉ ያሳዩት ነገር የለም።

ሆኖም ምቤኪ የስልጣን ተረካቢያቸዉ ሴት እንጂ ወንድ እንደማይሆን ፍንጭ ቢጤ በመስጠታቸዉ ጉዳዩ የዙማን ደጋፊዎች የሚያነጋግር ሆኗል።

ከANC ጋር ህብረት የፈጠረዉ የደቡብ አፍሪካ የሰራተኞች ማህበር ጉባኤ ላይ ባለፈዉ ሳምንት ምላምቦ ናጉካ በተገኙበት ወቅት ተሳታፊዎቹ ባለቤታቸዉን የሚተች መዝሙር አዚመዉባቸዋል።

ባለቤታቸዉ ዙማን ከስልጣን ለማባረር ባይከሷቸዉም በወንጀል ወጥመድ ተብትበዉ አስገብተዋቸዋል በሚል ይጠረጠራሉ።

የዙማ ከሙስና ክስ ነፃ መለቀቅምና የፍርድ ቤቱ ዉሳኔ ግን የአገሪቱን የፖለቲካ ኃይላት እያነጋገረ ነዉ።