1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሙቀት ማዕበል እና አውሮጳ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 1 2010

ረዘም ባለው የክረምት ወራት ከዜሮ በታች የሙቀት መጠን የሚያስተናግዱት የአውሮጳ ሃገራት በዘንድሮው የበጋ ወቅት ከፍተኛ የሙቀት ማዕበል አስጨንቋቸዋል። በጋው በሙቀት ብቻ አልተገታም የዝናብ አለመኖር ቃጠሎ ብሎም ድርቅ ማስከተሉ እየታየ ነው።

https://p.dw.com/p/32lW9
Bildergalerie Hitzewelle in Europa Schweiz
ምስል picture-alliance/dpa/V. Flauraud

ከስድስት ወራት በላይ በቅዝቃዜ እና በበረዶ መሰንበት የለመደበት ምድረ አውሮጳ የሰሜኑን ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት ተንተርሶ ላለፉት ሳምንታት ከመጠን ባለፈ የሙቀት ማዕበል እየተናጠ ነው። ያን አጥንት ድረስ ዘልቆ የሚሰማ መደበኛ ልብስ ሙቀት የማይፈጥርለት ቅዝቃዜ የተላመደው የዚህ ክፍለ ዓለም ኗሪ ራቁት እያስኬደ የሚገኘው የሙቀት ማዕበክ ከሰሃራ በሰሜን አፍሪቃ በኩል አላባራ እንዳለው የሰዎች ሕገ ወጥ ስደት ሁሉ ሜዲትራኒያንን አቋርጦ ቢጫማውን የአሸዋ ቡናኝ ሳይቀር አስከትሎ ወደ አውሮጳ ሃገራት መዝለቁን መገናኛ ብዙሃኑ የዘርፉን ምሁራን እያጠያየቁ ማብራሪያ በመስጠት ተግባር ተጠምደዋል። መረጃዎቹ እንደሚጠቁሙት ይህ ከአፍሪቃ የተሻገረ የሙቀት ማዕበል የጠናባቸው በደቡብ ምዕራብ የሚገኙ የአውሮጳ ሃገራት ቢሆኑም ካለፉት ሦስት ሳምንታት አንስቶ በሙቀት ያልተጨነቀ የአውሮጳ ሀገር የለም ማለት ይቻላል። ሙቀቱ ከ40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ የተመዘገበባት የፖርቱጋል ባለስልጣናት በዚሁ ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት የጤና ችግር ሊከተል እንደሚችል እያሳሰቡ ነው። በተመሳሳይ ከ50 የስፔን ግዛቶች ለ40ዎቹ ይኸው ማሳሰቢያ ተላልፏል። ለወራት በብርድ ተቆራምዶ የሚሰነብተው አውሮጳዊ አቅም በፈቀደ ሞቃት የአየር ጠባይ ፍለጋ ወደተለያዩ የባህር ዳርቻ መዝናኛ ወዳላቸው ሃገራት መጓዝ የተለመደ ነው። ዘንድሮ ግን ታይቶም አይታወቅ የተባለለት አልበርድ ያለው ሙቀት ከየመንደሩ መጥቶለት ይርገም ይመርቅ ግራ የተጋባ መስሏል።

የሙቀት መጠኑ ባሳለፍነው የሳምንት መጨረሻ በተለይ በስፔን፣ ጣሊያን እና ፈረንሳይ ከ35 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ መድረሱ ተመዝግቧል። በተለይም የሙቀት መጠኑ ከ40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ በሆነባት ፖርቱጋል በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል ደን ውስጥ የተነሳው የሰደድ እሳት ዛሬም አልበረደም።  በበጋ ደመና አልባ ሰማያዊ ሰማይ የሚፈጥረው ውስጣዊ መነቃቃት እና ደስታ እንዳለ ሆኖ ከፀሐያማው የአየር ጠባይ ጀርባ በርካታ መዘዞች እንደሚከተሉ በማስተዋል ብዙዎች ስጋታቸውን እያሰሙ ነው። እጅግ ሞቃቱ የአየር ሁኔታ የሰደድ እሳቶችን በያለበት በመጫር ሳይወሰን ሰብል ማበላሸት ፤ የውኃ መጠንን የመቀነስ እና የሰው ሕይወት የመቅጠፍ አደጋ ስጋትን አስከትሏል።

Bildergalerie Hitzewelle in Europa Italien
ምስል picture-alliance/dpa/A. Carconi

ጎርሪዮሳዊዉ 2016ዓ,ም እጅግ ሞቃት የተባለው ዓመት በመሆን ተመዝግቧል። ያኔ በአየር ንብረት ለውጥ እና ኤሊኒኞ በተሰኘው የወቅት ክስተት የመጣ ከፍተኛ ሙቀት መሆኑ ነበር የተገለጸው። ዘንድሮ ተቃራኒ የሆነው የወቅት ክስተት ላኒኛ ነው ቢባልም የሚጠበቀው ቅዝቃዜ ቀርቶ ከሰኔ ወር አንስቶ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ተመዝቧል። የዓለም የሜቲሪዎሎጂ ድርጅት ለዶይቼ ቬለ እንዳረጋገጠውም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከዚህ በፊት የታየው ክስተት እንዳመለከተው ከመጠን ያለፈ እና ተደጋጋሚ የሙቀት ማዕበል ሊያጋጥም ይችላል። ለደቡባዊ የአውሮጳ ሃገራት ሞቃት አየር እጅግም እንግዳ አይደለም። የሰሜን አውሮጳ አብዛኛው ነዋሪ ከጥቅምት ወር ጀምሮ አንዳንዴ እስከ ሚያዚያ እና ግንቦት ከሚራዘመው የክረምት ቅዝቃዜ ተፅዕኖ አካል መንፈሱን ለማፍታታት ወደእነዚህ ሃገራት መጓዙም የተለመደ ነው። እንደ እንግሊዝ እና አየርላንድ ያሉት በሰኔ ወር ግፋ ቢል 20 ዲግሪ ሴንትግሬድ ብቻ የነበራቸው ሙቀት ዘንድሮ 30 እና ከዚያ በላይ ዲግሪ ሴንት ግሬድ መድረሱ በትክክል የአየር ንብረት ለውጥ ሚናው እየጎላ መምጣቱን ምስክር ሆኗል የሚሉት ይበረክታሉ።

ሙቀቱ የጫረው የሰደድ እሳት

በበጋው  ወራት ሙቀት በሚያይልባቸው የተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት የሰደድ እሳት መነሳቱ እንግዳ አይደለም። ብዙውን ጊዜ አስቀድመው ስለሚዘጋጁበትም በሰው ሕይወት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት መቀነስ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ይበረክታሉ። ዘንድሮም እንደተለመደው የፖርቱጋልን ደኖች ሰደድ እሳት እያነደደ ሲሆን በግሪክም እንዲሁ እሳት የደሴት ላይ መንደሮች እና ደን እያቃጠለ መሆኑ እየተነገረ ነው። የግሪክ እሳት 79 ሰዎችም ገድሏል። ስዊድንም እንዲሁ ከበረዷማው የክረምት የአየር ጠባይ ተላቃ ወደ በጋው ስትሻገር 60 ሚሊየን የተገመተው የደን ሀብቷ በሰደድ እሳት ጋይቷል።  

ድርቅ በጀርመን

ጀርመን በአረንጓዴነታቸው ደምቀው ከሚታዩ የአውሮጳ ሃገራት አንዷ ናት። የበጋው ወራት ገና በጥቅምት እና ሕዳር ወር ቅዝቃዜ ቅጠሎቻቸው ረግፈው በክረምቱ እንጨታቸው ብቻ ቀርቶ የከረሙት ዛፎች ለምልመው የሚታዩበት ነው። በደኑ ውስጥ ለሚንቀሳቀሰውም ሆነ በአቅራቢያው ለሚገኘው ነፋሻማ አየር የሚያተርፉ ነበሩ። የእነሱ መኖርም በሞቀው የበጋ ወቅት በየጣልቃው ዝናብ የመጋበዝ አዝማሚያቸውም የተለመደ ነበር። ዘንድሮ ለተከታታይ ሳምንታት ከ30 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ለበለጠው የበጋው ወቅት የአየር ጠባይ ግን ዛፎቹ መፍትሄ መሆን አቅቷቸው ለራሳቸውም መተንፈስ ያቃታቸው መስለው ይታያሉ። በሰሜን እና ምሥራቅ ጀርመን አካባቢ ከ10 ሳምንታት በላይ ዝናብ አለመኖሩ በእርሻ ምርቱም ሆነ በውኃው ክምችት ላይ ጫና ማሳደሩ እየተነገረ ነው። የጀርመን ገበሬዎች ማኅበር እንደገለፀው ድርቁ የዘንድሮው ምርት 20 በመቶ እንዲቀንስ ሳያደርገው አይቀርም። የጀርመን የግብርና ሚኒስትር ዩሊያ ክሎክነር ድርቁ የሀገሪቱን የግብርና ዘርፍ እንደጎዳ አመልክተዋል።

Deutschland - Ernteausfall wegen Trockenheit
ምስል picture alliance/dpa/P. Pleul

«ድርቁ እዚህ ጀርመን ውስጥ ገበሬዎቻችንን ክፉና እያጠቃ ነው። ለወራት ይህ ነው የሚባል ዝናብ አልነበረም። አፈሩ ደርቋል፤ ይህ ድርቅ በብዙዎቹ የጀርመን ገበሬዎች ቤተሰቦች ላይ ሊያስከትል የሚችለው መዘዝ እጅግ እንዳሳሰበኝ እገልፅላችኋለሁ። ከብት አርቢዎች ለእንስሶቻቸው የሚመግቡት ተቸግረዋል፤ ምክንያቱም ለመኖ የሚሆናቸው ሳር የለም።እንደምታውቁት መጀመሪያ ለመኖ የሚሆነው ሳር ታጭዷል፤ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ደረጃ የሚታጨድ አልተኘም።»

በፍራንክፈር ት አካባቢ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በእርሻ ሥራ መሠማራታቸውን የሚገልፁት ዶክተር ማቲያል ሜህል እንዲህ ያለ ሙቀት በሀገሪቱ አጋጥሞ አያውቅም ይላሉ።

«ላለፉት 25 ዓመታት በእርሻ ሥራ ላይ ነው የተሰማራሁት፤ እንዲህ ያለ የሙቀት ማዕበል አይቼ አላውቅም። በዚህ ምክንያት በእኛ አካባቢ ስመለከተው በግብርናው ዘርፍ የሚገኘው ትርፍ እስከ 20 በመቶ ሊቀንስ ይችላል፤ በሌላ የጀርመን አካባቢ ከ40 እስከ 70 በመቶ ሊደርስ ይችላል።»

እሳቸው እንደሚሉት በሚኖሩበት የፍራንክፈርት አካባቢ በግብርና ምርቶች ላይ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል ይህንኑ ክስረት ለማካካስ። በተለይ በምሥራቅ እና ሰሜን ጀርመን አካባቢ ለሚገኙ ገበሬዎች ሥራቸውን ሊያደናቅፍ እና በግብርናውም እንዳይገፉበት ሊያደርግ የሚያስችል ክስረት በመኖሩ ትርጉም ያለው ርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲሉም ያሳስባሉ። ጀርመን እርሻው በማሽኖች የሚታገዝ ዘመናዊ ፤ አስፈላጊዉ ግብአት እና ትኩረትም ከመንግሥት የሚያገኝ መሆኑ ይታወቃል። በግብርናው የተሠማሩት ዶክተር ማቲያል ሚህል ከዚህ የተሻለ ድጋፍ ለጀርመን አርሶ አደሮች መደረግ አለበት ይላሉ።

Sommerwetter in Deutschland
ምስል picture-alliance/dpa/P. Pleul

«በአሁኑ ወቅት በትክክል የሚያስፈልገን ዘመናዊ ግብርና ላይ ያተኮረ ምርምር ነው፤ ሰብልን በዘመናዊ መንገድ የሚያበቅል ቴክኒክ ያስፈልገናል፤ ተክሎችን በዘመናዊ መንገድ መከላከል የሚችሉ ምርቶች እንሻለን፤ በዲጂታል ስልት ልንታገዝ ይገባል፤ ዘመናዊ የበሽታ መከላከያ እና ሰብሉን ውኃ ማጠጫም ያስፈልገናል። ኅብረተሰቡ በግብርናው ዘርፍ ላይ ከፍ ያለ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ ይኖርበታል።»

የግብርና ሚኒስትሯ ዩሊያ ክሎክነርም ድርቅ ላሰጋው የጀርመን የግብርና ዘርፍ ትኩረት መስጠቱ የእያንዳንዱን ቤት የሚያንኳኳ የሕይወት ጉዳይ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ለመንግሥታቸውም ሆነ ለመላው አውሮጳ አሳስበዋል።

«ሁላችንም በአንድ ጀልባ ውስጥ ነው የተቀመጥነው። ይህ ጀርመን ውስጥ ገበሬዎቻችን የሚያመርቱት ምርት እንደሌላው ዕቃ አይደለም፤ ይህ በእያንዳንዳችን ማዕድ ላይ የሚቀርብ የዕለት እንጀራ ነው። ለመኖር ደግሞ ወሳኝ ነው። ለዚህ ነው ለሁላችንም እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው።»

አውሮጳን እያስጨነቀ የሚገኘው ከፍተኛ ሙቀት ካስከተለው ድርቅ በተጨማሪ የጤና እክልም ሊያመጣ እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች እያሳሰቡ ነው። በሀርቫርድ ቻን የማኅበረሰብ ጤና ተቋም የተካሄደው ጥናት እንዲህ ያለ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ባለበት የአየር ጠባይ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ለተለያዩ የጤና ችግሮች መጋለጣቸው እንደማይቀር አመልክቷል። በተለይ ደግሞ በአግባቡ ለማሰብ እንደሚያዳግት ያመለከተው ይኸው ጥናት በኃይለኛው ሙቀት ሳቢያ የሰዎች የማሰብ አቅም በ13 በመቶ እንደሚቀንስ ዘርዝሯል። ከዚህም ሌላ የሙቀት መጠኑ በጣም ከፍ ሲል ኬሚካዊ ውጤቶችን ስለሚያፋጥን በአየር ውስጥ የሚኖረውን ብክለት መጠንም እንደሚጨምር፤  ይህ ደግሞ በሰዎች የመተንፈሻ አካል እና የልብ ሥርዓተ እንቅስቃሴን እንደሚያውክም ገልጿል። የዓለም የጤና ድርጅት የአውሮጳ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ኃላፊ ቭላድሚር ኬንድሮቭስኪ ከሌላው የአየር ጠባይ በሙቀት ማዕበል ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እጅግ እንደሚጨምር ነው የተናገሩት። በዚህ ወቅት ሰለባዎች የሚሆኑት ደግሞ ሰዎች በርክተው በሚኖሩባቸው የከተማ አካባቢዎች የሚገኙ ሕጻናት እና እድሜያቸው የገፋ ወገኖች መሆናቸውም ተገልጿል። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2003ዓ,ም አውሮጳን የመታው የሙቀት ማዕበል በመላው አህጉር ለ70 ሺህ ሰዎች እልቂት ምክንያት መሆኑ ተመዝግቧል። በዚህ ወቅት በጀርመን ብቻ ሙቀቱ 7 ሺህ ሰዎችን ፈጅቷል። የዚህ ዓመቱ ከፍተኛ የሙቀት ክስተት የአውሮጳ ሃገራትን ብቻ አይደለም የነካው እስያ እና አውስትራሊያም እንዲሁ መጨመሩ የደን ቃጠሎን ማባባሱ ተነግሯል። ጀርመንን በተመለከተ ግን ሙቀቱ እስከ ነገ ከፍ ብሎ እንደሚቀጥል እየታየ ነው፤ ምናልባት ሐሙስ ዝናብ ከጀርመን ሰማይ ይወርዳል ተብሎ ተስፋ ተደርጓል።  ተፈጥሮ የደገሰችው ውሎ አድሮ የሚታይ ይሆናል።  

Deutschland - Ernteausfall wegen Trockenheit
ምስል picture alliance/dpa/S. Gollnow

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ