1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሙባራክ ከሥልጣን መውረድ ያሳደረው ስሜትና ያስሠነዘረው አስተያየት፣

ሰኞ፣ የካቲት 7 2003

ጥር 17 ቀን 2003 ዓ ም፤« የቁጣ መግለጫ ዕለት» በሚል መፈክር ፣ የሆስኒ ሙባረክን መንግሥት በመቃወም፣ ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን ይወርዱ ዘንድ ለማሳሰብ አደባባይ መውጣት የጀመሩት ፣ ግብጻውያን ትናንት ከቀትር በኋላ በ 18 ቀናት ትግል ፣ ፈላጭ ቆራጭ ይሰኙ የነበሩትን መሪአቸውን ፣ ከሥልጣን እንዲወርዱ አስገድደዋል።

https://p.dw.com/p/R0LF

የሙባረክ ከሥልጣን መሰናበት በቴሌቭዥን እንደተነገረም ፣ ህዝቡ በነቂስ አደባባይ በመውጣት ደስታውን በጭፈራ ሲገልጥ ማምሸት ብቻ ሳይሆን አንግቷል። የፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክን በህዝብ ግፊት ከሥልጣን መወገድ በተመለከተ በዓለም ዙሪያ የመንግሥታት መሪዎችና ጋዜጦች የተለያዩ አስተያየቶችን ሠንዝረዋል። ተክሌ የኋላ አሳባስቦ የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅሯል።

«የ 30 ዓመት የአምባገነንነት ግንብ በ 30 ሴኮንድ ፈረሰ ፣» ይህን ያለው የብሪታንያው ጋዜጣ ፣ The Guardian ነው። ከግብጽ ሁለት ታዋቂ የመንግሥት ጋዜጦች መካከል ኧል አህራም፣ «የወጣቶች አብዮት ሙባራክን ከስልጣን እንዲወርዱ አስገደደ» ሲል፣ ኧል ጎምሁሪያ ፣ «የጥር 17ቱ አብዮት ድል አደረገ። ሙባረክ ከሥልጣን ተወገዱ፤ ጦር ኃይሉ እያስተዳደረ ነው!» ሲል ጽፏል።

ባለፈው ታኅስስ በቱኒሲያ የተጀመረው፣ የህዝብ አመጽም ሆነ መነሣሣት፣ ፕሬዚዳንት ቤን ዓሊን አገር ለቀው እንዲኮበልሉ ሲያስገድድ ፣ በዓረቡ ዓለም በህዝብ ብዛት የመጀመሪያውን ደረጃ የያዘችውን አገር መሪም ከ 30 ዓመታት አገዛዝ በኋላ ከሥልጣን እንዲወርዱ አብቅቷል። ግብጻውያን ፤ «ነጻነት፣ ሰብአዊ ክብርና ዴሞክራሲ» ሊኖራቸው እንደሚገባ በአጽንዖት ሲያሳስቡ በሰነበቱበት ውቀት፣ ምዕራባውያን መንግሥታት ተገቢ ነው ሲሉ ለግብጻውያኑ ሰልፍ ሞራላዊ ድጋፍ መስጠታቸው አይዘነጋም። የጀርመን ህዝብና የፖለቲካ መሪዎች፣ በግብፅ በመጨረሻ የተከናወነውን ድርጊት በቀዝቃዛው ጦርነት ፍጻሜ፤ የበርሊን የግንብ አጥር ከፈረሰበት ሁኔታ ጋር ሳያመሳስሉት አልቀሩም። በመሆኑም፣ የሙባረክን ከሥልጣን መውረድ፣ በደስታና እርካታ ነው የተቀበሉት። ስሜትን መግለጽ ብቻ ሳይሆን ፣ የጀርመን ፌደራል መንግሥት፣ የግብፅን የተሃድሶ ለውጥ በገንዘብ ለመደገፍም ቃል ገብቷል። የጀርመን መራኂተ መንግሥት ወ/ሮ አንጌላ ሜርክል፤ የሙባረክ ሥልጣን መልቀቅ ከተገለጠ በኋላ ፤ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ፣ሙባረክ ከሥልጣን መሰናበታቸው፣ ለህዝብ ይበጅ ዘንድ በመጨረሻ የፈጸሙት ተግባር ነው ብለዋል። ዕለቱ የተለየ ስለመሆኑም ሲገልጡ፤--

«ዛሬ ታላቅ ሐሴት የሚደረግበት ዕለት ነው። እኛ ሁላችን የአንድ ታሪካዊ ለውጥ ምሥክሮች ነን። ከግብፅ ህዝብ ጋር ፣ በሚሊዮን ከሚቆጠሩት አደባባይ ከወጡት ጋራ ደስታቸውን እጋራለሁ»

የጀርመን መራኂተ መንግሥት፤ ለውጥ ያሳየው የግብፅ ማኅበረሰብ፤ ባለፉት ሳምንታት ያሥመሠከረውን ትጋትና ደፋርነት ለቀጣይ ለውጥ እንዲገፋበት፣ ያላቸውን በጎ ምኞት ከመግለጻቸውም፣ አሁን የተጀመረው ጎዞ ነጻና ፍትኀዊ ምርጫ እንዲካኼድ የሚስችል ሊሆን ይገባል ብለዋል።

«አሁን ኀላፊነቱን የተሸከሙትን ና ወደፊትም የሚሸከሙትን፣ በግብፅ የተጀመረውን ታሪካዊ ሂደት እንዳይቀለብሱት፣ ሂደቱንም በሰላማዊ መንገድ ተግባራዊ ያደርጉት ዘንድ እጠይቃለሁ። ባለፉት ቀናት ህዝቡ ያቀረባቸው ፣ አግባብ ያላቸው ጥያቄዎች ፤ በእውን ሥራ ላይ ሊውሉ ይገባል።»

ግብፅና እሥራኤልን የሰላም ውል እንዲፈራረሙ ያበቃችው ፤ የሁለቱም ወዳጅ መሆኗ የሚነገርላት፣ የመካከለኛውን ምሥራቅ ይዞታ ምንጊዜም በጥሞና የምትከታተለው ኀያል መንግሥት ዩናይትድ እስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ ያለፉትን ሳምንታት የግብፅ ሂደት በመገምገም ፤\{ በግብፅ ታሪክ ይሠራል » ካሉ ወዲህ፤ ሆስኒ ሙባረክ ከካይሮው ቤተ-መንግሥታቸው ለቀው ከወጡና ስልጣን መልቀቃቸው ከተገለጠ በኋላ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል።

«በህይወት ዘመናችን፣ ታሪክ ሲሠራ መመሥከር የምንችልበት አንዳንድ ጥቂት ቅጽበቶች ይኖራሉ። ይህ ከእነዚያ ጥቂት ቅጽበቶች መካከል አንዱ ነው። ይህ ከእነዚያ ጊዜያት መካከል አንዱ ነው። የግብፅ ህዝብ ተናግሯል ፤ ድምፁም ተሰምቷል ፤ እናም ግብጽ ከእንግዲህ በምንም ዓይነት ድሮ ወደነበረችበት አትመለስም። »

የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ፣ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ የብዙኀኑን የህዝብ ድምፅ ተገንዝበው ሥልጣን መልቀቃቸው የሚስከብርና አስፈላጊ እርምጃ ነው የወሰዱት ሲሉ አድንቀዋቸዋል። አያይዘውም፤ ግብጻውያን በመላ ለነጻነት የሚያደርጉትን ትግል እንዲገፉበት ፈረንሳይ ጥሪ ታቀርብላቸዋለች ብለዋል።

የብሪታንያው ጠ/ሚንስትር ዴቪድ ኬምረን፣ ነጻ ወደምትሆን ዴሞክራሲ ወደሚገነባባት ግብፅ የሚያሸጋግረው መንገድ ፤ የሲቭል ዴሞክራቲክ አስተዳደር መመሥረት ያስችል ዘንድ አሳስበዋል። የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚዳንት ጄኮብ ዙማ፣ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ፣ እንደ ትክክለኛ መሪ በማሰብ ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ የህዝባቸውን ጥቅም አስቀድመዋል በማለት አወድሰዋቸዋል።

ተክሌ የኋላ፣