1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚሌኒየሙ ዕቅድ፤ የቻይናና ጃፓን ግንኙነት

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 13 1997
https://p.dw.com/p/E0em
የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር በም/ቤት ስለውዝግቡ ሲናገሩ
የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር በም/ቤት ስለውዝግቡ ሲናገሩምስል AP/Kyodo News

በቅድሚያ በመጀመሪያው ነጥብ ላይ እናተኩርና የምድራችን ግማሽ ሕዝብ ዛሬ ኑሮውን የሚገፋው ከአንዲት ዶላር ባነሰች ዕለታዊ ገቢ ነው። ይህ ደግሞ በተለይ በሕዝብ ብዛታቸው ግዙፍ በሆኑት ሁለት የእሢያ አገሮች በቻይናና በሕንድ ነው ጎልቶ የሚታየው። ይሁንና በነዚህ በሕዝብ ብዛት በካበቱ አገሮች የተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት እየሰፈነ በመሆኑ በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎቻቸው በሚቀጥሉት ዓመታት ዝቅተኛውን የድሕነት ደረጃ እየለቀቁ መሄዳቸው የማይቀር ነው።

በአንጻሩ በተቀሩት በአብዛኞቹ ታዳጊ አገሮች ግን የድሃው ቁጥር ጠንከር ባለ መልክ ይቀንሳል ተብሎ አይጠበቅም። የዓለም ባንክና የምንዛሪው ተቋም IMF እንደሚያስገነዝቡት በተለይ ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል ተሥፋው በጣሙን የደበዘዘ ነው። ሁለቱ የገንዘብ ተቋማት በቅርቡ ባወጡት ዘገባ መሠረት በነዚህ የአፍሪቃ አገሮች እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ የድሃው መጠን እንዲያውም 10 በመቶ እንዳይጨምር ያሰጋል። ዓለምአቀፉ የልማት ፖሊሲ እስካሁን ባለ መልኩ ከቀጠለ ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኙት አገሮች የተቀሩትን የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒዬም ዕቅዶች ከግብ ማድረሳቸውንም ማመኑ ሲበዛ ያዳግታል። “Global Monitoring Report” የተሰኘውን የጋራ ዘገባ ያረቀቁት የዓለም ባንክ ባልደረባ ዚያ ኩሬሺ የተፈራው እንዳይደርስ ከተፈለገ መወሰድ የሚኖርበትን ዕርምጃ እንደሚከተለው ያመላክታሉ፤

“የልማት ዕርዳታው በሰፊው መጨመር ይኖርበታል። ተረጂዎቹ አገሮችም የራሳቸውን የፖለቲካ ይዘት ማሻሻላቸው ግድ ነው የሚሆነው። የሚያገኙትን የልማት ዕርዳታ በተሻለ ሁኔታ ሥራ ላይ ማዋል መቻል ይጠበቅባቸዋል። የልማት ዕርዳታው መጨመር በበለጠ ዕድገትና የድሃውን ሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎት በማሟላት ላይ ያለመ ሰፊ የአሠራር ስልት አንድ አካል መሆን አለበት። እንግዲህ የልማት ዕርዳታው መጨመር ብቻውን ለችግሩ ምላሽ ሊሆን አይችልም።”

እርግጥ የገንዘብ ተቋማቱ ዘገባ አፍሪቃን በተመለከተ ጨርሶ ተሥፋን የሚያቆረቁዝ አይደለም። ጋናን፣ ማሊን፣ ሞዛምቢክን፣ ታንዛኒያንና ኡጋንዳን የመሳሰሉ 12 ሃገራት ባለፉት አሥር ዓመታት በአማካይ 5.5 በመቶ ዕድገት ማድረጋቸው ተመልክቷል። ይህም የሚያበረታታ ነው። ግን በዓለም ባንክና በምንዛሪው ተቋም ግምት መሠረት በአፍሪቃ ከሚሌኒየሙ ግብ ለመድረስ ሰባት በመቶ ዕድገት የግድ አስፈላጊ ነው። የዘገባውን አቅራቢዎች ይበልጥ አሳስቦ የሚገኘው በተለይ በጤና ጥበቃው ዘርፍ ያለው ሁኔታ ነው። በዚህ በኩል ፈጣንና ተዓምራዊ ለውጥ ካልተደረገ ከሚሌኒየሙ ግብ እንደማይደረስ ከአሁኑ በግልጽ ነው የተነገረው።

“በየሣምንቱ ዕድሜያቸው ከአምሥት ዓመት በታች የሆነ 200 ሺህ ሕጻናት በበሽታ ያልቃሉ። በየሣምንቱ አሥር ሺህ ሴቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ችግር ይሞታሉ። ካሣሃራ በስተደቡብ ባለው የአፍሪቃ ክፍል ብቻ በዚህ ዓመት ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ በኤይድስ እንደሚሞት ነው የሚጠበቀው። ከ 115 ሚሊዮን የሚበልጡ ሕጻናት ደግሞ የትምሕርት ዕድል አያገኙም። ....” ይላሉ የዓለም ባንኩ ባልደረባ ዚያ ኩሬሺ!

በዕውነትም ከዚህ አንጻር እስከ 2015 ማለት በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ ዕቅዱ መሳካቱ ቀርቶ ጥቂት ዕርምጃ መታየቱ እንኳ ሲበዛ የሚያጠያይቅ ነው። የ HIV-AIDS መስፋፋት ሂደት ነው በተለይ ችግሩን ይበልጥ አጉልቶ የሚያሳየው። ባለፈው ዓመት ብቻ በዚህ ደዌ በዓለም ዙሪያ 3.5 ሚሊዮን ሕዝብ አልቋል። አምሥት ሚሊዮን ሕዝብም በ HIV ተለክፏል። ይህም ከ 1990 ሲነጻጸር አራት ዕጥፍ መሆኑ ነው። ሂደቱ የሚገታ ለመሆኑም በወቅቱ ጭብጥ ምልክት አይታይም።

እርግጥ ብራዚልን፣ ሤኔጋልን፣ ካምቦጃንና ታይላንድን የመሳሰሉ አገሮች ቁርጠኛ ዕርምጃ በመውሰድ የልክፍቱን መዛመት ሊያለዝቡት በቅተዋል። ዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋማት እንደሚሉት ይሁንና አርዓያውን ተከትለው የተራመዱት አገሮች በጣም ጥቂቶች ናቸው። ከነዚሁ መካከልም በተለይ በሕዝብ ብዛታቸው ግዙፍ የሆኑት ቻይና፣ ሕንድና ሩሢያ ይገኙበታል። የወባ በሽታን በተመለከተም ሁኔታው ተሥፋን የሚያዳብር ሆኖ አይገኝም። እዚህም በሽታውን ለመታገል የበለጠ ገንዘብ በሥራ ላይ መዋሉ ግድ ነው የሚሆነው።

እንዲህም ሆኖ ከሚሌኒየሙ ግቦች መድረስ እንዲቻል የዓለም ባንክና IMF አምሥት ነጥቦችን ያቀፈ ዕቅድ አቅርበዋል። ዕቅዱ ታዳጊ አገሮች ይበልጥ ወጣቶችን በትምሕርት ለማነጽና የጤና ጥበቃ አገልግሎታቸውን ለማሻሻል እንዲጥሩ የሚጠይቅ ነው። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታትም በበኩላቸው ዚያ ኩሬሺ እንደሚሉት ዕርድታቸውን በእጥፍ መጨመርና የእርሻ ምርት ገበዮቻቸውን ለደቡቡ ዓለም መክፈት ይጠበቅባቸዋል።

“የዘገባው ዓቢይ መልዕክት የጉዳዩ አስቸኳይነት ነው። ዓለምአቀፉ ሕብረተሰብ በተቻለ ፍጥነት ጭብጥ ዕርምጃዎችን ካልወሰደ ከሚሌኒየሙ ግብ መደረሱ ብርቱ አደጋ ላይ ነው የሚወድቀው።” በወቅቱ የሚታየው አዝማሚያ ያን ያህል የሚያበረታታ አይደለም።

የቻይናና የጃፓን የኤኮኖሚ ትስስር እጅግ የጠነከረ ሆኖ ቆይቷል። የጃፓን ኩባንያዎች በተለይ ባለፉት ዓመታት በቻይና ሥራ ላይ ያዋሉት ገንዘብ ከፍተኛ ነው። ሁለቱ አገሮች በንግዱ መስክም የጠበቀ ግንኙነት አላቸው። ሆኖም አሁን በጃፓን የወረራውን ዘመን ታሪክ የሚያቃልሉ የትምሕርት ቤት መጻሕፍት በመፈቀዳቸው በቻይና የተቀሰቀሰው ቁጣ የሁለቱን አገሮች የዲፕሎማሲ ግንኙነት ብቻ ሣይሆን የኤኮኖሚ ትስስሩንም አደጋ ላይ እየጣለው ነው።
በቻይና አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎች ከአንዴም ሁለቴ ሕዝብ የጃፓን ምርቶችን እንዳይገዛ ጥሪ አድርገዋል። መቶ ገደማ የሚጠጉ የጃፓን ኩባንያዎችንና ምርቶቻቸውን የእገዳ ዒላማ ያደረጉ ተባራሪ ወረቀቶች ሲበተኑ የተለያዩ የቻይና መደብሮችም የጃፓን ምርቶችን ለገብዪው ማቅረብ አቁመዋል። የቅስቀሳ ዘመቻው እሰከ ኢንተርኔቱ መረብ ድረስ ሲዘልቅ ተቃውሞው የሚቀጥል ነው የሚመስለው።

ዓመጹን የሚፈሩት በቻይና የሰፈሩ ታላላቅ የጃፓን ኩባንያዎች ሠራተኞቻቸው ቤታቸው እንዲቆዩና ወደ ጃፓን ምግብቤቶች ከመሄድ እንዲቆጠቡም ያሳስባሉ። የአውቶሞቢል ኢንዱስትሪው ሆንዳ ሙያተኞቹ ወደ ቻይና የሚያደርጉትን የሥራ ጉዞ በተቻለ መጠን ለመቀነስ ማቀዱን አስታውቋል። በርካታ የጃፓን ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ሻንግሃይ ውስጥ የሚካሄደው የዓመቱ ታላቅ የአውቶሞቢል ትዕይንትም ዓመጽ እንዳይጋርደው መፈራቱ አልቀረም። የወቅቱ ሁኔታ ይህን የመሰለ ነው።

የቻይናና የጃፓን የኤኮኖሚ ግንኙነት ሁለቱ አገሮች የዓመታት ጥላቻ ቢኖራቸውም ስኬታማ ሆኖ ነው የመጣው። ቻይና ካለፈው ዓመት ወዲህ ዋነኛዋ የጃፓን የንግድ ሸሪክ ስትሆን የሁለቱ አገሮች የንግድ ልውውጥ በዚያው ዓመት 211 ሚሊያርድ ዶላር የደረሰ ነበር። የጃፓን ባለሃብቶች ባለፉት ሁለት ዓመታት ቻይና ውስጥ አርባ ሚሊያርድ ዶላር በሥራ ላይ አውለዋል። የልማት ዕርዳታውም ሃያ ሚሊያርድ ዶላር ገደማ የተጠጋ ነበር።

ጃፓን እንግዲህ በዚህ መልክ እየተፋጠነ ለሚሄደው የቻይና የኤኮኖሚ ዕድገት ብርቱ አስተዋጽኦ አድርጋለች። በወቅቱ ሰላሣ ሺህ የጃፓን ኩባንያዎች በቻይና የሰፈሩ ሲሆን በርካሹ የሥራ ጉልበት ለማትረፍ አብዛኛውን ዕቃቸውን የሚያመርቱትም በዚያው ነው። ግን አሁን ከፖለቲካው ውዝግብ ባሻገር የአካባቢው የተፈጥሮ ጋዝና የነዳጅ ዘይት ሃብት ማከራከር በመያዙ የኤኮኖሚው ግንኙነት ጤናማ ሆኖ መቀጠሉ ሲበዛ ያጠያይቃል።