1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚሌኒየሙ ግቦች ዕጣ

ረቡዕ፣ መስከረም 16 2005

ዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ በዓለም ላይ ድህነትን በግማሽ መቀነሱን የሚጠቀልለው የሚሌኒየም ግብ በተጣለለት የጊዜ ገደብ በጎርጎሮሳውያኑ 2015 ዓመተ-ምሕረት መሳካቱን አደጋ ላይ እንዳይጥል የሚያሰጋ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/16Fit
ምስል DW

ዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ በዓለም ላይ ድህነትን በግማሽ መቀነሱን የሚጠቀልለው የሚሌኒየም ግብ በተጣለለት የጊዜ ገደብ በጎርጎሮሳውያኑ 2015 ዓመተ-ምሕረት መሳካቱን አደጋ ላይ እንዳይጥል የሚያሰጋ ሆኗል። ይህን ያመለከተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ 67ኛ ጠቅላይ ጉባዔው ዋዜማ በጉዳዩ ባቀረበው ዘገባ ነው። በዘገባው መሠረት ዓለምአቀፉ የልማት ዕርዳታ ባለፈው ዓመት ሶሥት ከመቶ ቀንሷል። ታዲያ የሚሌኒየሙ ግቦች የጊዜ ገደብ ሊያበቃ ሶሥት ዓመታት ብቻ ቀርተው ሳለ ሂደቱ በዕውነትም የሚያበረታታ አይደለም።

እርግጥ የተባበሩት መንግሥታት ዘገባ እንዳመለከተው ድህነትን በከፊል በመቀነሱ ረገድ አንዳንዶቹ ግቦች ከወዲሁ እንደሚታየው በ 2015 የሚደረስባቸው ናቸው። ለምሳሌ ያህል በጾታ እኩልነትና በመሠረታዊ ትምሕርት መዳረስ በኩል አሰደሳች ዕርምጃ መደረጉ ነው የተጠቀሰው። ይሁን እንጂ ዓለምአቀፉን የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ተከትሎ በገጠማቸው ችግር የተነሣ በርካታ ለጋሽ ሃገራት ባለፈው ዓመት ለአዳጊው ዓለም የሚያቀርቡትን የልማት ዕርዳታ ቀንሰዋል ወይም ዝቅ አድርገዋል። ከነዚሁ መካከልም ለምሳሌ ግሪክ፣ ስፓኝ፣ አውስትሪያና ቤልጂግ በምሳሌነት የሚጠቀሱት ጥቂቶቹ ናቸው።

ዓለምአቀፉ የልማት ዕርዳታ ባለፈው 2011 ዓመተ-ምሕረት ሶሥት ከመቶ ሲቀንስ የቀረበው ገንዘብ ለጋሽ መንግሥታት ገብተውት ከነበረው ቃል ሲነጻጸር በ 167 ሚሊያርድ ዶላር ዝቅ ያለ ነው። ይህም በአውሮፓ የተባበሩት መንግሥታት የመረጃ ማዕከል ባልደረባ አርነ ሞልፌንተር እንደሚያስረዱት ጨርሶ ጥሩ ዜና አይደለም።

« የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዘገባው የመጀመሪያውን ግልጽ ማስጠንቀቂያ ነው ያስተላለፈው። ይህ ደግሞ በፍጥነት ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል። ለማንኛውም ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ጊዜ አለ። በወቅቱ ሁኔታ ጠቃሚው ነገር ትርጉም ያለው ዕርምጃ አለመደረጉን መዝግቦ መያዙ ነው። በመሠረቱ ከ 2015 ግቦች ለመድረስ ብዙ የራቅን አይደለንም። ግን በተመሳሳይ ጊዜ የልማት ዕርዳታው ሶሥት በመቶ ማቆልቆሉን እናያለን። እናም ለብዙ አካባቢዎች ከሚሌኒየሙ ግቦች መድረሱ ከባድ ነው የሚሆነው»

Niebel in Ruanda
ምስል picture alliance / dpa

ከዋና ዋናዎቹ ለጋሽ ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው የጀርመን ፌደራላዊ የልማት ሚኒስትር መሥሪያ ቤት በበኩሉ የማቆልቆሉን ሂደት ለመግታት አጥብቆ እንደሚታገል አመልክቷል። ተቋሙ የመጪው 2013 ዓመተ-ምሕረት የዕርዳታ በጀቱ በ 670 ሚሊዮን ወደ 6,5 ሚሊያርድ ኤውሮ ከፍ እንደሚል ነው ያስታወቀው። ይህም ጀርመንን በዓለምአቀፉ የልማት ትብብር ከአሜሪካ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ታላቅ አገር ያደርጋታል ምንም እንኳ አውሮፓ በወቅቱ በከባድ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ተወጥራ ብትገኝም።

ሆኖም ጀርመን ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቷ አንጻር በምታቀርበው 0,4 ከመቶ የልማት ዕርዳታ በአውሮፓውያን ንጽጽር ግንባር ቀደም ሣትሆን በመካከለኛ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው። ተቀማጭነቱ በዚህ በቦን የሆነው « ቬልት-ሁንገር-ሂልፈ» በመባል የሚጠራ የዓለም የረሃብ ዕርዳታ ድርጅት ባልደረባ ሽቴፋን ክራይሸር እንደሚሉት ጀርመን የምታደርገው ከአቅሟ የሚመጣጠን አይደለም።

«ጀርመን ከኤኮኒሚ ጥንካሬዋ ሲነጻጸር የምታደርገው አስተዋጽኦ ጥቂት ነው። መንግሥት እርግጥ በየጊዜው የልማት ዕርዳታውን እስከ 2015 ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቱ አንጻር ወደ 0,7 በመቶ ከፍ ለማድረግ በያዘው ግቡ እንደሚጸና ያስረግጣል። ግን ከዚህ ግብ ላይ እንዴት እንደሚደረስ የምናየው ነገር የለም»

በወቅቱ ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርታቸው 0,7 በመቶ የሚሆነውን ድርጃ ለልማት ዕርዳታ የሚያውሉት የበለጸጉ ሃገራት ሶሥቱ የስካንዲኔቪያ ሃገራት ስዊድን፣ ኖርዌይና ዴንማርክ፤ እንዲሁም ሉክሰምቡርግና ኔዘርላንድ ብቻ ናቸው። በኤኮኖሚ ታላላቅ የሆኑት መንግሥታት አሜሪካ፣ ጃፓንና ሌሎችም በዚህ ተርታ ከፍ ብለው አልተሰለፉም። ይሁንና የተባበሩት መንግሥታት የአውሮፓ የመረጃ ማዕከል ባልደረባ አርነ ሞልፌንተር እንደሚያስረዱት ያለ አሜሪካና መሰሎቿ የሚሌኒየሙን ግቦች በተሟላ ሁኔታ ከግብ ማድረሱ አዳጋች ነገር ነው።

«ያለ ታላላቆቹ ተጫዋቾች ያለ ጃፓንንና አሜሪካ ወዘተ የሚሌኒየሙን ግቦች በሙሉ ልናሟላ አንችልም»

Entwicklungshilfe der EU
ምስል picture-alliance/dpa

የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒም ዕቅድ ገቢር በማድረጉ ረገድ ትናንሽ ዕርምጃዎች ሲደረጉ ብዙዎቹን ታዳጊ ሃገራት ገና ከባድ ፈተና ነው የሚጠብቃቸው። የተባበሩት መንግሥታት ዘገባ የንጹህ ውሃ አቅርቦትንና የሴት ልጆችን የመሠረተ ትምሕርት ተሳትፎ በተመለከተ ከግቦቹ ላይ መደረሱን አመልክቷል።

የድርጅቱ ዓባል መንግሥታት በዓለም ላይ ያለውን ድህነት በግማሽ ለመቀነስ በጎርጎሮሳውያኑ 2000 ዓ,ም በጤና ጥበቃ፣ በትምሕርት፣ በውሃ አቅርቦት፣ በሴቶች የጾታ እኩልነትና በዘላቂ ልማት መስኮች ስምንት ግቦችን ይዘው መነሳታቸው የሚታወስ ነው። ዛሬ መድሃኒቶችንና ክትባቶችን በማግኘት በኩል ግልጽ መሻሻል መታየቱን ነው የድርጅቱ ዘገባ ያመለከተው። ሆኖም መድሃኒቶች በታዳጊው ዓለም ከሕዝቡ የገቢ አቅም ሲነጻጸር ከዓለምአቀፉ አማካይ በአምሥት ዕጅ ውድ ሆነው ነው የሚገኙት። ግን እንደ ሽቴፋን ክራይሸር ገንዘብ ብቻ አይደለም ወሣኙ ነገር።

«ረሃብን በመታገሉ ረገድ ወሣኙ ነገር ለዓለም የረሃብ ዕርዳታ ድርጅት ገንዘብ ብቻ አይደለም። ከሚሌኒየሙ ግብ መድረሱ እንዲያው ዕርዳታው ሳይቆረጥም የሚሆን አይመስልም»

ለዚህም ምክንያቱ አዘውትሮ የሚታየው የዕርምጃ አለመጣጣም ነው። ክራይሸር ለዚህ የአውሮፓ ሕብረትን የዕርሻ ድጎማ ይጠቅሳሉ።

«ብዙ ትርፍ ምርት እንዲመረት ይደረጋል። ይህም ምርቱ ወደ ድሆች አገሮች በሚላክበት ጊዜ በዚያ የዕርሻ ልማትን አቅም የሚያሳጣና የሚቀብር ነው የሚሆነው። ከአውሮፓ ለምሳሌ ወደ አፍሪቃ የሚሄዱት ምርቶች ከአገሪው የእርሻ ውጤቶች ርካሽ ናቸው። ይህ ደግሞ የገበሬውን የኑሮ መሠረት የሚያፈርስ ነው»

የጀርመን መንግሥት በበኩሉ በአውሮፓ ደረጃ የእርሻ ድጎማውን ለማስወገድ እንደሚሻ ነው የፌደራሉ የልማት ትብብር መሥሪያ ቤት ባለሥልጣናት የሚናገሩት። ለዚሁም ምክንያቱ ድጎማው በአበሮቹ ሃገራት ውስጥ የዕርሻ ልማትን ይጎዳል የሚል ነው። ይህ ጥያቄ ፌደራሉ መሥሪያ ቤት ለገጠር ልማት ያወጣው አሥር ነጥቦችን ያቀፈ ዕቅድ አካልም ነው። የሆነው ሆኖ በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ የሚደረገው የዕርሻ ምርት ድጎማ ባለበት እስከቀጠለ ድረስ ርሻሽ ምርቶችን ወደ አፍሪቃ መላኩ የሚቀጥል ነገር ይሆናል።

«በአውሮፓ ለእርሻ ልማቱ ዘርፍ ድጎማ ይደረጋል። የሚመረተውም ከመጠን በላይ ነው። ይህ ምርት ደግሞ ርካሽ በመሆኑ በድሆች ሃገራት ከተራገፈ ገበሬውን የፉክክር አቅም ያሳጣዋል። የአውሮፓ ምርቶች በአንድ የአፍሪቃ አገር ገበያ ላይ በሚቀርቡበት ጊዜ አገር ካፈራቸው ዕጅግ የረከሱ ሆነው ነው የሚገኙት። እናም በዚያ የሚኖሩትን አምራቾች የኑሮ መሠረት ያፈርሣሉ ማለት ነው»

ይህ እንዳይሆን ለጋሽ መንግሥታት የፖሊሲ ለውጥ ማድረጋቸው እጅግ አስፈላጊ ነው። ሽቴፋን ክራይሸር እንደሚያሳስቡት፤

«ፌደራላዊው የጀርመን መንግሥትና ሌሎች በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ ሃገራት አጠቃላይ ፖሊሲያቸውን መልሰው እንዲያጤኑ መጠየቅ አለባቸው። በዚህ የተነሣ የልማት ውጥኖች፣ የሰብዓዊ መብት ከበሬታና የሚሌኒየሙ ግቦች አደጋ ላይ ሊወድቁ አይገባም»

Entwicklungshilfe Afrika
ምስል picture-alliance/ZB

እንግዲህ ችግሩ የገንዘብ ብቻ አይደለም። እርግጥ ለጋሽ ሃገራቱ የገቡትን የፊናንስ ዕርዳታ ቃል ማክበራቸው አስፈላጊ ነው። ከዚህ ባሻገርም ፍትሃዊ የንግድ ስርዓትን ማስፈን ያስፈልጋል የተባበሩት መንግሥታት የአውሮፓ የመረጃ ማዕከል ባልደረባ አርነ ሞልፌንተር እንደሚሉት። ታዳጊዎቹ ሃገራት ከዚሁ ሌላ ወደ በለጸጉት ሃገራት ገበዮች የመዝለቅ ፍትሃዊ ሁኔታና ቀጣይ የዕዳ ምሕረትም ያስፈልጋቸዋል።

እነዚህ ሶሥት ጠቃሚ ነጥቦች ከሚሌኒየሙ ግቦች ለመድረስ እንደሚያስችሉ የሞልፌንተር ዕምነት ነው። በወቅቱ ጠርሙሱ በግማሽ ሞልቷል። እናም እንዲሞላ የቀረውን የበለጸጉት መንግሥታት ማከል ይጠበቅባቸል። አለበለዚያ አዳጊዎቹ ሃገራት የልማት ጥማቸውን ሊያረኩ አይችሉም።

በሌላ በኩል የበለጸጉት መንግሥታት ይፋ የልማት ዕርዳታ ለታዳጊ ሃገራት ዕርምጃ በጅቷል አልበጀም ባለፉት ዓመታት እያከራከረ የመጣ ጉዳይ ነው። የበለጸጉት መንግሥታት ባለፉት አምሥት አሠርተ-ዓመታት በዝቅተኛ የልማት ደረጃ ላይ ለሚገኙት ለድሆች ሃገራት ከ 4,6 ትሪሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ሲያቀርቡ ገንዘቡ የሚገባውን ልማት ማስከተሉ ብዙም ጎልቶ አይታይም። በአንጻሩ በአምባገነን ገዢዎችና በሙስና በተዘፈቁ አበሮቻቸው ሲመዘበር ነው የኖረው።

ስለዚህም አፍሪቃውያን ራሳቸው ሳይቀር የልማት ዕርዳታው ቀርቶ ሕዝብ ከተመጽዋችነትና ከባዕድ ገንዘብ ለመላቀቅ እንዲታገል ጥሪ ማድረግ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ልማት በምጽዋት የሚሆን ነገር አይደለም። ታዲያ በተለይም ከሣሃራ በስተደቡብ አፍሪቃ የሚሌኒየሙን ግቦች ለማሟላት ጉዞው ረጅም የሚሆን ነው የሚመስለው።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ