1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚጥል በሽታ (ኢፕሊፕሲ)

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 9 2011

በበርካታ ሚሊየኖች የሚገመቱ ሰዎችን የሚያስቸግር የማይጋባ ህመም መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፤ ኢፕሊፕሲ ወይም በዘልማድ የሚጥል በሽታ በሚል የሚታወቀውን የጤና እክል። ታማሚዎቹ የሃኪሞች ያላሰለሰ ምክር እንደሚያስፈልጋቸውም ይመክራሉ። ኢፕሊፕሲ ህክምና ሊረዳው የሚችለው የጤና እክል ነው ወይስ የርኩስ መንፈስ ሥራ? ሃኪሞች ምን ይላሉ?

https://p.dw.com/p/3MAYI
Wellcome Image Awards Brain-on-a-chip
ምስል Collin Edington and Iris Lee/Koch Institute at MIT

«ብዙዎች በህክምና የሚረዳ አይመስላቸውም»

የሚጥል በሽታ በመባል በዘልማድ የሚታወቀው ኢፕሊፕሲ አንጎልን የሚጎዳ የማይጋባ በሽታ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት (WHO ) መረጃ ያመለክታል። (WHO) በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎችን ሊጎዳ እንደሚችል የገለፀው ይህ የጤና ችግር በመላው ዓለም 50 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎችን እንደሚያሰቃይም ጠቅሷል። ከዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ፋኩልቲ የተሠራ አንድ ጥናት ደግሞ ከ360 እስከ 400 ሺህ የሚደርሱ የኢፕሊፕሲ ታማሚዎች መኖራቸውን ያመለክታል። የሥርዓተ ነርቭ ችግር በሆነው ኢፕሊፕሲ ወይም በልማድ የሚጥል በሽታ በሚባለው ከሚቸገሩት መካከልም 70 በመቶው በአግባቡ ምርመራ ተደርጎላቸው ሕክምናውን ቢያገኙ በዚህ የጤና እክል ምክንያት የሚያጋጥነው ማንቀጥቀጥ ሊወገድላቸው እንደሚችልም ይገልጻል። ኢትዮጵያ ውስጥ የተደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው ግን ከተጠቀሰው የኢፕሊፕሲ ታማሚዎች 1,6 በመቶው ብቻ ናቸው ተገቢውን ዘመናዊ ህክምና ማግኘት የቻሉት። አብዛኞቹ በሀገር ባህል መድኃኒት፣ እና በክታቦች አንዳንዶቹም በጸበል ችግሩን ለመቆጣጠር እንደሚሞክሩ ነው ያሳየው።

የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ የሚያመለክተው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሃገራት የሚኖሩ ከተጠቀሰው የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር ¾ኛው የሚያስፈልጋቸውን ህክምና ማግኘት እንደማይችሉም ነው ። ከምንም በላይ ደግሞ በአብዛኛው የዓለም ክፍል የዚህ በሽታ ተጠቂዎች እና ቤተሰቦቻቸው በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ የመገለል እና የአድሎ ሰለባዎች መሆናቸውንም መረጃው ያመለክታል።

ብዙውን ጊዜ ሰዎች ስለበሽታው ምንነት እና ትክክለኛ መንስኤ አለማወቃቸው ከታማሚዎች ጋር የሚኖራቸውን አቀራረብ እና አግባብ ሲጎዳ ይስተዋላል። ታማሚው በጤናው መታወክ የሚገጥመው ስነልቡናዊ ጉዳት እንዳይበቃው ከሰዎች የሚገጥመው መገለል ተጨማሪ ማኅበራዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው መረዳት ይቻላል። የዚህ መነሻ ደግሞ ሰዎች ስለዚህ በሽታ ያላቸው ግንዛቤ ውሱን መሆኑ እንደሚሆን አያነጋግርም።

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የግል ተሞክሯቸውን ያካፈሉ ኤዛና የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ ለኢፕሊፕሲ የሚጥል በሽታ የሚለውን ዘልማዳዊ አገላለፅ፤ በቅንፍ የለም የማይጥል የኢፕሊፕሲ አይነት መኖሩን በማመልከት፤ ብዙዎች መፍትሄ እንደሌለው ቢያዩትም እሳቸው ግን በቤተሰባቸው ጥረት ህክምና ማግኘት መቻላቸውን ጽፈዋል። ከ14 ዓመታቸው ጀምረው ህክምናውን ማግኘት በመቻላቸውም ዛሬ ከሚገኙበት የትምህርት ደረጃ መድረስ እንደቻሉ እና በሽታው ተገቢውን የህክምና ርዳታ ካገኙ ሰዎችን በሕይወት ከሚታሰብ ስኬት ሊያግድ እንደማይችልም ምክራቸውን ይለግሳሉ። ዋናው ነጥባቸው ደግሞ ጉዳዩ ከነርቭ ጋር የተገናኘ የጤና ችግር እንጂ ልክፍት አይደለም የሚል ነው።

Logo Weltgesundheitsorganisation WHO
ምስል Getty Images/AFP/E. Jones

እኛም በዚህ መሰናዶ ስለበሽታው ምንነት እንዲያብራሩልን በህክምናም ሊረዳ እንደሚችልም ለወገኖቻችን እንዲያስረዱልን የነርቭ ከፍተኛ ሃኪም የሆኑትን ዶክተር ተሻገር ደመቀን እንግዳችን አደረግን። የነርቭ ሃኪሙ ይህ በሽታ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት እንደሚችል ነው የሚያስረዱት።

«አንደኛው አንጎላችን ክፍል ላይ በተለይ ደግሞ ኮርቴክስ የሚሉት ቦታ ላይ ችግር ከተነሳ፤ ለምሳሌ የደም መዘዋወር እዚያ ላይ ከቆመ፣ ወይም ደግሞ ባልታወቀ ምክንያት ተጎድቶ ጠባሳ ካለበት፣ ወይም ደግሞ ኢንፌክሽን የተጎዳ ከሆነ፣ ወይም እዚያው አንጎል ውስጥ የሚፈጠሩ እጢዎች ወይም ደግሞ ከሌላ የሰውነት ክፍላችን ወደዚያ ተዘዋውረው እዚያ ሊበቅሉ የሚችሉ እጢዎች የሚጥል በሽታ ሊያስነሱ ይችላሉ።»

ይህም ብቻ አይደለም አንዳንዴም ታማሚው በሚደረጉለት የተለያዩ ምርመራዎች ምንም ምልክት ካልተገኘ በዘር ሊመጣ እንደሚችል እንደሚገመትም ጠቁመዋል። ያ ማለት ግን ይላሉ ዶክተር ተሻገር።

«ያ ማለት ግን አባትየው የሚጥል በሽታ ካለው ልጁም አውቶማቲካሊ ይይዘዋል ማለት አይደለም።»

ኢትሊፕሲ ወይም በልማት የሚጥል በሽታ የሚባለው የጤና ችግር ከሥርዓተ ነርቭ እና ከአንጎል ጋር የሚገናኝ፤ ተፅዕኖው ደግሞ ለመላ አካል የሚተርፍ እንደሆነ ነው ዶክተር ተሻገር የገለፁት።

ነርቮች በሰውነታችን ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያላቸው እንደሚሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች መታወካቸውም እንዲህ ያለውን የጤና እክል ሊያስከትል ይችላል። የነርቭ ሀኪሙ ቀጠሉ፤

Menschliche Nervenzellen
ምስል imago/Science Photo Library

«አንደኛው የአንጎላችን ክፍል ያው የነርቭ ሴሎች ያሉበት ነው። እንግዲህ የተለያየ የአንጎላችን ክፍሎች ውስጥ ቦታ ይዘው የራሳቸውን ሥራቸውን ይሠራሉ። ለመንቀሳቀስ፣ ለመተንፈስ፣ እንደገናም ለመብላት፣ ለማኘክ፣ ለመናገር ያ ያ ሁሉ ሥራዎች በአንጎላችን ባሉ ነርቮች ተስተካክሎ የሚመጣ ነው። አሁን እነሱ በተለያየ ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው ይሄ አይነት ምክንያት ሊመጣ ይችላል።»

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን የጤና ችግር አስመልክቶ የተሠራው ጥናትም ሆነ፤ የግል ተሞክሯቸውን በፌስ ቡክ ያጋሩት ኤዛና እንደጠቆሙት ሰዎች ኤፕሊፕሲን ወይም በልማድ የሚጥል በሽታ የምንለውን ከርኩስ መንፈስ ጋር ያገናኙታል። እናም ከዘመናዊ ህክምና ይልቅ ሌላ መፍትሄ ለማፈላለግ ይደክማሉ። የነርቭ ከፍተኛ ሃኪሙ ግን እንዲህ ነው የሚሉት።

«ብዙውን ጊዜ በኅብረተሰቡ ፣ የሚጥል በሽታ የያዘውም ሰውም ሆነ፣ ዘመዶቹ፣ አካባቢው እንደሌላ ሊገልፀው ይችላል። ይክ የተከሰተው ምናልባት አጋንንንት ይዞት ነው፣ ወይም ደግሞ እዚህ ቦታ ተዳርጎ ስለነበረ ይሆናል የሚል መግለጫ ይሰጣሉ። ግን ይህ በሽታ ምንም ከአጋንንት ወይም ከሰይጣን ወይም ከመሳሰሉት ሁኔታ የሚከሰት አይደለም።  ይሄ የአንጎላችን ሥራው ሲታወክ የሚመጣ ነገር ነው።»

ስለበሽታው ምንነት አውርተን መፍትሄውን መሻታችን አይቀርም፤ ሳምንት እንመለስበታለን። እናንተም ያላችሁን ጥያቄ እና አስተያየት ልትልኩልን ትችላላችሁ። የነርቭ ከፍተኛ ባለሙያውን ዶክተር ተሻገር ደመቀን እናመሰግናለን።  

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ