1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሊ ሕዝብ እና የምርጫ ሂደት

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2006

የማሊ ሕዝብ ባለፈው እሁድ ሁለተኛውን ዙር ምክር ቤታዊ ምርጫ አካሂዷል። የሀገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ አሁንም አሳሳቢ የሆነበት ድርጊት በምርጫው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉ አልቀረም። እንደታየው፣ ሕዝቡ በምርጫ ለመሳተፍ ፍላጎት ያለው አይመስልም። ከማሊ በተገኙ ዘገባዎች መሠረት፣ ድምፁን ለመስጠት የወጣው መራጭ ሕዝብ ቁጥር በጣም ዝቅተኛ ነበር።

https://p.dw.com/p/1AbCj
Mali Parlamentswahlen 15.12.2013
ምስል Habibou Kouyate/AFP/Getty Images

የማሊ ሕዝብ በ2013 ዓም ብቻ አራት ጊዜ ምርጫ አካሂዷል። የመጀመሪያው ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በማሊ የጦር ኃይሉ መፈንቅለ መንግሥት ካካሄደ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ባለፈው ሐምሌ መጨረሻ፣ ሁለተኛው ዙር ደግሞ ከሁለት ሳምንታ በኋላ በነሐሴ ወር ተካሂዶ ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ አሸንፈዋል። ባለፈው ኅዳር መጨረሻ ደግሞ በተካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫ ላይ አንድም ፓርቲ ወይም ጥምረት የብዙኃኑን መራጭ ድምፅ ሳያገኝ ቀርቶዋል። በዚህም የተነሳ መራጩ ሕዝብ እንደገና ድምፁን ሰጥቷል።

Mali Parlamentswahlen 15.12.2013
ምስል Habibou Kouyate/AFP/Getty Images

ለ127 የምክር ቤት መቀመጫዎች የተካሄደው ምርጫ ውጤት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል። በማሊ መዲና ባማኮ የሚገኘው የነፃው የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ተቋም ኃላፊ ባድየ ሂማ እንዳስታወቁት፣ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ ነው የተጠናቀቀው።

«በማሊ ሁለተኛው ዙር ምክር ቤታዊ ምርጫ በጣም በተስተካከለ ጥሩ መንገድ ተካሂዷል ለማለት ይቻላል።»

በምርጫው የተሳተፈው ሰው ቁጥር በይፋ ባይታወቅም፣ ዝቅተኛ እንደነበር ነው የአውሮጳ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ልዊ ሚሼል ባማኮ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ያስታወቁት።

«የአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎችን ተሳትፎ ብቻ ነው የማውቀው። በነዚህ ጣቢያዎች የመራጩ ተሳትፎ በ 25 እና በ 28 ከመቶ መካከል ነበር። ይህ በማሊ የተለመደ ነው። የመራጭ ተሳትፎ ከፍተኛ ሆኖ አያውቅም።»

በመጀመሪያው ዙር ምክር ቤታዊ ምርጫ ላይ ድምፁን የሰጠው ሕዝብ ቁጥር 38,6 ከመቶ ብቻ ነበር። ለዚሁ ዝቅተኛ ተሳትፎ ምክንያቱ ምናልባት ያልተረጋጋው የሀገሪቱ ፀጥታ እና ሕዝቡ በኑሮው ላይ አንዳችም መሻሻል ያላየበት ሁኔታ ሊሆን እንደሚችል በባማኮ የሚገኘው የጀርመናውያኑ የጥናት ድርጅት «ኮንራድ አድናወር ተቋም» ተጠሪ ፋጡማ ሲ ጌይ ይገምታሉ። ምክንያቱም ከምክር ቤታዊው ምርጫ አንድ ቀን አሰቀድሞ ወጊያ በሚካሄድባት በሰሜን ማሊ የኪዳል ከተማ አንድ አጥፍቶ ጠፊ ራሱን በቦምብ ባነጎደበት ጥቃት ሁለት የሴኔጋል ሰላም አሰከባሪ ጓድ ወታደሮች ተገድለዋል። በፕሬዚደንታዊው ምርጫ ላይ ግን ከየሁለቱ መራጭ ሕዝብ አንዱ ድምፁን ሰጥቶዋል። ።

Bildergalerie Mali
ምስል DW/S. Blanchard

«በሰሜኑ ብዙ መራጭ ራሱን አደጋ ላይ ላለመጣል ሲል ከቤቱ እንደማይወጣ የተጠበቀ ነበር። በፕሬዚደንታዊው ምርጫ ላይ ግን ሕዝቡ አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር ቆርጦ በመነሳቱ ተሳትፎዉ ከፍተኛ ነበር።»

ማሊ የጦር ኃይሉ መጋቢት 2012 ዓም መፈንቅለ መንግሥት ካካሄደ በኋላ ነበር ቀውስ ውስጥ የገባችው። ይህን ተከትሎ አክራሪ ሙሥሊሞች እና የቱዋሬግ ዓማፅያን በሰሜኑ የሀገሪቱ አካባቢ የጀመሩት ውጊያ ሊያበቃ የቻለውም በፈረንሳይ የጦር ጣልቃ ገብነት ነበር። ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ የማሊ ፐሬዚደንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ከቱዋሬጎች ጋ ዕርቀ ሰላም የማውረዱን ጥረት ቀዳሚው ተግባራቸው እንደሚያደርጉ አስታውቀው ነበር፤ ግን ይህ ለጊዜዉ የሚደረስበት አይመስልም፣ እንደሚታወሰው ለአዛዋድ ነፃነት የሚታገለው በምሕፃሩ ኤም ኤን ኤል ኤ የሚባለው የቱዋሬግ ዓማፅያን ቡድን ከማሊ መንግሥት ጋ ደርሶት የነበረው የተኩስስ አቁም ውል ባለፈው ኅዳር ወር አብቅቶዋል።

የማሊን ፖለቲካ በቅርብ እንደሚከታተሉት የኮንራድ አድናወር ተቋም ባልደረባ ፋጡማ ሲ ጌይ አስተያየት፣ የሀገሪቱ መንግሥት ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ የሰጠውን ዓይነት ትኩረት ለምክር ቤታዊው ምርጫ አለመስጠቱ ሕዝቡ ምርጫው የያዘውን ከፍተኛ ትርጓሜ በሚገባ እንዳይረዳው አድርጓል።

ያም ቢሆን ግን የምርጫው መደረግ በሀገሪቱ ሥርዓት እየተመለሰ መሆኑን ለሕዝቡ የሚጠቁም ዋነኛ ሂደት ነው ያሉት ሲ ጌይ ምርጫው ባይደረግ ኖሮ የሀገሪቱ ሁኔታ ይበልጡን ይበላሽ ነበር ብለዋል።

ሀይከ ፊሸር/አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

 

 

 

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ