1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሊ ምርጫ ዝግጅት

ዓርብ፣ ግንቦት 30 2005

የማሊ መገናኛ ብዙሃን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ስለ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ እንቅስቃሴ ተከታታይ ዘገባዎች ሲያቀርቡ ቆይተዋል ። በዋና ከተማይቱ ባማኮ ጎዳናዎች ግን ምርጫው የመነጋገሪያ ርዕስ አይደለም ። ከዚያ ይልቅ ብዙዎች የሃገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ ብሔራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማስቻሉን ይጠይቃሉ ።

https://p.dw.com/p/18lcU
ምስል DW/K. Gänsler


የፊታችን ሐምሌ 21 2005 ዓም በማሊ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል ። ሆኖም ምርጫው በተቃረበበት በአሁኑ ጊዜ ህዝቡ ስለ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች መርሃ ግብሮችም ሆነ ስለ እጩ ተወዳዳሪዎች ብዙም ሲነጋገር አይሰማም ። ከዚያ ይልቅ ብዙዎች አሁን የሚያወጡ የሚያወርዱት ምርጫው በታሰበው ጊዜ ይካሄዳል አይካሄድም የሚለውን ጥያቄ ነው ። የማሊ ጊዜያዊ መንግሥት በዚህ ሳምንትም የአስቸኳይ ጊዜ ህጉን አራዝሟል ። ከዚህ በኋላ የምርጫ ዘመቻው ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሎ ይታመናል ።
ሮክያ ድያራ ካራምቤ የሴቶች መብት ተሟጋችና የማሊ ስደተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ፕሬዝዳንትም ናት ። ማሊ ውስጥ ምርጫ እስከሚካሄድ 6 ሳምንታት ይቀራሉ ። ካራምቤ ግን እንደተባለው ሐምሌ 21 2005 ዓም ምርጫ ይካሄዳል ብለው አይጠብቁም ።
« መንግሥት በሐምሌ ምርጫውን ማካሄድ ይቻላል ይላል ። ሆኖም ብዙ ዜጎች ና የሲቪክ ማህበራት ይህ ፍፁም ሊሆን እንደማይችል ነው የሚናገሩት ። ለምንድን ነው በደንብ እንድንዘጋጅ 4 ተጨማሪ ወራት የማይሰጠን ። ? »

Wahlen in Mali
ፕሬዝዳንት ዲዮኑኩንዳ ትራኦሬምስል DW/K. Gänsler


ይህ የብዙዎች አስተሳሰብ ነው ። ባለፉት ሳምንታት ብዙ ፓርቲዎች ዋና ዋና እጩ ተወዳዳሪዎችን ሰይመዋል ። የ46 ዓመቱ ድራማኔ ደምብሌ ጥሩ ተስፋ ካላቸው እጩዎች ውስጥ አንዱ ናቸው ። ደምብሌ በአሁኑ ምርጫ መወዳደር የማይችሉት የጊዜያዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት ዲዮኑኩንዳ ትራኦሬ ምልምል ና አዴማ PASJ የማሊ ዲሞክራሲያዊ ህብረት የተባለው ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ ናቸው ። የማሊ መገናኛ ብዙሃን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ስለ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ እንቅስቃሴ ተከታታይ ዘገባዎች ሲያቀርቡ ቆይተዋል ። በዋና ከተማይቱ ባማኮ ጎዳናዎች ግን ምርጫው የመነጋገሪያ ርዕስ አይደለም ። ከዚያ ይልቅ ብዙዎች የሃገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ ብሔራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማስቻሉን ይጠይቃሉ ። የማሊ ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ኢሳጋ ካምፖ የህዝቡን ስጋት ያውቃሉ ።
« እርግጥ ነው በባማኮም ቢሆን መቶ በመቶ ፀጥታ የለም ። ከቀውስ የወጣንበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው ።

ሁኔታው በ 2010 በ 2011 ም ይሁን በ 2012 መጀመሪያ ፍፁም የተለያየ ነበር ። ሰሜናዊው የሃገራችን ክፍል በ አሸባሪዎች ተይዞ ነበር ። እግዚአብሔር ይመስገን አሁን የሉም ። ደረጃ በደረጃ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ከማሊ ጋር በመሆን ምርጫው እንዲካሄድ ፀጥታ ማስፈን ይፈልጋል ። »

Wahlen in Mali
ቼካ አብዱ ቱሪምስል DW/K. Gänsler


ተጨማሪ ችግር ሆኖ የሚገኘው በኪዳል ያለው ሁኔታ ነው ። ከተማይቱ አሁንም በቱዋሬግ አማፅያን እንደተያዘች ነው ። ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ የማሊ ወታደሮች ኪዳል ዘምተዋል ከማክሰኞ አንስቶ ከቱዋሬጎች ጋር ከባድ ውጊያ ላይ ናቸው ። ለዚህ ቀውስ መፍትሄ መፈለግ ያሻል ። የአውሮፓ ህብረት ሐምሌ 21 2005 በኪዳሊም ምርጫ እንዲካሄድ ይፈልጋል ።ይህ እንዲዳካ ግን ሁኔታዎች አስተማማኝ መሆን አለባቸው ።ቼካ አብዱ ቱሪ የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማህበረሰብ በምህፃሩ ኤኮዋስ ተጠሪ ግን ወታደሮች በብዛት ከተሰማሩ የታሰበውን ማከናወን እንደሚቻል ያምናሉ ።
«ፀጥታ ለማስከበር ብዙ ሰርተናል ። ማሊ ውስጥ 6337 የአፍሪቃ ወታደሮች ይገኛሉ ። ዝነዚህን ወታደሮች ወደ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ማዛወሩን ማፅደቁ አለ ። ሰኔ 24 2005 12 600 ሰላም አስከባሪዎች ሰሜን ማሊ ስለሚሰፍሩ ህዝቡ ደህንነት ይሰማዋል »

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ መርጃ ድርጅት በምህፃሩ UNHCR እንደሚለው በጦርነቱ ምክንያት 475 ሺህ ሰዎች ከሰሜን ማሊ ተሰደዋል ። ብዙዎች ወደ ደቡብ ማሊ የሸሹ ቢሆንም 174 ሺሁ በጎረቤት አገሮች ውስጥ ነው ያሉት ። ስደተኞቹም በያሉበት እንዲመርጡ ነው የታሰበው ። በሚገኙበት ቦታ የምርጫ ዘመቻ ላይካሄድ ይችላል ።

Malische Binnenflüchtlinge
የማሊ ስደተኞችምስል DW/K. Gänsler

ጋዜጣ ኢንተርኔትም ሆነ ቴሌቪዥን ስለሌለ ስለ እጩ ተወዳዳሪዎች መረጃ ማግኘት አይቻልም ። ኤኮዋስ የአውሮፓ ህብረት ወይም ፈረንሳይን የመሳሰሉት የውጭ ኃይሎች ምርጫው በተያዘለት ቀን እንዲካሄድ የሚያደርጉት ከፍተኛ ግፊት በርካታ ማሊዎችን አበሳጭቷል ። ሃገራቸው ማሊ ግን የእርዳታ አቅራቢ መንግሥታት ቅምጥል ናት ። የሃገሪቱ ገቢ ይበልጡን ከውጭ በሚገኝ እርዳታ ላይ ጥገኛ ነው ። ከመንግስት በጀት 1/4 ተኛው በውጭ እርዳታ ነው የሚሸፈነው ። የምርጫ ኮሚሽኑ ሃላፊ እንደሚሉት ይህ ሁሉ እንደቀድሞው እንዲቀጥል በማሊ ህጋዊና ቋሚ መንግሥት መቋቋም አለበት ።

ካትሪን ጌንስለር

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ