1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ የካቲት 10 2009

የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ኅልፈተ-ዜና፤ እንዲሁም የአትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ቤተሰቦች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አቅንተው ከአትሌቱ ጋር መገናኘታቸው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሰፊ ሽፋን አግኝቷል። ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው የተነገረው ሐሙስ የካቲት 9 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. ነበር።

https://p.dw.com/p/2XjKW
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

ኢትዮጵያ በጣሊያን በተወረረችበት ወቅት በነበረው ትግል ታላቅ አስተዋጽዖ ያበረከቱ የቁርጥ ቀን ልጅ ናቸው፤ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት። በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው የተነገረው ትናት ነበር።

ካለፉት ስድስት ወራት አንስቶ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በስደት የሚኖረው አትሌት ፈይሳ ሊሌሳ ከቤተሰቦቹ ጋር መገናኘቱም ሌላኛው መነጋገሪያ ነበር። አትሌት ፈይሳ በስደት መኖር የጀመረው በሪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ሩጫ ውድድር ወቅት ሁለት እጆቹን ከፍ አድርጎ በማነባበር መንግሥት ላይ ተቃውሞ ማሳየቱን ተከትሎ ነው። አትሌት ፈይ ሳ ሌሊሳ ከባለቤቱ እና ከሁለት ልጆቹ  ጋር ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ መገናኘት ችሏል። 

እዉቁ የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪና ጸሐፊ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ማረፋቸው የተሰማው ሐሙስ የካቲት 9 ቀን 2009 ዓም ነበር። ድንገት የተሰማው ዜና ረፍት ብዙዎችን አስደንግጧል። ትዊተር እና ፌስቡክ ተጠቃሚዎችም በቅጽበት ነበር ዜናውን በስፋት ያሰራጩት። 

Hauptcampus der Universität Addis Abeba AAU
ምስል DW

በርካቶች ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በሕይወት ዘመናቸው ለኢትዮጵያ ያበረከቱትን አስተዋጽዖ አወድሰዋል። «የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ባለውለታ»፤ «በኢትዮጵያ በልዩ ዐይን የሚታዩ ስመጥር»፤ «ኢትዮጵያን ደከመኝ ሳትል አገልግለኻታልና እናመሠግንሃለን»፤ እንዲሁም «ነፍስህን በገነት ያኑራት» የሚሉት በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። 

በኢትዮጵያ ጥናት ስማቸው በገናናነት ከሚነሱ ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ የኾኑት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ከብሪታንያ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በፊት ነበር። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1956 አንስቶ ነዋሪነታቸው በኢትዮጵያ ነበር። እስካለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት ማለትም መራመድ እስኪሳናቸው ድረስም ከኢትዮጵያ ጥናት አለመለየታቸውም ይነገራል። በተለይ ለተቋሙ መዳበር የፕሮፌሰር ሪቻርድ አስተዋጽኦ ላቅ ያለ መኾኑን የተቋሙ ኃላፊ የነበሩት ዶክተር ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ እንዲህ ይዘክራሉ።

ፕሮፌሰር ሪቻርድ የአክሱም ሐውልትን ከጣሊያን ወደ ኢትዮጵያ በማስመጣቱ ሒደት ላበረከቱት አስተዋጽዖም የማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ምሥጋና አድርሰዋቸዋል። በእርግጥ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1999 ዓመት አዲስ አበባ ውስጥ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የመቅደላ ቅርሶች አስመላሽ ማኅበር (AFROMET) በሚባለው የብሪታንያ ቤተ-መዘክር የሚገኙ በመቅደላ ጦርነት ወቅት የተወረሱ ቅርሶችን ለማስመለስ ያደረጉት ከፍተኛ ጥረት ግን አልተሳካም።  

ኾኖም የዳግማዊ ምንሊክ ዳዊት እንዲሁም የዓጼ ቴዎድሮስ ጋሻ በሒደት ተመልሰዋል። ይኽም የኾነው የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ጥረትን እና ትግልን የተገነዘቡ ሰዎች ባደረጓቸው ጥቆማዎች እንደነበር  ዶክተር ኤልሳቤጥ አክለው ተናግረዋል። ኢትዮጵያን ወዳዱ ፕሮፌሰር ለኢትዮጵያ ጥናት ጥለው ያለፉት  በርካታ አስተዋጽዖ እንደነበረም ጠቅሰዋል። 

19ኛው የኢትዮጵያ ጥናት ጉባኤ ተሳታፊዎች በዋርሶው ፖላንድ
19ኛው የኢትዮጵያ ጥናት ጉባኤ ተሳታፊዎች በዋርሶው ፖላንድምስል Dr. Andreas Wetter

የኢትዮጵያ  ታሪክ ሲነሳ መቼም ሊዘነጉ ከማይገባቸው ጥቂት ብርቅ ሰዎች መካከል ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት አንዱ ናቸው። የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ኅልፈተ-ዜና ትናንት በተሰማበት ቅጽበት ነበር የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ሰፊ መነጋገሪያ የኾነው።

ሌላኛው የሳምንቱ መነጋገሪያ ርእስ የነበረው የአትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ቤተሰቦች ከስድስት ወር መለያየት በኋላ ማክሰኞ የካቲት 7 ቀን 2009 ዓም ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ዳግም መገናኘታቸው ነበር። ዜናው በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ሰፊ ሽፋን አግኝቷል።

አትሌት ፈይሳ መቼም ቢሆን ከሀገሩ ርቆ በስደት ስለመኖር አስቦ እንደማያውቅ ተናግሯል። ከቤተሰቦቹ ጋር ዳግም መገናኘቱ እጅግ እንዳስደሰተውም ገልጧል። አትሌት ፈይሳ ከቤተሰቦቹ ጋር ተገናኝቶ በሚደሰትበት ቅጽበት ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አሁንም ድረስ መገደላቸው፣ መገረፋቸው፣ መጋዛቸው፣ የትም መጣላቸው እና በድኅነት አረንቋ መማቀቃቸውን እንደማይዘነጋው አስታውቋል።  

ሕዝብ ያሸንፋል ያለው አትሌት ፈይሳ፦ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ የምዕራቡ ዓለም ማኅበረሰብ ሀገሪቱ ውስጥ ሰብአዊ መብት ይዞታ ባሽቆለቆለበት በአሁኑ ወቅት  የውጭ ርዳታቸውን እና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ቆም ብለው እንዲያጤኑ ጠይቋል። 

አትሌት ፈይሳ በኋላ ላይ በተቀለበሰው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጉዞ እገዳ ውሳኔ ምክንያት ቤተሰቦቹን የማግኘት ስጋት ገብቶት እንደነበረ መናገሩም ተዘግቧል።  አትሌት ፈይሳ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአየር ማረፊያ ባለቤቱን እና ሁለት ልጆቹን አቅፎ የተነሳው ፎቶ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች በስፋት ተሰራጭቷል።  
አትሌት ፈይሳ ሊሌሳ በፍቅረኞች ቀን ከቤተሰቦቹ ጋር መገናኘቱንም የጠቀሱ አሉ። የፍቅረኞች ቀንን በእንግሊዝኛው (valentines day) አይመለከተንም እንዲሁም ጥሩ ጥሩውን ከውጭ ሀገር ሰዎች ብንወስድ ምን አለበት የሚሉ አስተያየቶች ተንሸራሽረዋል።  በአንጻሩ የገዢው ኢሕአዴግ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ያን ያኽል ትኩረት አላገኘም።

አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በብራዚሉ የሪዮ ማራቶን ሁለተኛ በወጣበት ቅጽበት የተቃውሞ ምልክት ሲያሳይ
አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በብራዚሉ የሪዮ ማራቶን ሁለተኛ በወጣበት ቅጽበት የተቃውሞ ምልክት ሲያሳይምስል Getty Images/AFP/O. Morin

ጥቂት አስተያየቶች በዶይቸ ቬለ የአማርኛው ክፍል የፌስቡክ ገጽ ላይ ተሰጥተዋል። የተወሰኑትን እንመልከት። «ይኽ ድርድር ወያኔ እድሜውን ለማራዘም የፈጠረው ሌላው ትርጉም የለሽ ስልት ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ዛሬም አልባነኑም» በሞሐመድ አህመድ የተሰጠ አስተያየት ነው፡፡ ዮሃና አብርሃም ደግሞ፦  «ህወሀትን ማመን እንዴት ነው?» ስትል ጠይቃለች።

«ምንም ትርጉም የለሽ ዉይይት ነዉ!!ኣምባገነኑ የወያኔ መንግስት እሚገረሰስበት ስልት መንደፍ እና ወደተግባሩ መግባት ነዉ መፍትሄዉ። የወያኔ የግፍ ኣገዛዝ ልክ እንደኢቦላ ወረርሽኝ:ከዳር እስከዳር ኢትዮጵያን ነዉ ያዳረሰዉ» ያለው ደግሞ ጎይቶም ባሕታ ነው። ገዢው ኢሕአዴግ እና 21 የፖለቲካ ፓርቲዎች የፊታችን ዐርብ ለመወያየት ቀጠሮ መያዛቸውም  የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቅሷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ