1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ሰኞ፣ መጋቢት 16 2011

በሳምንቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተፈናቃዮች ንፉግ ሆኗል በሚል የተቀሰቀሰ ሙግት፤ የሕዝብ እና ቤቶች ቆጠራ መራዘም እና ሐሰተኛ ዜና እና የኢትዮጵያ ኹናቴ ያሳሰባቸው የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መልዕክት ትኩረት ያገኙ የማኅበራዊ ድረ-ገፆች መወያያ ነበሩ። 

https://p.dw.com/p/3FWk4
Äthiopien Commercial Bank of Ethiopia in Addis Abeba
ምስል DW/E. Bekele

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በአማራ ክልል ለተጠለሉ ዜጎች እርዳታ ለማሰባሰብ በተካሔደው መርሐ-ግብር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ንፉግ ሆኗል በሚል የቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ ትችት እና ውዝግብ በሳምንቱ አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል ይገኝበታል። አያሌው መንበር የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "የአማራ ተፈናቃዮችን ቴሌቶን በሚመለከት አንዳንድ ቅሬታዎችና መጣራት ያለባቸው ጉዳዮች" ብለው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል ይኸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጉዳይ ይገኝበታል። አያሌው "የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተፈናቀሉ አማራዎች በተደረገው ቴሌቶን ምንም አይነት ድጋፍ አለማድረጋቸው የሚነግረን ነገር እንዳለ አልዘነጋነውም" ሲሉ በግል የፌስቡክ ገፃቸው ሐሳባቸውን አስፍረዋል። 

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው "ንግድ ባንክ ሀብታሙን እንጅ ድሃውን አማራ አልፈልገውም በማለቱ በርካቶች አማራጭ ባንክ እየፈለጉ ነው። ሀብት ያለው አማራም ከድሃው ወገኑ ጎን መቆሙን አሳይቷል። ገንዘቡን ከንግድ ባንክ በማውጣት ደግሞ ይበልጥ አጋርነቱን ማሳየት አለበት" ሲል በንግድ ባንክ ላይ የተነሳውን ተቃውሞ አበረታቷል። ጌታቸው በተቃውሞ የተቀዳደዱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መገልገያ ደብተሮች የሚያሳይ ምስል በፌስቡክ ገጹ አሰራጭቷል። 

በማኅበራዊ ድረ ገፆች በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች ከዚህ ቀደም በንግድ ባንኩ በኩል ይከፈላቸው የነበረ ደሞዝ ወደ ሌላ ተቋም እንዲቀየር ጠይቀዋል የሚሉ መረጃዎች ታይተዋል። ሸዋ ኢንሳይት የተባለ የፌስቡክ ገፅ "ንግድ ባንክ ላይ የተጣለው ማእቀብ የቀጠለ ሲሆን በሸዋ መርሀቤቴ እና ኤፍራታና ግድም ወረዳዎች የሚገኙ የግብርና ፅህፈት ቤት ሰራተኞችን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ሰራተኞች ደሞዛቸው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ አባይ ባንክ እንዲዞርላቸው ጠይቀዋል" በሚል ያሰራጨው መረጃ በምሳሌነት ይጠቀሳል።

"በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ እየተካሄደ ያለውን የብሔርተኝነት ዘመቻና የማዳከም እንቅስቃሴ የአቅመ ቢስ የፖለቲካ ስብስቦች ውጤት ነው"  ያሉት ማቲየል ሙለታ በበኩላቸው ዘመቻውን በጽኑ እንደሚቃወሙ ገልጸዋል። ኪዳነማርያም ደግሞ "ንግድ ባንክ ላይ የተከፈተው ዘመቻ አግባብነት የለውም። እከሌን ካልረዳ እንጎዳዋለን ብሎ ማስፈራራት የትም አያደርስም። ችሮታ በግዴታ እንዴት ይሆናል? ንግድ ባንክ መስጠት ካልፈለገ ትዝብቱን ለህዝብ እንተወው" የሚል ሐሳባቸውን አጋርተዋል። ጌታሁን ወልዴ በፌስቡክ ገፃቸው "ተራ ጫወታ አቁሙ። ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀጥሎ የሐገሪቱ እና የኢትዮጵያውያን ሐብት ነው" በማለት ዘመቻውን ነቅፈዋል። 

በማኅበራዊ ድረ-ገፆች የተደረገው ዘመቻ ፍሬ አፍርቶ ባንኩ 20 ሚሊዮን ብር ለመስጠት ቃል መግባቱን የሚጠቁም ደብዳቤ ተሰራጭቶ ነበር። ወሬው ከተሰማ በኋላ ደጀን ምንይሉ "ንግድ ባንክ 20 ሚሊዮን ብር እያለቃቀሰ ሰጠ ነዉ ምትሉኝ? 'አማራን ተዉት፣ ምንም አያመጣም' የሚባልበት ዘመን አልፏል። በገዛ ገንዘባችንም አንደለልም፤ ከዚህ በኋላ ለሁሉም ጉዳይ የራሳችን ምርጫዎች ይኖሩናል" ሲሉ ሐሳባቸውን አጋርተዋል። ይሁንና ዘግየት ብሎ ይኸኛውም መረጃ ሐሰተኛ መሆኑ ተሰማ። 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጋቢት 11 ቀን 2011 ዓ.ም. "ባንኩን በተመለከተ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ከሚሰራጩ ሀሰተኛ መልዕክቶች ይጠንቀቁ" በሚል ርዕስ ባሰራጨው መግለጫ በፌስቡክ እና በትዊተር ጎራ ለይቶ ለሚያጠዛጥዘው ጉዳይ መፍትሔ ለማበጀት ሞክሯል። ባንኩ "ሰሞኑን የተወሰኑ ግለሰቦች በማሕበራዊ ሚዲያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአምቦ ስታዲየም፣ ትምህርት ቤት… 400 ሚሊዮን ብር ሰጠ እንዲሁም ለአማራ ክልል ተፈናቃዮች 20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ ወዘተ… የሚሉ ፍጹም ሀሰተኛ መልዕክቶች እየተሰራጩ ይገኛሉ። ባንኩ ለአምቦ ስታዲየምም ሆነ ለአማራ ክልል ተፈናቃዮች የሰጠው የገንዘብ ድጋፍ የለም። በያዝነው በጀት ዓመት ባንኩ በዘጠኙ ክልሎች እያስገነባ ላለው የጤና ጣቢያዎች እና ለመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ከሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ውጪ ለየትኛውም ክልል ይሁን ተቋም የገንዘብ ድጋፍ አላደረገም" የሚል መረጃ ሰጥቷል። 

መግለጫው "የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ባንክ ነው። ባንኩ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሀብት ነው። ስለሆነም እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የሚያገለግለውና የሚደግፈው ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ አግባብ በራሱ ተነሳሽነት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል" የሚል ሐሳብ ይዟል። 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተፈናቃዮች ድጋፍ አልሰጠም የሚለው ዘመቻ የቀሰቀሰው ፍጭት ከፍ ብሎ የተቋሙን አመራሮች የብሔር ስብጥር ወደማጠያየቅ ተሻግሯል። የማኅበራዊ ድረ-ገፆች ተጠቃሚዎች፣ አራማጆች እና ፖለቲከኞች ይኸንንው የብሔር ስብጥር ያሳያል ያሉትን ቁጥር እያጋሩ ነው። 
 

ቆጠራው 

የኢትዮጵያ መንግሥት በመጪው መጋቢት 29 ቀን ይጀመራል ተብሎ ይጠበቅ የነበረውን የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ ለማራዘም ሐሳብ አቅርቧል። ቆጠራው ቀድሞም ተቃውሞ በርትቶበት ነበር። ዮሐንስ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ "የኢትዮጵያ የሕዝብ ቆጠራ ውጤትን ሳስበው ሳስበው በጣም ያስቀኛል። ከ1.5 – 2 ቢሊዮን የምንሆን ይመስለኛል። ኦሮሞ እና አማራ እያንዳንዳቸው 300 ሚሊየን ነን ማለታቸው አይቀርም" ሲሉ በቀልድ ሥራው የገጠመውን ፈተና አስቀድመው ለመጠቆም ሞክረው ነበር። የማራዘም ሐሳቡ በይፋ መቅረቡ ከመሰማቱ በፊት ማሒ የተባሉ ትዊተር ተጠቃሚ "የሕዝብ እና የቤት ቆጠራውን እናራዝመው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ቆጠራውን ለማካሔድ ትክክለኛው ጊዜ አይደለም። ችኮላው ለምን ነው?" የሚል ሐሳብ አቅርበው ነበር። ኖሌ ጃላል የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ በበኩላቸው "ኢትዮጵያ ከቆጠራው አውጪኝ። መጪው የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ አጠራጣሪ ይመስላል። አልቆጠርም" የሚል ሐሳባቸውን አጋርተዋል። ኖሌ "ለመሆኑ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በቆጠራው እንዴት ሊያካትቷቸው አቅደዋል?" የሚል ጥያቄ ጭምር አቅርበዋል። 

የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ ኮሚሽን መጋቢት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሔደው ስብሰባ ለ4ኛ ጊዜ ሊካሔድ የታቀደው ቆጠራ እንዲራዘም ውሳኔ ማሳለፉን የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል። ጽህፈት ቤቱ በፌስቡክ ገጹ ይፋ ባደረገው መግለጫ መሰረት የሕዝብ እና የቤት ቆጠራውን የማካሔድ ሥልጣን የተሰጠው ኮሚሽን ያሳለፈውን ውሳኔ ለተወካዮች ምክር ቤት እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ልኳል። 

በተለያዩ ግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ መኖሪያ ቀያቸው አለመመለሳቸው ቆጠራውን ለማራዘም ካስገደዱ ምክንያቶች መካከል እንደሚገኝበት የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት አስታውቋል። የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት መግለጫ እንደሚጠቁመው "የቆጠራውን አላማና ግብ በአስተማማኝ ሁኔታ ለማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት የተሟሉ ባለመሆናቸው ማለትም በየአካባቢው ለስራው መሳካት በተገቢው ሁኔታ መጠናቀቅ የሚገባቸው ተግባራት ባለመጠናቀቃቸው" ተጨማሪ ጊዜ ማስፈለጉ ለመራዘሙ ሌላኛው ምክንያት ነው። 

PM  Abiy Ahmed  in der Frankfurt Arena
ምስል DW/M. Zimmer

ሐሰተኛ መረጃ እና የጠቅላይ ምኒስትሩ ምክር

"ኢትዮጵያዊነት የሚፈተንበት ወቅት እየመጣ ነው" የሚል ሥጋት የገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች አጠቃቀም ላይ ይበጃል ያሉትን መልዕክት አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ባለፈው መጋቢት 10 ቀን በቢሯቸው በኩል ይፋ ያደረጉት ደብዳቤ እንደሚለው በተለያዩ ፅንፎች በቆሙ ሁለት ኃይሎች ምክንያት "ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን አደገኛ ውጥረት ውስጥ" ይገኛሉ። ዐቢይ ኢትዮጵያውያን አቅማቸውን "በማኅበራዊ ሚዲያ ዐውደ ውጊያ ሀገር ለማተራመስ" ከመጠቀም እንዲቆጠቡ መክረዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ አንዳንድ የማኅበራዊ ድረ-ገፅ ጦማሪዎች "ድረ-ገፃቸውን የሚያነብላቸው ተከታታይና ደጋፊ ማብዛታቸውን እንጂ ሀገር እና ሕዝብ ላይ እየተከሉ ያሉትን አደጋ፤ እየረጩ ያለውን መርዝ ሊያዩት አልቻሉም" ሲሉ ወቅሰዋል።  
"በማኅበራዊ ሚዲያ በጣም የበዙ የሐሰት መረጃዎች ይተላለፋሉ። ሐሰት ጮኾ ስለተነገረ፤ ጎልቶ ስለተፃፈ፤ በብዙ ሰዎች ስለተደገፈ ወይም በታዋቂ ሰዎች ስለተወራ እውነት አይሆንም" ያሉት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሐሳባቸው መወያያ ሆኖ ተስተውሏል። 

አለሙ ማንአለብህ "አንዳንድ ጊዜ ጠቅላይ ምኒስትሩ እንደ አራማጅ ይሆናሉ። ፖለቲከኞች ስህተት የሚሰሩትን የማስተዳደር ኃላፊነት አለባቸው። ጠቅላይ ምኒስትር መምህርም ተለማማጭም አይደለም። ይልቁን በአንድ አገር የሕግ የበላይነት የማስከበር ኃላፊነት አለበት። መንግሥት የሕግ የበላይነት ጠበቃ ነው። ትክክል የሚሰሩ እውቅና ሊሰጣቸው የተሳሳተ ሥራ የሚሰሩ ደግሞ በሕግ ሊጠየቁ ይገባል" የሚል አስተያየታቸውን በጠቅላይ ምኒስትሩ ደብዳቤ ግርጌ አስፍረዋል።  

ጴጥሮስ ታደሰ በበኩላቸው "ያለውን እውነት ማወቅ አለበኝ ብዬ ሙሉ ፅሁፍን አነበብኩት። ነገር ግን ግልፅ አይደለም። እነማን ናቸው ፅንፈኞቹ? ለምን በግልጽ አይነገረንም ....የተደበቀው አጀንዳ ምንድን ነው? ስርዓቱ ሊገባኝ አልቻለም። ዶክተርር ዐቢይ ብቻህን ለምን ትደክማለህ? እውነት አለህ፤ በፍቅር ታምናለህ፤ እውነቱን ለህዝብ አስረዳ፤ ውስጣችሁ ምንድን ነው የገባው? ለማነኛውም ከጎንህ ነኝ እንደማትከዳኝ እርግጠኛ ነኝ" ብለዋል። 

Logos App Twitter Facebook Google
ምስል picture-alliance/xim.gs

ወለጋ ላይ አምስት ሰዎች በታጣቂዎች መገደላቸውን ከሰሙ በኋላ አስተያየታቸውን እንዳሰፈሩ የገለጹት አበበ አሰኑ አያኖ ደግሞ "ጌታዬ ተግባር አልባ ወሬዎ እጅግ ሰልችቶኛል። ጣፋጭ ስብከቶችዎ አጉራዘለሎችን አልገራም። ቆፍጠን፣ መረር፣ ጨከን ማለት ካልቻሉ ሀገራችን እንዳይሆን እየሆነች ነው። ከሙሉ አክብሮት ጋር ቦታዎን ለሚመጥነን ጉልቤ መሪ ይልቀቁና የመኖርም የመሥራትም ዋሥትናችን ይረጋገጥ" የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። 
ጃራ ፈጠነ "በበኩላቸው የተከበሩ ጠቅላይ ምኒስትር የማኅበራዊ ድረ-ገፆች አጠቃቀምን የሚገዛ መመሪያ ይዘጋጅ ዘንድ ያስቡበት። አሊያም በኢትዮጵያ ያለው ኹኔታ እስኪረጋጋ ይዝጉት። ፅንፈኞች ኹከት ከመፍጠራቸው በፊት ጊዜ ያለ አይመስለኝም" ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል። 

ጌታቸው ሳሙኤል ፈለቀ በወገናቸው "እነዚህ የሀሰት ዜና የሚፈበርኩትን ለይቶ እርምጃ የማይወሰደው ለምንድ ነው? ወይስ ይህን የማረግ አቅም ደህንነት ድርጅቱ የለውም? ያም ከሆነ ሶሻል ሚዲያውን ድርግም አርጎ ሰው ልቡን እስኪገዛ መዝጋት ነው" ሲሉ ከጃራ ፈጠነ ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ አንጸባርቀዋል። 

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ