1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሚያዝያ 29 2013

«እሰኪ እንወያይበት በዚህ ሳምንት ህውሀት እና ሸኔ በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ተወሰኗል። ህውሃት የሚባል ድርጅት ያለ እና የነበረ መሆኑ ግልጽ ነው በመሆኑም በሽብርተኘነት ለመፈረጅ ድርጊቱ የሽብር ወንጀሎችን እስካሟላ ድረስ ችግር የለውም ። ሸኔ ብሎ መፈረጅ ግን በግሌ ሽብርተኛ ለማለት መስፍርቱን ያሟላል ብየ አላስብም ። »

https://p.dw.com/p/3t3BE
Repräsentantenhaus in Äthiopien
ምስል DW/Y. Gebreegiziabher

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

“ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ የሚኒስትሮች ምክር ቤት  ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ የውሳኔ ሐሳብ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ አጽድቆታል።  የአውሮጳ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደማይልክ አስታወቋል። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ሕብረቱ ሉአላዊነቴን የሚገዳደር መስፈርት ማቅረቡ ከስምምነት ላለመደረስ ምክንያት ነው ብሏል።  በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የደሕንነት እና ጸጥታ የጋራ ግብረኃይል የምርጫውን ለማደናቀፍ የታቀደ ተግባር ማክሸፉን ባወጣው ዝርዝር መግለጫ ይፋ አድርጓል።ይህንኑ ተከትሎም  የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎችም ከሰሞኑ በርዕሰ ጉዳዮቹ ላይ የተለያዩ አስተያየቶችን ሲያጋሩ ቆይተዋል። የዕለቱ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅታችንም ትኩረቱ አድርጓል። አብረን እንቆይ።

በሚንስትሮች ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ አቅራቢነት ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው “ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት መፈረጃቸው በርካቶች የተለያዩ ሃሳቦችን እንዲያጋሩ ምክንያት ሆኗል። ሕወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ የተወሰነውም ድርጅቶቹ ሲፈፅሙ እና ሲያስፈፅሙ የነበሩት ጥፋቶች የሽብር ወንጀል ተግባራት በመሆናቸው እና ፈፃሚዎቹን በተናጥል በሽብር ወንጀል ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ድርጅቱን የሽብርተኛ ድርጅት አድርጎ መሰየሙ «የሽብር ወንጀል ድርጊቶቹን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር እና ለመከላከል» ሲል መንግስት ገልጿል የአምላክ ቃል ያውቃል በሳቅ በጀመሩት አጭር የፌስ ቡክ አስተያየታቸው «ብሂሉም "ትንሽ ስጋ እንደመርፌ ትወጋ" ነው። የተወለደ አንጀት አልቆርጥ አላቸውና ተቃዋሚ ካለ ብለው መረጃ ጠየቁ። ግን "ሸኔ" ማነው? ለማንኛውም ህወኃትና ሸኔ በሽብር ካልተጠየቁ የሽብር ህግ መኖሩ አስፈላጊ አደለም። » ዓሊ መሐመድ ደግሞ አዎ አሉ።«አዎ እንደኔ እንደውም ዘግይተዋል ባይ ነኝ ። ለሌሎች ሰዎች የመብት ጥሰት ግን መንግስት በትኩረት መስራት ያለበት ጉዳይ ነው። ብለዋል።

Äthiopien Addis Abeba | Volksrepräsentantenhaus
ምስል DW/Y. G. Egiziabher
Äthiopien TPLF feiert 45 jähriges Gründungsjubiläum in Mekelle
ምስል DW/M. Haileselassie

 ታመነ አደራ በፌስ ቡክ በጻፉት አጭር መልዕክታቸው ሕወሓት እና ሸኔን አሸባሪ ብሎ ከመፈረጅ መንግስት የራሱን መዋቅር ይፈትሽ።  ምክንያቱም አሁንም በነዚህ ድርጅቶች ስም  በህቡአ በተደራጀ ቡድን የከፋ ችግር ይፈጸማል ። በተለይ ሆን ተብሎ ሀይማኖቶችን ለማጋጨት በመዋቅር የሚሰሩ አሉና ዙርያ ገባው በጥንቃቄ ሊፈተሽ ይገባል ።» ብለዋል።
ወልድ ዋህድ ይመኑ ደግሞ አይፈረጁ የሚል አካል የለም::እንዴዉም ዘግይቷል እነርሱ ያልተፈረጁ ማን ሊፈረጅ? ብለው ሲጠይቁ
አማኑኤል ዮሐንስ በበኩላቸው ፓርላማውን በወቀሱበት አስተያየታቸው «ፓርላማዉ እራሱ ከሸኔ የፀዳ መሆኑ አይታወቅም ምን በጉያ ተይዞ አፋልጉኝ፣ ጆሮህን ቆርጦ በየትኛዉ እጄ ይዤዋለሁ ብሎ መጠየቅ ነው። ብለዋል።

ዮሐንስ ተገኘ ደግሞ እሰኪ እንወያይበት በዚህ ሳምንት ህውሀት እና ሸኔ በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ተወሰኗል። ህውሃት የሚባል ድርጅት ያለ እና የነበረ መሆኑ ግልጽ ነው በመሆኑም በሽብርተኘነት ለመፈረጅ ድርጊቱ የሽብር ወንጀሎችን እስካሟላ ድረስ ችግር የለውም ። ሸኔ ብሎ መፈረጅ ግን በግሌ ሽብርተኛ ለማለት መስፍርቱን ያሟላል ብየ አላስብም ። ምክኒያቱም ሸኔ የተባለ ድርጅት ነኝ የሚል አካል መኖር አለበት። እኔ ምሰማው ኦነግ ሸኔ የሚል እንጅ ሼኔ የሚል ድርጅት አላውቅም። እኔ ነኝ ብሎ ሀላፊነት የወሰደም ሆነ የሚወስድ የለም ይህ ከሆነ ደግሞ በሸኔ አባልነት ተባባሪነት እንዲሁም ተሳታፊነት ወንጀል ፈጽመሀል ብሎ ሰውን ለመክስስ ወንጀልን ለማቀቋቋም ከሚያስፈልጉት የሀሳብ ክፍል፣ የድርጊት ክፍል፣የህግ ክፍል መስፍርቶች ውስጥ የህግ ክፍልን አያሟላም ። ምናልባት ምክር ቤቱ ቢያጸድቀው ለአፈጻጸም የሚያስቸግር ይመስለኛል» በማለት አስተያየታቸውን አካፍለዋል።

ግርማቸው ጌትነት በተመሳሳይ ባሰፈሩት ምጸታዊ አስተያየታቸው «ግን "ሸኔ" ማለት ማን ነው?»  በማለት ይጠይቃሉ። «ሲጠራ አቤት ሲል አልሰማን። ወይ በግለፅ እኔ ሸኔ ነኝ ሲል አላደመጥን። ወይም ለደረሱ ጥቃቶች ኃላፊነቱን ወስጃለሁ ሲል አልሰማን። ታዲያ በሌለ እና በገሀድ ያልታየን ሽብርተኛ ማለት ምን ማለት ይሆን? "ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ" አሉ አያቴ።» በማለት ጽፈዋል።

 የአውሮጳ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደማይልክ አስታወቋል።ሕብረቱ ከውሳኔው የደረሰው የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ሕብረቱ ባስቀመጣቸው ቁልፍ መስፈርቶች ከስምምነት አለመደረሱን ተከትሎ  መሆኑን የሕብረቱ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሬል ባለፈው ሰኞ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ሕብረቱ ሉአላዊነቴን የሚገዳደር መስፈርት ማቅረቡ ከስምምነት ላለመደረስ ምክንያት ነው ብሏል።  ይህንኑ ተከትሎም በርካቶች በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ አስተያየቶቻቸውን አጋርተዋል። ሰለሞን ኃይለማርያም በፌስ ቡክ ባሰፈሩት አስተያየታቸው « የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ ተገቢነት አለው ፡፡አውሮፓ ህብረት ገንዘብ ስለሚያበድር ብቻ አፍሪካ ውስጥ የመንግስታትን እጅ መጠምዘዝ አለብኝ ብሎ የሚያስብ የቀኝ ገዢዎች ስብስብ ነው፡፡በተለይ በየክፍለ አለማቱ የሚፈለፈለው አሽባሪዎች የምዕራባዊያን ጥፍጥፍ እንደሆኑ የማያውቀው የአለም ህዝብ ቀላል አይደለም፡፡ ምክንያት ግልፅ ነው በርካታ ስራ አጦች በአባል ሀገራቱ የሚገኝ በመሆኑ ስራ ይፈጠርላችዋል በሌላኛው ግን ለጦር መሳሪያችው በቂ ገበያ ያገኛሉ፡፡ ተጨማሪ በርካታ እኩይ አላማችውን ለማስፈፀምም ይረዳችዋል፡፡» ብለዋል። ኦስማን ጉላይ የተባሉ በትዊተር በጻፉት አስተያየታቸው የአውሮጳ ሕብረት በቀጣዩ ምርጫ ታዛቢዎቹን ላለመላክ መወሰኑ ኢትዮጵያውያን ሉዓላዊነታቸውን ማስጠበቃቸውን ያሳያል። ኢትዮጵያውያን ወንድም እና እህቶች እንኳን ደስ አላችሁ። ብልህ ሉዓላዊ መንግስት መቼም የቅኝ ገዚዎችን ቅድመ ሁኔታ አይቀበልም።» ብለዋል።

EU flags at half-staff after terror attacks in Vienna, Nice
ምስል picture alliance / Kyodo

ህሊና አበበ በትዊተር በጻፉት መልዕክታቸው ቅኝ ገዢዎች በ1900ዎቹ እና አሁን በተመሳሳይ የመጫወቻ ካርድ ነገር ግን የአፈጻጸሙ መንገድ ብቻ ነው የሚለያየው » ይላሉ። ህሊና አያይዘው  «በ1900ዎቹ ጦር አዝምተው እና በአካል ተገኝተው አፍሪካን ቁምስቅሏን ሲያሳይዋት ነበር። አሁን ደግሞ በኮምፒውተር መተየቢያቸው ያንኑ ለመድገም ይሻሉ» በማለት ጽፈዋል።

ብሩክ ያሲን በበኩላቸው በፌስ ቡክ በጻፉት አስተያየት «ልታዘብ ሲሉ በገዥ ፓርቲው ታግደው ቢሆን ጮማ አጀንዳ በሆነ። አሁን እራሳቸው ናቸው ከመታዘብ የተቆጠቡት! በባለፈው ምርጫ ግዜ ንቁ ታዛቢ ነበሩ 100% ኢህአዴግ ባሸነፈበት ምርጫ። አድንቀው ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫ ብለው አሞካሽተው የሄዱ መሆነቻውን ሳንዘነጋ።» ብለዋል።

ለማ በገቢ የተባሉ ሰው ደግሞ «ደሃ አገር ሉአለዊነት የላትም ሲሉ አልነበር እንዴ ዛሬ ሉአላዊነት ከየት መጣ» በማለት የኢትዮጵያ መንግስት ስለሉዓላዊነት የሰጠውን ምላሽ ወቅሰው ጽፈዋል።

ጉዲሳ በርበዳ «በልመና ላይየተመሰረተች አገር ምን ልትሆን ይሁን እርዳታ ሰጭ አገራት ፊታቸውን ሲያዙሩባት ? ብለው ጠይቀዋል።አበራ መብራቱ ም «የአውሮፓ ህብረት በምርጫው ላይ በታዛቢነት አልገኝም ማለቱ ፥ ለተቀረው ዓለም የሚሰጠው መልዕክት ጥሩ አይሆንም !» ሲሉ ስጋታቸውን የገለጹበትን ሀሳብ አስፍረዋል።«ስንታየሁ አሰፋ በበኩላቸው በርግጥ እርዳታ ላይ ተንጠልጥላ የምትኖርን ሀገር እንደፈለጉ ቢያደርጉ ጥፋቱ የእኛ የዜጎች እንጅ የነርሱ አይደለም። እንደምናየዉም የእኛ ሀገር ገዥም ሆነ ተቃዋሚ ፖለትከኛ የስልጣን ጥመኛ ነዉ።ነገር ግን የነሱም ፍላጎት ግልፅ ነዉ፣ የሚመቻቸዉን ሰዉ ማስቀመጥ። የሊቢያ ህዝብ ምን ኀድሎት ነዉ ጦር አዝምተዉ መከራ ዉስጥ የከተቱት፣ ጋዳፍ ስለናቃቸዉ። እራቅ ላይ በዉሸት ፕሮፓጋንዳ ዘምተዉ ስያወድሟት ማን ከሰሳቸዉ?»

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የደሕንነት እና ጸጥታ የጋራ ግብረኃይል የምርጫውን ለማደናቀፍ የታቀደ ተግባር ማክሸፉን ባወጣው ዝርዝር መግለጫ ይፋ አድርጓል። ግብረሃይሉ እንዳለው «ስለአዲስ አበባ ዝም አንልም» በሚል በሀገር ውስጥ እና በተለያዩ የውጭ ሃገራት በህቡዕ የተደራጀ ኃይል መኖሩን ጠቅሶ ከሀገር ውስጥ 15 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል። ይህንኑ ተከትሎ በርካቶች አስተያየቶቻቸው አጋርተዋል።

ላመስግነው ተካ ባሰፈሩት አስተያየታቸው «ሙሉ ከተማ ሲጠፋ ቸል ብሎ የነበረ የደህንነት መስሪያ ቤት ህዝብ ሲገደል ለምን ይገደላል ብሎ ስለጠየቀ ድምጽን ለማፈን የሚደረግ ሩጫ መሆኑ ነው።»

በሪሁን አበበ በበኩላቸው «ሀገሪቱን ለመበታተን ያቀዱትን በዚህ መንገድ በቁጥጥር ስር በማዋል ማክሸፍ ለህ/ሰቡ ትልቅ እፎይታ ነው።» በማለት ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

ብርሃኑ ታገለ «በግላጭ ተደራጅተው ታጥቀው ሀገር የሚያሸብሩትን እረስተህ ጭራሽ በህቡዕ ትላለህ» ሲሉ ጠይቀዋል።

ዊንታ ተስፋዬ ደግሞ «ፌደራል ፖሊስ፣ መከላከያ ሰራዊታችን እና ብሄራዊ ደህንነት የሀገር ምሶሶ መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል! ሀገር እነዚህ ሶስቱ ተቋማት እያሉ መቼም አትፈርስም!» ሲሉ ተግባሩን ያመሰገኑበትን ሃሳብ አካፍለዋል። ቅድስት በቀለ በበኩላቸው «ሰላም ለኢትዮጵያ ይሁን እባካችሁ እርስ በራስ ከመጨራረስ ሀሳብ እንውጣ እና ወደ አንድነት እንምጣ! የውጩም የውስጥም ጠላት ቢበትናት እኮ እኛም ግብፅ እና ሱዳን መንገድ ላይ ፈሰን የመለምን እድል ነው የሚገጥመን። አገር ብትበተን ተጎጂው ሁሉም ነው። ሰብሰብ እንበል።» በማለት ጽፈዋል። እንግዲህ አድማጮች ለዛሬ ያልነው የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግታችን ይህን ይመስል ነበር ። ከዝግጅቱ ጋር ታምራት ዲንሳ ነኝ ጤና ይስጥልኝ።

ታምራት ዲንሳ

አዜብ ታደሰ