1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ መስከረም 14 2014

የቆቦ የንፁሃን ግድያ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጫ፣የቀድሞ የኦነግ ሸኔ የደቡብ ዞን ዋና አዛዥ ሰላማዊ ትግልን ተቀላቀሉ መባል፤የሙሃዘ ጥበባት ዴያቆን ዳንኤል ክብረት ንግግርና የአሜሪካ ውግዘት በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ያነጋገሩ ጉዳዮች ነበሩ።

https://p.dw.com/p/40od7
Logos App Twitter Facebook Google
ምስል picture-alliance/xim.gs

የአርብ መስከረም 14, ቀን 2014 ዓ.ም. የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት


የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)  በቅርቡ ባወጣው መግለጫ  በቆቦ ከተማና በአካባቢው በንፁሃን ዜጎች  ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በእጅጉ እንዳሳሰበው አመልክቷል። ኮሚሽኑ ደረሱኝ ባላቸው መረጃዎች  በአካባቢው  ግድያ፣ ዝርፊያ እንዲሁም የመሰረተ ልማት ውድመት መፈፀሙን ገልጿል። በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ኃይሎች ተፈፀመ በተባለው በዚህ ጥቃት ቀጣይ ምርመራ እንደሚያደርግ ገልጿል። 
ይህንን ተከትሎ ጉዳዩ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ዘንድ ብዙ መነጋገሪያ ሆኖ ነው የሰነበተው። 
የማሪያም ልጅ በሚል የፌስ ቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት «ሕወሓት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች  ጥቃት ተፈፀመ እየተባለ  የመንግስት ዝምታም  አልገባኝም። ምን እስኪሆን እየተጠበቀ ነው?» ሲል ይነበባል።
 ፅጌ ዓለሙ  በበኩላቸው «የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተብየው መቼ ነው የሚያጣራው። ሰው ካለቀና መረጃ ከጠፋ በኋላ ነው? ብቻ እግዚአብሄር ይድረስልን» በማለት በቁጭት ፅፈዋል። 
ነገሩ ግራነው በሚል የፌስቡክ ስም ደግሞ፦ «ሕወሓት ምንም ቢያደርግ ተጠያቂው መንግስት ነው። አሸባሪ ብሎ ለፈረጀው አካል ቦታ አስረክቦ ተቀምጦ ማልቀስ ምን እሚሉት ነው?» የሚል አስተያየት ሰፍሯል።
«ከሞት የተረፉት ደግሞ በረሀብ እና በጥም እንዲሁም መድሃኒት አጥተው እየተሰቃዩ ነው። ማን ይድረስላቸው? መንግስትም የርዳታ ድርጅቶችም ዝም ብለው ማየታቸው ያስተዛዝባል» ያሉት ደግሞ ወሎየዋ ነኝ  የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው። 
ማሙሽ ማሙሽ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት፦ «ቆይ ግን መንግስት የመጀመሪያ ስራዉ ህዝቡን ከወራሪ መጠበቅ መስሎኝ በዛ ላይ አባረርናቸዉ ለወሬ ነጋሪ ሳይቀሩ ጨረስናቸው እያላችሁ። ምስኪኑ ህዝብ እናንተን አምኖ ቤቱ ተቀምጦ እየሞተ ነዉ። ራሱን እንዳይከላከል መሳሪያ የለውም። ፈጣሪ ፍርዱን ይስጥ» ብለዋል።
«መቼ ነው ከመርዶና ከሞት ዜና የምንወጣው? የሰው ሞት ተራ ነገር ሆነ።እግዚአብሄር ለሀገራችን ሰላም ያውርድ። ያሉት ደግሞ በዛብሽ  የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው።
ሌላው በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን  ያነጋገረው ጉዳይ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በአሸባሪነት የፈረጀው እና ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራዉ የኦነግ ሸኔ የደቡብ ዞን ዋና አዛዥ ታጣቂ ቡድኑን ትተው ሰላማዊ ትግልን  ተቀላቀሉ መባሉ ነበር። 
ታጣቂ ቡድኑን ለ14 ዓመት መርተዋል የተባሉት  አቶ ጎሌቻ ዴኒጌ፤ ወደ ሰላማዊ ትግል የመጡት የቀድሞ ድርጅታቸው ኦነግ ሸኔ በቅርቡ ከሕወሓት ጋር የፈጠረውን ጥምረት በመቃወም መሆኑን  የሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። አቶ ጎሌቻ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ይህንን ተከትሎ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ዘንድ የድጋፍና የነቀፌታ አስተያየቶች ተንሸራሽረዋል።
አበበ ዘማሪያም «በዚህ ሁኔታ ሕወሓትንም ተደራድረው በቀይ ምንጣፍ  መቀበላቸው አይቀርም» ሲሉ፤ መሰሉ አባተ ደግሞ «አዛዡ ወደ ሰላማዊ ሕይወት ሲመለሱ  እነሱ ያፈናቀሏቸው ሰዎች እና ወላጅ አልባ ያደርጓቸው ህፃናት  ግን አሁንም ድረስ ሜዳ ላይ ናቸው» የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። አቲ የእናቱ ልጅ በሚል የፌስ ቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ «በአሸባሪነት ከተፈረጀ ድርጅት ጋር ሆኖ ሰው ሲገል እና ሲያፈናቅል ቆይቶ፤ ሲበቃው ወደ ሰላማዊ ሕይወት ሲመለስ አቀባበሉ እንደዚህ ከሆነ፤ የሕወሓት አመራሮችም መምጣት አለባቸው» ብለዋል። 
ሀገሬ ኢትዮጵያ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ «ያጠፋውን ይቅር እያልን። ለሰላም እጁን የዘረጋውን እየተቀበልን ካልሆነ የትም መድረስ አንችልም። ከስንቱ ጋርስ ጦርነት ገጥመን እንችለዋለን» ሲሉ መልሰዋል።
 በርቺ ኢትዮጵያ በበኩላቸው «እንደሰማነው የቀድሞው የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ዋና አዛዥ ተቃዉሞ፤ ሸኔ ከሕወሓት ጋር መቀላቀሉን ብቻ ነው። ስለዚህ በሸኔ የንፁሃን ግድያ  ተስማምተዋል ማለት ነው። ያሳዝናል» ሲሉ፤ ያልፋል ቀኑ በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት  «በጦርነት ወቅት ሰላማዊ ድርድር ያለ እና የነበረ ነው። ሌሎች ሀገራትም ይህንኑ አድርገዋል። አዲስ ነገር አይደለም» ይላል።
ሄኖክ ውብሸት የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ «ወንጀለኛ በቦሌ ምስኪኑ እስክንድር ደግሞ ከርቸሌ የቀልድ ሀገር» በማለት ለቀድሞው የሸኔ አዛዥ የተደረገውን የቦሌ አቀባበል ተችተዋል።
«ብዕር የታጠቀን ጨለማ የምታስር፤ የአሸባሪን አውራ ጠርታ የምትሞሽር» በማለት ሀሳባቸውን በስንኝ ያሰፈሩት ደግሞ ሲስ ካሳ የተባሉ የፌስቡክ አስተያየት ሰጪ ናቸው።
የጠቅላይ ሚንስትሩ  አማካሪና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባል ሙሀዘ-ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአንድ መድረክ ተናገሩት  የተባለውን ንግግር አስመልክቶ የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ያቀረበው ዘገባ  በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  ብዙ መነጋገሪያ ሆኖ ነው የሰነበተው።
በመድረኩ ዲያቆን ዳንኤል  ተናገሩት የተባለው «እነሱ መጥፋት አለባቸው» የሚል ንግግር  አሜሪካ   «የጥላቻ ትርክት»   በሚል  የኮነነችው ሲሆን፤ ዲያቆን ዳንኤል ለዜና ምንጩ በሰጡት ምላሽ «እነሱ» የሚለው ቃል ሕወሓትን የሚመለከት መሆኑን ገልፀዋል። ይህንን ተከትሎ  የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ጎራ ከፍለው ተከራክረውበታል።
ጓል ትግራይ የተባሉ አስተያየት ሰጪ «አንድ የሃይማኖት ሰው ህዝብ  ይጥፋ ማለቱ ያሳዝናል። መወገዝም አለበት» ሲሉ፤ እውነቱ ይበልጣል ደግሞ «ዳንኤል የተናገረው ስለ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ስለ አንድ የፖለቲካ ድርጅት እንጅ ስለ ሕዝብ አልተናገረም» ብለዋል። 
ነብዩ ኃይሉ በበኩላቸው «ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እነዚያ የሚያማሩ ታሪኮችን በተናገረበት አንደበት የጥላቻ ቃል ባያወጣ ደስ ይለኝ ነበር» ያሉ ሲሆን፤ ሰርካለም አድማሱ ደግሞ «ዳንኤል ፈልጎ ያመጣው አይደለም። እየተሰማና እየታዬ ያለው ክፉ ስራ፣ ሞት ፣ መፈናቀል እና ረሀብ ጥሩ የሚያናግር አይደለም። ደግሞስ አሜሪካ የአንድ ግለሰብን የመድረክ ንግግር ከምታወግዝ ለምን በወሎ በጎንደርና በአፋር የደረሰውን የንፁሃን ግድያ አታወግዝም?» በማለት መልሰዋል።
ሀየሎም ሀይሌ የተባሉ አስተያየት ሰጪ «ከግለሰብ ጎን ከምትቆሙ፤ ከህዝብ ጎን ብትቆሙ አይሻልም»ሲሉ፤ ሀበሻዊት ነኝ ደግሞ «በሌሎቹ ንግሮቹ ሊተች ይችላል። ሊያጠፋም ይችላል። ነገር ግን በዚህ መድረክ የተናገረው ንግግር  እንዴት ሊያስተቸው እንደቻለ በግሌ አልገባኝም» ብለዋል።
ገጣሚ ኑረዲን ኢሳ በበኩሉ «ዳንኤል ክብረት ለኢትዮጵያችን ሲቆምላት : እኔስ ለዳንኤል ክብረት ስለምን አልቆምም ? ወቅቱ በአንድነት ብቻ ቀጥ ብለን የምንቆምበት ወሳኝ ወቅት ነው» በማለት ፅፏል።
« እኔን የገረመኝ መንግስትን እየተዋጋ ያለን ቡድን አንድ የመንግስት ኃላፊ በፍቅር እንዲጠራ አሜሪካ መጠበቋ ነው።- ምነው ጦርነቱን በመተሳሰብና በመፈቃቀር ላይ የተመሰረተ አስመሰሉት» በማለት ጆኒ የአርሴናል የተባሉት አስተያየት ሰጪ ነገሩን ወደ ቀልድ ወስደውታል።
ደሳለው ሞላ በበኩላቸው «እኔ እምለው ጎበዝ  ስለተዘረፉት የጤና ተቋማት ስለወደሙት ትምህርት ቤቶች ስለሚንገላቱና ስለሚሞቱት እናቶችና ህፃናትስ መቼ ነው አሜሪካ የምታወግዘው?» ሲሉ ጠይቀዋል።
አባይነህ ካሴ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ዲያቆን ዳንኤል የተናገረው አማርኛ እና አሜሪካኖቹ የተረዱበት እንግሊዝኛ አንድ አይደለም ባይ ናቸው። ረዘም ካለው ጽሑፋቸው ውስጥ እንዲህ የሚል ይገኝበታል።
«ውጫሌን ያስታውሰናል፡፡ ትርጉም ማዛበት ያስከፈልንን ዋጋ ከእኛ በቀር የሚያውቅ የለም፡፡ ነገረ ሠሪ ሲተረጉመው የተለያየ ይኾናል፡፡ በአማርኛ የተነገረውን በአማርኛው ልክ ልትሰሙት ይገባችኋል፡፡ ውጫሌ እኛ ያልነው ሌላ እነርሱ እንዲባል የፈለጉት ሌላ መኾኑን ነበር ያመለከተን፡፡ ለጊዜው በኢትዮጵያ ሕግጋት አንድ የትርጉም ብያኔ አለ፡፡ የአማርኛው ሕግ ከእንግሊዝኛው የተለየ ትርጉም በሚኖረው ጊዜ የአማርኛው የበላይነት አለው ይላል፡፡ ስለዚህ ዳንኤል የተናገረው በአማርኛ እንጅ በእንግሊዝኛ ስለልኾነ በእኛ ዘንድ ልክ ነው፡፡ ጠይቁን እናስረዳችሁ አለበለዚያ ዝም በሉ፡፡ ውጫሌን አታስታውሱን!» በማለት ፅፈዋል።

Daniel Kibret
ምስል Privat
Äthiopien Oromo-Befreiungsfront (OLF)
ምስል DW/N. Desalegn

 

ፀሀይ ጫኔ

ማንተጋፍቶት ስለሺ