1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ወቅታዊ ሁኔታ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 17 2005

ሚሼል ጆቶጅያ የሃገሪቱ ህገ መንግሥቱ መታገዱንና ፓርላማውና ካቢኔውምም መበተኑን ትናንት ማምሻውን አስታውቀዋል ። የቀድሞው ዲፕሎማት ጆቶጅያ ወደ ነፃ ተዓማኒና ግልፅ ምርጫዎች ይወስደናል ያሉት 3 አመት ያህል የሚወስደው የሽግግር ጊዜ በአስቸኳይ ጊዜ ህግ እንደሚመራም ከዋና ከተማይቱ ከባንግዊ ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/184bu
ምስል picture-alliance/ap photo

የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክን መንግሥት አስወግደው ሥልጣን የያዙት የሴሌካ አማፅያን መሪ ሚሼል ጆቶጅያ ሃገሪቱን በአስቸኳይ ጊዜ ህግ እንደሚያስተዳድሩ አስታወቁ ። ዦቶጅያ ትንንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ሐገሪቱን በአስቸኳይ ህግ የሚያስተዳድሩት በ3 አመት ጊዜ ውስጥ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ነው ። በኃይል ሥልጣን በያዙ በማግስቱ የአፍሪቃ ህብረት ሃገሪቱን ከአባልነት ሲያግድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአውሮፓ ህብረት ደግሞ መፈንቅል መንግሥቱን አውግዘዋል ። የሚመሯቸው አማፅያን ርዕሠ ከተማ ባንግዊን ከተቆጣጠሩ በኋላ ባለፈው እሁድ መፈንቅለ ራሳቸውን በማዕከላዊ አፍሪቃ ፕሬዝዳትነት የሰየሙት ሚሼል ጆቶጅያ የሃገሪቱ ህገ መንግሥቱ መታገዱንና ፓርላማውና ካቢኔውምም መበተኑን ትንናንት ማምሻውን አስታውቀዋል ።

Umsturz in der Zentralafrikanischen Republik
ምስል Reuters

የቀድሞው ዲፕሎማት ጆቶጅያ ወደ ነፃ ተዓማኒና ግልፅ ምርጫዎች ይወስደናል ያሉት 3 አመት ያህል የሚወስደው የሽግግር ጊዜ በአስቸኳይ ጊዜ ህግ እንደሚመራም ከዋና ከተማይቱ ከባንግዊ ተናግረዋል ።

ይህ የጆቶጅያ እርምጃ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ በዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ እንድትገለል አድርጓል ል ። በመፈንቅለ መንግሥቱ ማግስት የአፍሪቃ ህብረት ሃገሪቱን ከአባልነት ያገደ ሲሆን ባንጉዊን በተቆጣጠረው የሴሌካ አማፅያን ጥምረት አመራሮች ላይ የተጣለው የጉዞ ና የሃብት ዝውውር ማዕቀቦችን አጠናክሯል ። ህብረቱ መንግሥት የገለበጡት ለፍርድ እንዲቀርቡም ጠይቋል ። የህብረቱ የሰላምና የፀጥታ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ራምታኔ ላማምራ

« የሰላምና የፀጥታ ኮሚሽኑ አባል ሃገራት በአጠቃላይ ህገ መንግሥቱን የሚያፈርሱትን ሽምቅ ተዋጊዎች በማንኛውም መስኮች እንዲያገሏቸው ጠይቋል ። ጎረቤት ሃገራት መጠለያ ባለመስጠት በአፍሪቃ ህብረት በኩል የሚወሰዱትን እርምጃዎች በሙሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ መንግሥት የገለበጡት ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲደረግ እንጠይቃለን ። የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በዚህ ላይ የሚወስደውን አቋምም በጉጉት እየጠበቅን ነው »

15 አባላት ያሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አባላትም ትናንት በቀድሞዋ የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ቅኝ ገዥ ፈረንሳይ አሳሳቢነት በሃገሪቱ ቀውስ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ አካሂደው ነበር ። በስብሰባው ማጠቃለያ ምክር ቤቱ ተጨማሪ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ከማስጠንቀቅ ውጭ ማዕቀብ እንደሚጥል በዝርዝር የጠቀሰው ነገር የለም ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባንኪሙ ግን የሴሌካ አማፅያን ሥልጣን መያዛቸውን አውግዘው በሃገሪቱ ህገ መንግሥታዊ ስርዓት በአስቸኳይ እንዲሰፍን ጥሬ አቅርበዋል ።

Bangui Putsch
ምስል Reuters

የሴሌካ አማፅያን መዲናይቱን ባንግዊ እንደያዙ ነዋሪው በየመንገዱ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዞ ደስታውን በመግለፅ ቢቀበላቸውም ዘራፊዎች መንገዶቹን ሲቆጣጠሩ ስሜቱ ወደያውኑ ደብዝዟል ። ትናንት ሱቆች ተዘግተው የዋሉባት ባንጉዊ ኤሌክትሪክና ራድዮም አልነበራትም ። መፈንቅለ መንግሥቱ በተካሄደበት እለት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ በውል አልታወቀም ። እስካሁን የሚታወቅ ነገር ቢኖር 13 የደቡብ አፍሪቃ ወታደሮች በአማፅያኑ መገደላቸው ነው ። የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ጄኮብ ዙማ እንዳሉት ወታደሮቹ የተገደሉት 9 ሰዓት በዘለቀ ከባድ ውጊያ ነው ። የፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃው «የደቡብዊ አፍሪቃ ሃብት ተመልካች ድርጅት» ሃላፊ ክላውድ ካቤምባ አሟሟታቸውን አስደንጋጭ ብለውታል ።

Zentralafrikanische Republik Seleka Rebellen
ምስል AFP/Getty Images

« የደቡብ አፍሪቃ ወታደሮች በእውነት ሙስና ለተንሰራፋበት ፣ ለአምባገነንና ህዝባዊ መሠረት ለሌለው መንግሥት መሞታቸው ያስደነግጣል ።በሌላ በኩል ደግሞ ወታደሮቹ እዚያ የተላኩት በተለይ በማዕድኑ ዘርፍ የደቡብ አፍሪቃን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው የሚል መከራከሪያም አለ ።»

በ2003 በተካሄደ መፈንቅለ መንግሥትሥልጣን ይዘው በተመሳሳይ መንገድ ከሥልጣን የተባረሩት ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ቦዚዜ አሁን ካሜሩን ናቸው ። የካሜሩን ባለሥልጣናት እንደሚሉት ግን ሃገሪቱ የቦዚዜ ቋሚ መቀመጫ አትሆንም ። ቦዚዜ እጎአ የ2007 አም ቱን የሰላም ውል አላከበሩም ሲሉ ከሥልጣን ያባረሯቸው አማፅያን ከ 2 እስከ 3 ሺህ ይገመታሉ ።

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ