1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ እና የተኩስ አቁሙ ስምምነት

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 19 2006

የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ተቀናቃኝ ወገኖች ባለፈው ረቡዕ የተፈራረሙት የተኩስ አቁም ስምምነት ዘላቂነት እያጠያየቀ ነው። የፈረንሳይ ራድዮ፣ «ኤር ኤፍ ኢ» ባለፈው ሀሙስ እንደዘገበው፣ ስምምነቱን ተፋላሚዎቹ ወገኖች

https://p.dw.com/p/1Cj7H
Brazzaville Versöhnungsforum 23.7.2014
ምስል Guy-Gervais Kitina/AFP/Getty Images

በሀገሪቱ የቀጠለውን ቀውስ ለዘለቄታ ማብቃት የሚያስችል የተሟላ ውጤት ያላስገኘው ነው በሚል ተችተውታል። የተለያዩት ሚሊሺያ ቡድኖች መሪዎች በርግጥ ተዋጊዎቻውን መቆጣጠር መቻላቸው አጠራጥሮዋል። ይህ ሀገሪቱን ምናልባት ክርስትያኖች እና ሙሥሊሞች በሚኖሩባቸው ሁለት አካባቢዎች የመከፋፈል ስጋት ይደቅን ይሆን?

ካለፈው ሰኞ እአአ ሀምሌ 21 እስከ ረቡዕ ሀምሌ 23 ድረስ በኮንጎ ሬፓብሊክ መዲና ብራዛቪል በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የሚካሄደውን ደም አፋሳሽ ውዝግብ ለማብቃት የሚያስችል ብሔራዊ የዕርቀ ሰላም እና የውይይት መድረክ ተካሂዶዋል። የኮንጎ ፕሬዚደንት ዴኒ ሳሱ ንጌሶ በመሩት የድርድር መድረክ ላይ ውጊያ የቀጠሉት ተፋላሚ ቡድኖች እና የሀገሪቱ የሽግግር መንግሥት ተወካዮች ተሳታፊዎች ነበሩ። በብዛት የቀድሞ የሴሌካ ዓማፅያን ቡድኖች እና ተቀናቃኛቸው የክርስትያኖቹ ፀረ ባላካ ሚሊሺያዎች ተወካዮች በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሸምጋይነት በተካሄደው የድርድር መድረክ ላይ የተኩስ አቁሙን ስምመነት ፈርመዋል። በደንቡ መሠረት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ውጊያውን እና ማንኛውንም የኃይል ርምጃ ውሉ ከተፈረመበት ጊዜ አንስቶ ለማቆም ተስማምተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ተዋጊዎቻቸው በሲቭሉ ሕዝብ ላይ እየተፈፀሙት ያለውን የሰብዓዊ መብት በደል፣ የጅምላ ርሸና፣ ቁም ስቅል ማሳየት፣ ክትትል፣ መንደሮችን፣ የሕዝብ መገልገያ የሆኑውን የመንግሥት እና የግል ንብረት በእሣት ማጋየት፣ የእምነት ቦታዎችን ማውደም፣ ሕፃናትን ለውጊያ ተግባር መመልመልን እና ወሲባዊ ጥቃትን ለማብቃት እና ሚሊሺያዎቻቸውንም ወደየሠፈራቸው እንደሚመልሱ አረጋግጠዋል።

Brazzaville Versöhnungsforum 23.7.2014
ምስል Guy-Gervais Kitina/AFP/Getty Images

ይሁንና፣ የብራዛቪሉ ስምምነት የድርድሩ መድረክ ያስቀመጠውን ዓላማ ከማሟላት እጅግ የራቀ ሆኖ እንዳገኙት ነው ብዙዎቹ የፖለቲካ ታዛቢዎች የተናገሩት። የማዕከላይ አፍሪቃ ጉዳይ ተከታታይ የጠበብት ቡድን ዋና ፀሐፊ ዢል ፖቶሎ ለምሳሌ የጦር መሳሪያ ትጥቅ ተይዞ የኃይሉን ተግባር ለማቆም የሚደረስ ስምምነትን ትርጓሜ አጠያይቀዋል።

Symbolbild Verbrechen gegen die Menschlichkeit Zentralafrika
ምስል picture alliance/Yannick Tylle

« አሁን የተደረሰው የተኩስ አቁም ደንብ ወቅታዊ ሁኔታ የሚፃረር ይመስለኛል። የጦር መሳሪያ ትጥቅ ሳይፈታ እና የጦር መሳሪያህን ሁሌ በትከሻህ እንደያዝክ፣ በሀገሪቱ የቀጠለውን የኃይል ተግባር እና ግጭት ማስቆም መቻሉን በጣም እጠራጠረዋለሁ። ይህ በጣም የተወሳሰበ ዓቢይ ጉዳይ በመሆኑ ግን በጥሞና ሊታይ ይገባዋል። ስምምነቱ፣ በፍረማው ሥነ ሥርዓት ወቅት እንደተባለው፣ ሰላም ለማውረድ በተደረገው ሂደት ውስጥ የመጀመሪያው ርምጃ በመሆኑ፣ የሚመለከታቸው ሁሉ ወደ ሁለተኛው፣ ማለትም፣ የጦር መሳሪያ ትጥቅ ወደማስፈታቱ ርምጃ ባፋጣኝ እንደሚሸጋገሩ ተስፋ እናደርጋለን። »

ይሁን እንጂ፣ የቀድሞ የሴሌካ ዓማፅያን ቡድኖች ህብረት መሪ ዋና አዛዥ መሀመድ ሙሳ ዳፋ እና የፀረ ባላካ ቡድኖች አስተባባሪ ፓትሪስ ኤድዋርድ ንጌይሶና፣ እንዲሁም፣ በብራዛቪል የድርድር መድረክ የተሳተፉት እና በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ያስቀመጡት ወደ 40 የተጠጉት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሙያ ማህበራት፣ የሲቭል ማህበረሰብ ተወካዮች፣ እንዲሁም፣ የኮንጎ ፕሬዚደንት ዴኒ ሳሱ ንጌሶ፣ ሚሊሺያዎቹን ትጥቅ ማስፈታት እና ውሎ አድሮም የተቀናቃኞቹን ሚሊሺያ ቡድኖችን መበተን በሚያስችሉ ቅድመ ግዴታዎች ላይ ሳይስማሙ ነበር የቀሩት። ያም ቢሆን ግን፣ የዉሉን ፅናት ያረጋገጡት የቀድሞ ሴሌካ ዓማፅያን ቡድን ፕሬዚደንት ዳፋኔ ሀገራቸው የመከፋፈል ስጋት ተደቅኖባታል በሚል ብዙዎች የሚያሰሙትን ሀሳብ አይጋሩትም። ሆኖም፣ የትጥቅ ማስፈታቱ ርምጃ በሌላ መድረክ ሊነሳ እንደሚገባ አሳስበዋል።

Räumung der Muslime in der Zentralafikanischer Republik
ምስል ISSOUF SANOGO/AFP/Getty Images

« በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ውስጥ የቀጠለውን የኃይሉን ተግባር ለማቆም የደረስነው ስምምነት ፅኑ ነው። የሀገሪቱ ዜጎች በጠቅላላ አሁን በዓለም ካርታ ላይ በሚታየው የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ድንበር ላይ አንዳችም ለውጥ አይደረግበትም የሚል ተመሳሳይ አመለካከት እንጋራለን። ሚሊሺያዎችን የጦር መሳሪያ ትጥቅ ማስፈታትን የሚመለከተው ነጥብ በፖለቲካው ውል ሊካተት፣ እንዲሁም፣ በመዲናይቱ ባንጊ ያለው መንግሥት እና በሌሎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙት ታጣቂ ቡድኖች በጠቅላላ ትኩረት ሰጥተው ሊመክሩበት ይገባል ብለን እናስባለን። »

ፕሬዚደንት ሳሱ ንጌሶም የብራዛቪሉ ድርድር ሦስት ክፍሎች የያዘው የማዕከላይ አፍሪቃ ብሔራዊ የዕርቀ ሰላም እና የውይይት መድረክ የመጀመሪያው መሆኑን አመልክተዋል።

« የኃይሉን ተግባር በማስቆሙ መጀመር አለበት፣ ይህ ሰላም የማውረዱ ጥረት የመጀመሪያ ርምጃ ነው። የብራዛቪልም ድርድር የመጀመሪያው ርምጃ ነው። ይኸው የመጀመሪያ ርምጃ ያስቀመጠውን የብሔራዊው ዕርቀ ሰላም ውይይት በመዲናይቱ ባንጊ ከማደራጀታቹሁ በፊት በጠቅላላ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ውስጥ ሁሉን የሚያጠቃልል ምክክር ይካሄዳል። »

የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ጠቅላይ ሚንስትር ኦንድሬ ንዛፓየኬ የተኩስ አቁሙን ደንብ በቁጥብነት ሲያሞግሱ፣ ሌሎች የሙሥሊሞቹ የሴሌካ ዓማፅያን እና የክርስትያን ፀረ ባላካ ሚሊሺያዎች መካከል በቀጠለው ውጊያ ብዙ ስቃይ የደረሰባቸው ብዙዎቹ የሀገሪቱ ዜጎች እና ባለሥልጣናት ፣ ምንም እንኳን በይፋ ባይናገሩትም፣ ደንቡ መከበሩን መጠራጠራቸውን አስታውቀዋል።

Zentralafrikanische Republik Gewalt Bangui 02.02.2014
ምስል picture alliance/AP Photo

የባንጊ ጳጳስ ዲየዶኔ ንሳፓላይንጋ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ዜጎች ሀገራቸውን ወደ ሰላሙ መንገድ ለመመለስ በመስማማታቸው በማሞገስ፣ ርምጃቸው ሊበረታታ እና ሊጠናከር እንደሚገባው አስታውቀዋል።

« የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊካውያን ለሰላም ፀንተው እና እጅ ለእጅ ተያይዘው እንደሚሰሩ ተመልክተናል። አዳጋች የመሰለን ነገር አዳጋች አለመሆኑን አሁን የተገኘው ውጤት አሳይቶዋል። የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክን ሰላም የሚፈልጉ ሁሉ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሸምጋይነት አዎንታዊ ውጤት ላይ ደርሰዋል። ይህ ለዕርቀ ሰላሙ ሂደት ላይ የመጀመሪያው ርምጃ ነው። »

15 የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አባል ሀገራት በጋራ ባውጡት መግለጫ ተቀናቃኞቹ የሙሥሊሞቹ የሴሌካ ዓማፅያን እና የክርስትያን ፀረ ባላካ ሚሊሺያዎች በብራዛቪል የተደረሰውን ስምምነት ባፋጣኝ ተገባራዊ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ስምምነቱ በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ዘላቂ ሰላም፣ የሰብዓዊ መብት መከበርን ፣ ሲቭሉን ሕዝብ ደህንነት መከላከልን እና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ሲባል የተወሰደው የመጀመሪያ ርምጃ ብቻ መሆኑን በማስታወቅ በሀገሪቱ ዕርቀ ሰላም ማውረድ የሚያስችሉት ቀጣዮቹ ርምጃዎች ሳይዘገዩ እንዲከተሉ ጠይቀዋል።

አርያም ተክሌ

ልደት አበበ