1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ጊዚያዊ ሁኔታ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 11 2005

ከአምስት ወራት በፊት በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የተካሄደውን የመፈንቅለ መንግሥት የመሩት እና ራሳቸውን የሀገሪቱ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚደንት ብለው የሠየሙት ሚሼል ጆቶጂያ እአአ በነገው ዕለት ነሀሴ 18፣ 2013 ዓም ቃለ መሀላ ይፈፅማሉ።

https://p.dw.com/p/19RaX
Zentralafrikanische Republik mit der Hauptstadt Bangui und den Nachbarländern --- DW-Grafik: Peter Steinmetz
ምስል DW

ከመፈንቅለ መንግሥቱ ወዲህ ግን በዚችው ሀገር ውስጥ ምስቅልቅሉ ሁኔታ ነው የተስፋፋው። ከጆቶጂያ ቃለ መሀላ በኋላም በኋላ ግን ይህችኑ ከዓለም ድሆች ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችውን የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ብሩህ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንደማይጠብቃት ጊዚያዊ ሁኔታዎች አመላክተዋል።
ባለፈው እአአ መጋቢት 24 2013 ዓም አምሥት ያማፅያን ቡድኖች የፈጠሩት የሴሌካ ጥምረት ዓማፅያን የቀድሞውን የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ፕሬዚደንት ፍራንስዋ ቦዚዜን ከሥልጣን በማስወገድ በሚሼል ጆቶጂያ የሚመራ የሽግግር መንግሥት አቋቁመዋል። እአአ በ2003 ዓም በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የጨበጡት ቦዚዜ በዚያን ጊዜ ሀገር ለቀው ወደ ካሜሩን ሸሽተዋል። የሽግግሩ መንግሥት ከተቋቋመ ዛሬ ከአምስት ወራት በኋላም ግን በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ኤኮኖሚው ከመውደቁ ጎን፣ የተሰፋፋው ዝርፊያ፣ ግድያ እና ሴቶች የሚደፈሩበት ድርጊት በሕዝቡ ዘንድ ፍርሀት እና ጭንቀትን ማስከተሉን ለአንድ መንግሥታዊ ላልሆነ ያካባቢ ድርጅት የሚሰሩት ዠርቬ ላኮስ አስረድተዋል።
« በወቅቱ አመራሩን የያዘው የሽግግሩ መንግሥት እስካሁን አንድም ጥሩ ስራ አልሰራም። በሕዝቡ አንፃር እኩይ ተግባር የሚፈፀሙትን ወገኖች ፣ ማለትም የሴሌካ አባላትን ይደግፋል።
በተለይ በመዲናይቱ ባንግዊ በሲቭሉ ሕዝብ አንፃር ጥቃቱ መበራከቱን በሀምበርግ ከተማ በሚገኘው የላይፕኒትስ የዓለም አቀፍ እና የአካባቢ ጥናት ተቋም የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ተመራማሪ አንድሬያስ ሜለር ገልጸዋል።
« በጣም አሰከፊ ነው። በሀገሪቱ አሉ የሚባሉ ማህበራዊ ችግሮች በጠቅላላ ተባብሰዋል። በተለይ ያልተመጣጠነው አመጋገብ፣ የጤና ጥበቃ ዘርፍ መጓደል፣ ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት ሊሄዱ አለመቻላቸው፣ እነዚህ ችግሮች ሁሉ ተባብሰዋል። ከ 4,6 ሚልዮኑ የሀገሪቱ ሕዝብ መካከል 1,6 ሚልዮኑ አስቸኳይ ቀጥተኛ ርዳታ ያስፈልገዋል። »
ምንም እንኳን ሀገሪቱ አልማዝ፣ ወርቅ እና ዩሬንየምን በመሳሰሉ ማዕድናት ሀብት ብትታደልም፣ ከዓለም እጅግ ድሆች ሀገራት መካከል አንዷ ናት። በማዕከላይ አፍሪቃ ለሚታዩት በርካታ ችግሮች፣ አንድሬያስ ሜለር እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀሱት፣ የአምሥት ያማፅያን ቡድኖች በፈጠሩት የሴሌካ ጥምረት ውስጥ የሚታየውን ልዩነት ነው። ያማፅያኑ ጥምረት በመከፋፈሉ አንዱ ከሌላው ትዕዛዝ መቀበል አይፈልግም። በዚህም የተነሳ የሽግግሩ መንግሥት በሀገሪቱ የተስፋፋውን የኃይል ተግባር ማብቃት አልተሳካለትም። የሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚደንት ሚሼል ሁኔታውን ማረጋጋት የቻሉ ባይመስልም፣ በነገው ዕለት የሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚደንት ሆነው ቃለ መሀላ እንደሚፈፅሙ እና ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላም በሀገሪቱ ምርጫ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል። ይሁንና፣ ካለ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ርዳታ በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ምርጫ ማካሄድ መቻሉ አጠራጣሪ መሆኑን ነው አንድሬያስ ሜለር ያስታወቁት።
« ለዚሁ ተግባር ማሳኪያ ግዙፍ የቁሳቁስ ድጋፍ አስፈላጊ ነው። ባለፉት ጊዚያት ለምርጫ የሚያስፈልገውን ሁሉ አንድም የፈረንሣይ ጦር ወይም የተመድ ተልዕኮ ሲያቀርቡ ነበር ። እንግዲህ በጆቶጂያ ላይ ግፊቱን ለማጠናከር እና ከተቻለም እንዳይመረጡ ለማድረግ ከተፈለገ ይህንኑ የምርጫ ዕለት ማክበር ወሳኝ ነው። »
የተመድ የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ አስተባባሪ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ቫለሪ ኤሞስም ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ርዳታ ያስፈልጋታል በሚለው ሀሳብ ላይ ይስማማሉ። ኤሞስ ባለፈው ረቡዕ ስለ ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ጊዚያዊ ሁኔታ ዘገባቸውን ለተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ባቀረቡበት ጊዜ ስጋት የሀገሪቱን አንድነት ጠብቆ ለማቆየት እና የከፋ ሁኔታ እንዳይፈጠር ለመከላከል ከተፈለገ ለምሳሌ ባፋጣኝ ርምጃ እንዲወሰድ ነበር ያሳሰቡት። የአፍሪቃ ህብረት ወደዚችው ሀገር ሰላም አስከባሪ ጦር ለመላክ የወጠነው ዕቅድ ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን ነው ኤሞስ ያስታወቁት።
« የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ በርካታ ሀሳቦችን እንዲደግፍ ጠይቄአለሁ፣ ለምሳሌ አንዱ የአፍሪቃ ህብረት ወደ ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ አንድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ለመላክ መስማማቱ ነው። እና የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ይህንን አዲስ የተቋቋመውን ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ እንዲደግፍ ጠይቄአለሁ። »
የአፍሪቃ ህብረት ጊዜው በውል ባይታቅም ወደ 3,500 ወታደሮችን ወደ ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ መላክ ይፈልጋል። የተመድ ቀውስ ላዳቀቃት የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የሚሰጠውን በጀት ከፍ እንዲያደርግም ቫለሪ ኤሞስ ጠይቀዋል። የተመድ ዋና ፀሐፊ ፓን ኪ ሙንም የዚችኑ ሀገር ቀውስ ለማስወገድ አስቸኳይ ርምጃ መውስድ እንደሚገባ በማስታወቅ፣ ዝርፊያው፣ ግድያው እና ሴቶችን የመድፈሩ ተግባር ካላቆመ በዚችው ሀገር ላይ ማዕቀብ እንደሚጣል ዛቻ አሰምተዋል። ማዕቀቡ በተጨባጭ ምን እንደሚሆን ግን የፀጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ዝርዝር መግለጫ ገና አላቀረበም።
ናዲና ሽዋርስቤክ/አርያም ተክሌ
መሥፍን መኮንን

Seleka rebels pose in a vehicle left by South-African soldiers , on April 4, 2013 in a street of Bangui. South African President Jacob Zuma, facing a firestorm over the deaths of 13 soldiers in a coup in the Central African Republic, said on April 4, 2013 he was withdrawing troops from the restive nation.AFP PHOTO / PATRICK FORT (Photo credit should read PATRICK FORT/AFP/Getty Images)
ምስል Patrick Fort/AFP/Getty Images
©Serge Dibert/PANAPRESS/MAXPPP - 13/08/2013 ; ; Central African Republic - BANGUI - AUGUST 13: War guns burned at the square where takes place the celebration of the 53rd anniversary of the independence on August 13, 2013 in Bangui, Central African Republic. (Photo Serge Dibert /Panapress) - BANGUI - 13 AOUT: Un bucher d'armes de guerre brule sur la Place du Defile a l'occasion de la commemoration du 53e anniversaire de l'independance centrafricaine. Bangui, Centrafrique, 13 aout 2013. (Photo Serge Dibert /Panapress)
ምስል picture-alliance/dpa
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ