1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማዕድኑ አልማዝ ንግድ እና የኪምበርሊ ሂደት

ቅዳሜ፣ ኅዳር 5 2002

የአልማዝ ኢንዱስትሪ፡ መንግስታትና የሲቭል ማህበረሰቦች ከስድስት ዓመታት በፊት ባንድነት በደቡብ አፍሪቃዊቱ የኪምበርሊ ከተማ ተቀምጠው ከመከሩ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚካሄደው የአልማዝ ንግድ የሚገኘው ገቢ ለጦርነት ማካሄጃ እንዳይውል በመስማማት የኪምበርሊ ሂደት የተባለውን የመቆጣጠሪያ አውታር አቋቋሙ።

https://p.dw.com/p/KWZ4
የሲየራ ልዮን ዜጎች በአልማዝ ማዕድን ሲሰሩምስል AP

የኪምበርሊ ሂደት ለተቋቋመበት ርምጃ ዋነኛ ምክንያት የሆነው እአአ በ 1990 ኛዎቹ ዓመታት በሲየራ ልዮን፡ በላይቤርያ እና በአንጎላ የተካሄደው ጦርነት ነበር። በዚያን ጊዜ የተመድ የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት እአአ በ 1998 ዓም በአንጎላ ይካሄድ የነበረውን የርስበርስ ጦርነት ለማብቃትም በማሰብ፡ በመንግስቱ አንጻር ይዋጋ የነበረውን የዩኒታ ዓማጽያን ቡድንን አልማዝ ወደ ውጭ በንግድ እንዳይልክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከለከለ። ይሁን እንጂ፡ ዩኒታ ከአልማዝ ንግድ በሚያገኘው ገቢ ጦርነቱን በመቀጠሉ፡ በደቡባዊ አፍሪቃ የሚገኙ በርካታ የአልማዝ አምራች ሀገሮች እአአ በ 2000 ዓም ስለዚሁ ችግር ተወያዩ፤ እአአ በ 2003 ዓመተ ምህረትም የኪምበርሊን ሂደት በይፋ በማቋቋም፡ በዓለም ገበያ ላይ መቅረብ ያለበት ማዕድኑ አልማዝ ከየትኛው ሀገር እንደመጣ የሚያረጋግጥ ሰርፊኬት (ሰነድ) ያለው አልማዝ ብቻ መሆኑን አስታወቁ። አርባ ሰባት ሀገሮች፡ ከነዚህም ብዙ አልማዝ አምራች አፍሪቃውያት ሀገሮች የኪምበርሊ ሂደት አባል ሲሆኑ፡ ቡድኑ አባላቱ ሀገሮች የአልማዙን ምንጭ የሚያረጋግጠውን ሰነድ በትክክል፡ ካለ ሙስና ተግባር፡ መስጠት አለመስጠታቸውን የሚቆጣጠር አንድ ዓለም አቀፍ ቡድን መስርቶዋል።

በየጊዜው እየተሰበሰቡ በወቅታዊው የአልማዝ ንግድ ሁኔታ ላይ የሚመክሩት የኪምበርሊ ሂደት አባል ሀገሮች ተወካዮች ባለፈው ሳምንት በናሚብያ ባደረጉት ስብሰባቸው ላይ በአባል ሀገር ዚምባብዌ ውስጥ በሚታየው የሰብዓዊ መብት ረገጣ አንጻር ምን ዓይነት ርምጃ መውሰድ ይቻላል የሚሰኘውን ጥያቄ ዋነኛው የመወያያ አጀንዳቸው አድርገውት ነበር። አባል ሀገራቱ በዚሁ ጥያቄ ላይ አንድ አቋም መያዝ ሳይችሉ ነው የቀሩት።

የራሱ የኪምበርሊ ሂደት አባል መንግስታት የጠበብት ኮሚሽን፡ የዚምባብዌ አባልነት ለስድስት ወራት እንዲቋረጥ ሀሳብ አቅርቦ ነበር። ይሁንና፡ ይኸው ሀሳቡ ግን በስብሰባው ተካፋዮች ዘንድ ተቀባይነትን ሳያገኝ የቀረበት ድርጊት ታዛቢዎችን እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን አብዝቶ አስቆጥቶዋል። ዚምባብዌ ከሂደቱ አባልነት ለጊዜው ብትገለል ኖሮ በዓለም ገበያም ላይ የአልማዝ ምርትዋን መሸጥ ባልቻለች ነበር። ለውዝግቦች የመፍትሄ ሀሳብ የሚያፈላልግ የጀርመናውያን ተቋም ባልደረባ የሆኑት ቮልፍ ክርስትያን ፔስ ግን የዚምባብዌ አባልነት ለጊዜው ይቋረጥ የተባለበትን ሀሳብ የሚደግፍ በቂ ምክንያት አለ ብለው ነው የሚያምኑት።

« ከዚምባብዌ የማዕድን አካባቢዎች በዚህ በተያዘው ዓመት እጅግ አሳሳቢ የሆኑ ዘገባዎች ተገኝተዋል። በብዙ መቶ የሚገመቱ ሰዎች በፕሬዚደንት ሙጋቤ ጸጥታ አስከባሪዎች ሳይገደሉ አልቀሩም ነው የሚባለው። ይህ ለኛ ዚምባብዌን ከአባልነት ለማግለል የሚያስችል ሁነኛ ምክንያት ነው። »
ይሁንና፡ ብዙዎቹ የኪምበርሊ ሂደት ተወካዮች ከዚህ የተለየ አቋም ነው የያዙት። የአስተናጋጅዋ ሀገር ናሚቢያ ኬኔዲ ሀሙሴንያ የኪምበርሊ ሂደት ለዚምባብዌ ፖለቲካዊ ችግር ተጠያቂ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
« የኪምበርሊ ሂደት የሰብዓዊ መብትን የማስከበር ዓላማ ይዞ የተነሳ መድረክ አይደለም። ለዚህ የቆሙ ለምሳሌ፡ የተመድ ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤትን የመሳሰሉ ሌሎች ድርጅቶች አሉ። የደም አልማዝ ለሚለው አባባል ግልጹ ማብራሪያ ቀርቦዋል። ያማጽያን ቡድኖች አንድን በህጋዊ መንገድ የተመረጠ መንግስትን ከስልጣን ለማውረድ የሚጠቀሙበት አልማዝ ማለት ነው። ብዙዎች አሁን የሚሉት አልማዝ ግን ለንዲህ ዓይነቱ ውዝግብ አገልግሎት የሚሰጥ አይደለም። »
ቮልፍ ክርስትያን ፔይስ ይህን የ-መከራከሪያ ሀሳብ አርኪ ሆኖ አላገኙትም። በርስበርስ ጦርነት እና በሌሎች ውዝግቦች መካከል ልዩነት ለማድረግ የሚሞከርበት ሁኔታ ትርጉም አልባ ነው። ለርሳቸው ወሳኙ ሁሉም ለኃይሉ ተግባር መጠቀሚያ መዋሉ ነው።
« እርግጥ ነው የደም አልማዝ የሚለው ቃል ትርጉም ግልጽ አይደለም። የኪምበርሊ ሂደት በሲየራ ልዮን፡ በአንጎላ፡ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፑብሊክ ለተካሄዱት የርስበርስ ጦርነቶች ምላሽ ይሆናል ተብሎ የተቋቋመው ነው፤ በዚምባብዌ የሚታየው ሁኔታም የርስበርስ ጦርነት አይደለም። ይህም ቢሆን ግን፡ አሁን በዚምባብዌ ይፈጸማል የሚባለው የኃይል ተግባር ደረጃ ሲታይ አንድ ርምጃ መውሰዱ ተገቢ ይሆናል። ችግሩ ከቦትስዋና በስተቀር ሁሉም የዚምባብዌ ጎረቤት ሀገሮች ሀራሬ በሚገኘው መንግስት አንጻር ጠንካራ ርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ አለመሆናቸው ነው። »
የኪምበርሊ ሂደት ተወካዮች በናሚቢያው ስብሰባቸው ከዚምባብዌ ጎን መመልከት የነበረባቸው ሌሎች ተጨማሪ ችግሮችም ነበሩ። እአአ በ 2005 ዓም ኮት ዲቯር የቡድኑንን አባልነትዋን አብቅታለች። የኪምበርሊ ሂደት አባላት የአልማዙ ሽያጭ ገቢ ለርስበርሱ ጦርነት ማካሄጃ ሳይውል እንዳልቀረ አስረድተዋል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የኮት ዲቯር የአልማዝ ምርት አልቀነሰም፤ አልማዙ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከሀገር እንዲወጡ ይደረጋል። ለውዝግቦች የመፍትሄ ሀሳቦችን የሚያቀርበው ድርጅት ባልደረባ ፔይስ በኪምበርሊ ሂደት ዙርያ ሁለትዮሽ የሆነ አመልካከት ነው ያተረፉት።
« በዓለም ገበያ ላይ የሚሸጠው በህገ ወጥ መንገድ የሚወጣው አልማዝ መጠን ንዑስ ነው። መጠኑ እአአ በዘጠነኛዎቹ ዓመታት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በርግጥ ቀንሶዋል። ይሁን እንጂ፡ ችግሩ አሁንም ቀጥሎዋል። በርካታ ውዝግቦች ጥሩ ፍጻሜ አግኝተዋል፤ ግን በኪምበርሊ ሂደት የተነሳ አይደለም፤ ምክንያቱም፡ ይህ የተቋቋመው እአአ በ 2003 ዓም ነውና። በዚያን ጊዜ ብዙዎቹ ውዝግቦች በሌሎች ምክንያቶች አብቅተው ነበር። »
የኪምበርሊ ሂደት እንደሚጠበቅበት መስራት ይችል ዘንድ፡ ይላሉ የናሚብያን ስብሰባ በጥሞና የተከታተሉት ግሎባል ዊትነስ የሚባለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሃላፊ ወይዘሮ አኒ ዱነቤክ፡ መሰረታዊ ተሀድሶ ያሻዋል። አባል ሀገሮችም ድፍረት ያስፈልጋቸዋል።
« የፖለቲካው በጎ ፈቃድ ተጓድሎዋል። ይህ አንዳንዴ ከፖለቲካ ጋር፡ አንዳንዴም ከኤኮኖሚያዊ ጥቅም ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። በተለይ በውሳኔ አሰጣጡ ሂደት ላይ ተሀድሶ አስፈላጊ ነው። እስካሁን፡ ሁሉም ሲስማሙ ብቻ ነው ውሳኔ የሚወሰደው። ይህም የመሻሻል ሂደት ሊያስገኝ ይችል ይሆናል የሚባል ውሳኔ ተቀባይነት እንዳያገኝ ሊያግድ ይችላል ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪም የተላለፉ ውሳኔዎችን በትክክል መቆጣጠር የሚቻልበት አውታር መተከል ይኖርበታል። »
የዘንድሮው የኪምበርሊ አባል ሀገሮች ተወካዮች ስብሰባ ሂደቱ በትክክል የሚሰራ የመቆጣጠሪያ አካል ለመሆን ገና ብዙ እንደሚቀረው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ያምናናሉ። አልማዝ የሚገዙ ሰዎች በዚሁ ክብር ድንጋይ ውዝግቦችና የሰብዓዊ መብት ረገጣ የሚካሄድበት ሁኔታ ድርሻ እንደማያበረክቱ ዋስትና ለመስጠት ያስቀመጠውን የተነሳለትንም ዓላማ በሚገባ ከግብ አላደረሰም። በመሆኑም፡
የኪምበርሊን ሂደት ለማሻሻል በወቅቱ የተደረገው ጥረት የተጠበቀውን ውጤት ሳያስገኝ ነው የቀረው።

Diamantenfund in Südafrika
ምስል picture alliance/dpa
አርያም ተክሌ/ያን ሾልስ/ሳራ ካማራ