1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሜርክል የቻይና ጉብኝት

ሰኞ፣ ነሐሴ 21 1999

የቻይና የሰብዓዊ መብት አያያዝና ሁለቱ አገራት ከንግድ ግንኙነቶች በሻገር ግኙነታቸውን ሊያሰፉ የሚችሉበት መንገድ የውይይታቸው ትኩረት ነበር ።

https://p.dw.com/p/E87m
ሜርክልና ጅያባው ወታደራዊውን ሰልፍ ሲጎበኙ
ሜርክልና ጅያባው ወታደራዊውን ሰልፍ ሲጎበኙምስል AP

ቻይናን በመጎብኘት ላይ ያሉት የጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ከቻይናው ፕሬዝዳንት ሁ ጁንታው እና ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጅያባው ጋር በሁለቱ አገራት ልዩ ልዩ የጋራ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል ። ሜርክል ከፕሬዝዳንቱና እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ስለተወያዩባቸው ጉዳዮች ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች እንደሚናገሩት በቻይና የሰበዓዊ መብት አያያዝ ከቀድሞው የተሻለ ቢመስልም አሁንም በሀገሪቱ ብዙ ትኩረት ሊያገኙ የሚገባቸው የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች አሉ ።
የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጅያባው ለመራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል የወዳጅ አቀባበል ነው ያደረጉላቸው ። ። የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ጅያባው እንደተናገሩት የጀርመንና የቻይና ግንኙነት በጣም ጥሩ በሚባል ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው ። እንደ ጅያባው በሜርክል የስልጣን ዘመን የአገራቱ ግንኙነት ሻክሮም አያውቅም ። ይልቁንም ግንኙነቱ እያደገ መምጣቱን ነበር ጅያባው አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩት ።
« በግልፅ ልናገረው የምፈልገው ከሞላ ጎደል ለውጥ መምጣቱን ነው ። ግንኙነቱ ደግሞ ከመበላሸት ይልቅ እየተሻሻለ ነው የሄደው »
በዛሬው ዕለትም የሁለቱን አገራት ግንኙነት የሚያጠናክሩ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ስምምነቶች ተፈርመዋል ። ሜርክልና ጅያባው በተገኙበት ከተፈረሙት ስምምነቶች ውስጥ ታዋቂው የጀርመን ኩባንያ ታይሰንክሩፕ ናንዪንግ በተባለችው የቻይና ከተማ በአንድ መቶ ሀምሳ ሚሊዮን ዩሮ ሊገናባ ያቀደው የመኪና መለዋወጫ ማምረቻ ፋብሪካ ስራ ስምምነት ይገኝበታል ። በመንግስታቱ መካከልም አካባቢ ጥበቃን የተመለከተ የጋራ ስምነነትም ተፈርሟል ። ለዐዕምሮ ውጤቶች መደረግ የሚገባው ጥበቃና የየዓየር ፀባይ ለውጥም ሜርክልና ጅያባው ያካሄዱት ውይይት ማዕከላዊ ትኩረት ነበር ።
« በዛሬው ዕለት የምጣኔ ሀብት ግንኙነቶቻችንን ከማጠናከሩ በተጨማሪ የዐዕምሮ ውጤቶች ጥበቃ ጥያቄ እንዲሁም የምርቶችን ጥራት መጠበቅና በተመሳሳይ ሁኔታም የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ላይም ተነጋግረናል ። »
በአሁኑ ሰዓት ከባቢ አየርን ከሚበክሉት አገራት በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀሰው ቻይና ናት ። ይሕችው አገር እጅግ በከፋው የከባቢ አየር ብክለት ተጎጂም ናት አሁን ። ከወንዞችዋ ከሰባ በመቶ በላይ የሚሆኑት ከመጠን በላይ ተበክለዋል ። ይሁንና የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ጅያባው ቻይና ወደፊት ከአሁኑ በበለጠ ለአየር ፀባይና ለአከባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ትኩረት ለመስጠት ዝግጁ ናት ብለዋል ። ሜርክልም በበኩላቸው ለቻይና በሰጡት ምክር ቻይና በኢንዱስትሪ የበለፀጉ አገራት ከዚህ ቀደም የሰሩትን ስህተት መድገም አይኖርባትም ። መጀመሪያ አካባቢን በክለው ከዚያ በኃላ የተበላሸውን ለማስተካከል አሁን እንደሚያደርጉት ሙከራ ማለታቸው ነው ። ከዚህ ሌላ ጅያባው በተለይ ከኢንተርኔት ሰነዶችን በሚዘርፉ ወንበዴዎች ላይ ቻይና ከጀርመን ጋር እንደምትተባበር ተናግረዋል ። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጅያባው መንግስታቸው ይህን መሰሉን ውንብድና የሚያራምዱ ሰዎች ላይ ዕርምጃዎችን ይወስዳል ። ቀደም ካሉት ዓመታት አንስቶ ቻይና በሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉድለት እንደተተች ነው ። ሜርክል ከቻይና መሪዎች ጋር ባካሄዱት ውይይት ላይም የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ማንሳታቸውን ጠቅሰዋል ። በተለይ የሁለት ሺህ ስምንቱ የቤይጂንግ ኦሎምፒክስ በተቃረበበት በአሁኑ ሰዓት ዓለም የቻይናን ሰብዓዊ መብት አያያዝ በንቃት እንደሚከታተለው ነው ሜርክል ያስገነዘቡት ። በአሁኑ ሰዓት ስለ ቻይና የሰብዓዊ መብት ይዞታ አስተያየታቸውን የተጠየቁት በጀርመን ህግ መምሪያ ምክርቤት የሰብዓዊ መብትና የሰብዓዊ ዕርዳታ ኮሚቴ ሊቀመንበር የቀድሞዋ የጀርመን የፍትህ ሚኒስትር ሄርታ ዶይብለር ግሜሊን የቻይና
የሰብዓዊ መብት አያያዝ ብዙ ይቀረዋል ባይ ናቸው ።
« የቤይጂንግ የስልጣን አቻዎቻቸውንም ሆነ ከዛም አልፎ በየክፍላተ ሀገራቱ የሚሰሩትንም የግል ነፃነትንና የዜጎች መብትን በተመለከተ ብዙ መሰራትና መሻሻል ያለበት መሆኑም አያጠራጥርም ። የአንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ዜጋ መታሰር ከዚህ ውስጥ የሚካተት ነው ። ወይዘሮ ሜርክልም ስለዚህ ጉዳይ ማንሳት አለባቸው ።