1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምሥራቅ ጀርመን ሳይንቲስቶች ፈተናና የሠመረ ዕድል በ 20 ዓመት የውህደት ታሪክ፣

ረቡዕ፣ መስከረም 19 2003

«ከአያያዝ ይቀደዳል ከአነጋገር ይፈረዳል» እንዲሉ መጥፎም ሆነ አስከፊ አመራር ወይም አያያዝ ያለፍላጎቱ የህዝብን ልብ ያስሸፍት ይሆናል። አያያዙን ያወቁበት በተለያዩ ሳንኮች ምክንያት ያጡትን መልሰው ያገኙታል ።

https://p.dw.com/p/PQ1x
ምስል DW-TV

የጀርመን የሶሺያል ዴሞክራቱ ፓርቲ መሪና የኖቤል ሰላም ተሸላሚ የነበሩት ታዋቂው መራኄ-መንግሥት፣ ቪሊ ብራንት እ ጎ አ ኅዳር 10 ቀን 1989 ዓ ም፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሳቢያ ተከፋፍለው ስለነበሩት ምሥራቅና ምዕራብ ጀርመን የማይቀር መልሶ ውህደት ሲናገሩ፣ «አንድ የሆነ አብሮ በአንድነት ያድጋል» የሚል ታሪካዊ ንግግር ማሰማታቸው አይዘነጋም ። ብዙ አልቆየም፣ በዓመቱ ምሥራቅና ጀርመን እንደገና ተዋኻዱ። በተለያዩ ሥርዓቶች ተለያይቶ ለኖረው አንድ ህዝብ የመዋኻዱ ሂደት ከፈተና ነጻ እንዳልነበረ ቢታወቅም፣ ለየሙያውና ምርምር ዘርፉ አዲስ በር መከፈቱና ። ዕድሉም መሥመሩ አልቀረም። ጤናይስጥልኝ እንደምን ሰነበታችሁ? በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን፣ ያለፉትን 20 ዓመታት የጀርመንን የሳይንስ ተቋማት ውህደትና ተኀድሶ ይሆናል የምንቃኘው።

(ሙዚቃ)

በሌሎቹ ዘርፎች እንደታየው ሁሉ፣ የምሥራቅ ጀርመን ሳይንስ ተቋማትና ሳይንቲስቶች፣ መልሳ በተዋኻደች ጀርመን ውስጥ ትክክለኛ ቦታቸውን ለማግኘት መታገል ነበረባቸው። ለአንዳንዶቹ በጣም ቀላል ነበረ። በተለይ ለወጣት ሳይንቲስቶች! በመሠረቱ ምሥራቅና ምዕራብ ጀርመን የነበራቸው ልዩነት በፖለቲካ ሥርዓት፣ በኤኮኖሚ መርኅ፤ በገንዘብና በመሳሰለው ይሁን እንጂ ፣ ሳይንሱ አንዳች ልዩነት እንዳልነበው የታወቀ ነው። ውህደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ፤ የምዕራብ ጀርመን መንግሥት አማካሪ አካል፤ «የሳይንስና «ሁማኒቲ» ምክር ቤት፣ የምሥራቅ ጀርመን የምርምር ተቋማት የቱን ያህ ል የተሟሉ ተፈላጊ ቁሳቁሶች እንዳሏቸው ይ,ፈትሽ ዘንድ ኀላፊነት ተሰጠው። አሁን በዩናይትድ እስቴትስ YALE ዩኒቨርስቲ የሚገኙት ፤ ምዕራባ ጀርመናዊው የማኅበራዊ ኑሮ ጥናት ሊቅ Karl Ulrich Mayer ለዶቸ ቨለ ራዲዮ በሰጡት ቃል ምልልስ ላይ እንዳብራሩት፣ እ ጎ አ ጥቅምት 3,ቀን 1990 ዓ ም ውህደቱ በይፋ ከተከናወነበት ጊዜአንስቶ በቀጠሉት ጊዜያት የተዘጉት የምርምር ተቋማት ጥቂቶች አልነበሩም። የተዘጉበት ምክንያት ፤ በአመዛኙ፣ ተቋማቱ ፤ የፓርቲ መስመር ተካታዮች ናቸው ተብለው ነበር።

Karl Ulrich Mayer በአሁኑ ጊዜ በተጨማሪ ፣ በመላይቱ ጀርመን ፣ የቀድሞዎቹን የምሥራቅ ጀርመን የሳይንስ ምርምር ጣቢያዎች ጨምሮ፣ በአጠቃላይ 86 የምርምር ተቋማትን የሚያጠቃልለው፣ የ ላይብኒትዝ ማኅበር ፕሬዚዳንትም ናቸው። ከታወቁት የላይብኒትዝ ተቋማት መካከል አንዱ፤ ከ ላይፕትዚግ ወጣ ብሎ የሚገኘው በዕፅዋት ሥነ-ህሽወትና ቅመማ ላይ ያተኮረው ማእከል ነው። በውህደቱ ማግሥት፤ ምሥራቅ ጀርመን ውስጥ፤ ከተለያዩ የተፈጥሮ ሳይንስ ምርምር ዘርፎች ሳይቀር ቁጥራቸው የተቀነሰ የተባረሩም እንደነበሩ አልታበለም።

ለምሳሌ ያህል ፤ በቲሪንጊያ (ቱዑሪንገን)ፌደራል መስተዳድር የሚገኘውን የየናውን የሳይንስ ተቋማቱን አከደሚ መጥቀስ ይቻላል። በዚያ የምርምር ማእከል በ«ፔንስሊን»ዙሪያ የተሠማሩ 1,000 ያህል ተመራማሪዎች እንደነበሩ ሲታወቅ ወዲያው ነበረ ቁጥራቸው ወደ 550 ዝቅ እንዲል የተደረገው። ቀሪዎቹ 550 ደግሞ፣ በሁለት የላይፕኒትዝ የምርምር ተቋማትና አንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች እንዲሠማሩ ነበረ የተደረገው።

አንዳንድ የምሥራቅ ጀርመን የምርምር ተቋማት በምዕራብ ጀርመን የተለያዩ የሳይንስና ሥነቴክኒክ ተቋማት እንዲጠቃለሉ ሲደረግ፤ ይህን አልሞክረውም ያለ የ ማክስ ፕልንክ ተቋም ወይም ማኅበር ነበረ። ይሁንና በምሥራቅ ጀርመን አዳዲስ የምርምር ተቋማት እንዲገነቡ ማገዙ አልቀረም።

የጀርመን ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ በመባል ይታወቅ የነበረው በምሥራቅ ጀርመን ተመሥርቶ እ ጎ አ እስከ 1989 ዓ ም ጸንቶ የቆየው መንግሥት፤ በሥነ-ቅመማ፤ ሥነ-ህይወታዊ ሥነ-ቴክኒክ፤ እንዲሁም በኑክልዮር ሳይንስ ላይ የላቀ ትኩረት ያደርግ ነበር። የአቶም ሥነ ቴክኒኩን ጥበብ ከቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ነበረ የሚያገኘው። በተፈጥሮ የምርምር ሳይንስ ላይ ያተኮሩ የጥናት ውጤቶች፤ በምዕራባውያን መጽሔቶች የመታተም ዕድል ያገኙ ነበር። የማኅበራዊ ሳይንስ ጥናት ነክ ጽሑፎች ግን፤በርሊን ውስጥ፤ በማክስ ፕላንክ ተቋም የሳይንስ ታሪክ ባልደረባ ዲተር ሆፍማን እንደሚሉት ፣ እጅግ ከባድ ነበረ። የግንቡ አጥር ከመፍረሱ በፊት ፣ ሆፍማን፤ በምሥራቅ ጀርመን የሳይንስ አካዳሚ በተለይም ፣ የነባቤ- ቃልና የሳይንስ ታሪክ ተቋም ውስጥ ይሠሩ ነበር። ሆፍማን እንደሚያስረዱት፤ «ያኔ፣ በምዕራባውያን መጽሔቶች ማሳተም አይቻልም ነበር። ወደ ምዕራብ በመጓዝ፣ ባልደረቦችን መጎብኘት ወይም በጉባዔዎች መሳተፍ ፤ የሳይንሳዊ ምርምር ውጤቴንም በአደባባይ ማቅረብ ፈጽሞ የሚቻል አልነበረም።»

በዚያ ዘመን፣ ምሥራቅ ጀርመን ውስጥ፣ የፓርቲውን የአመራር መሥመር የማይከተሉ ወይም የያኔውን ፈላጭ ቆራጭ የአንድ ፓርቲ መንግሥት፣ የሚነቅፉ ናቸው ተብለው ይጠረጠሩ የነበሩ ሳይንቲስቶች፣ ሥራቸው ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግበት ነበረ። አለበለዚያም እንዳይታተም ይታገዳል። ያም ሆኖ በአንዳንድ ረገድ ወጣት ሳይንቲስቶችን የሚጠቅሙ አንዳንድ ሁኔታዎች እንደነበሩ ይነገራል።

ሂልደጋርድ ማሪያ ኒከል ምሥራቅ ጀርመን ውስጥ፣ የማኅበራዊ ኑሮ ምሁር ሆነው በትምህታዊው የሳይንስ አካዳሚ ባልደረባ በመሆን ሠርተዋል። እርሳቸውም በምሥራቅ ጀርመን ተወልጄ ባልድግ ኖሮ፣ ፕሮፌሰር የመሆን ዕድል አላገኝም ነበረ ይላሉ። 8 ልጆች ካሉት ሠርቶ አደር ቤተሰብ የተወለዱት ሂልደጋርድ ማሪኢ ኒከል፤ በቀድሞዋ የጀርመን ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ፤ ሴቶች ከወንዶች እኩል ለመማርም ለመሥራትም ዕድሉ ነበራቸው። ይህ በጎ ጎኑ ነው ቢባልም፤ የምርምር ውጤትን የሚፈትሽ ሥርዓት ስለነበረ የሚያስደሥት አልነበረም። በ 1970 ዎቹና በ 1980 ዎቹ ዓመታት በሚገባ የተከናወኑ የወጣቱን ትውልድ ፍላጎት የሚያንጸባርቁ፤ አገሪቱን ለቆ መውጣት ፍልጎታቸው መሆኑንም የሚጠቁሙ ጥናቶች ቀርበው ነበረ። ምንም ለማወቅ የፈለገ አልነበረም ልናሳትመውም አልቻልንም፣ ይላሉ-- ኒኬል።

የግንቡ አጥር ሲፈርስ፤ ኒኬልና ሆፍማን፤ በተዋኻደችው ጀርመን ሥራ ማግኘት አልተሳናቸውም። በቀላሉ፣ ካገር- አገር መዘዋወር፣ ሥራዎቻቸውንም ማሳተም አላዳገታቸውም። በዕድሜ ጠና ያሉት ግን ፤ ከሥራ መሰናበት አለበለያም የነበራቸው ደረጃ ዝቅ ማለቱ አልቀረም። ሆፍማን እንዳብራሩት፤ አንዳንድ ምሥራቅ ጀርመናውያን ያኔ አስቀድመው ያለዕድሜ ጡረታ መውጣት የመረጡ ነበሩ። ምርምራቸውን በአካባቢያቸውም ሆነ ፈንጠር ብለው ማካሄድ አልቻሉም። ሥራ እስከማጣት የደረሱም ነበሩ። በሳይንሱ ዘርፍ ተሠማርተው ከነበሩትና ወዲያውኑ በምዕራብ ጀርመን ሥራ ካገኙት ምሥራቅ ጀርመናውን መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት፤ የአሁኗ የአገሪቱ መራኂተ-መንግሥት ዶ/ር አንጌላ ሜርክል ናቸው። በፖለቲካው መስክ ከመሠማራታቸው በፊት፤ ምሥራቅ በርሊን ውስጥ ፣ በፊዚክስና ሥነቅመማ ክፍል ምርምርና ሥራ ላይ ያተኮሩ በዚያም የዶክተርነት ማዕረጋቸውን ለማግኘት የበቁ መሆናቸው የታወቀ ነው።

ጀርመን በፈጠራ ውጤቶች የምትመካ አገር እንደመሆንዋ መጠን፣ ለሳይንስ ምርምር ዐቢይ ግምት ነው የምትሰጥ። ከብዙዎቹ ተቋማት አንዱ የማክስ ፕላንክ የምርምር ማእከል ሲሆን እርሱ ብቻ፤ 80 የምርምር ቅርንጫፎች እንዳሉት የታወቀ ነው። እ ጎ አ በ1948 ዓ ም፤ ከተመሠረተ ወዲህ 17 የዚሁ ተቋም ባልደረቦች የኖቤል ተሸላሚዎች ለመሆን በቅተዋል። የላብኒትዝ ተቋም ደግሞ በመላይቱ ጀርመን 86 ቅርንጫፎች አሉት። የጀርመን የምርምር ማኅበር ፕሬዚዳንት ማትያስ ክላይነር በበዘንድሮው የላይብኒትዝ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲህ ማለታቸው ይታወሳል።

(«በላይብኒትዝ ሽላማት በኩል፣ ከፍተኛ ምርምር እንዲካሄድ መገፋፋቱ፤ ከ 25 ዓመታ በፊት በጀርመን ለሳይንስ ትልቅ ነጻነት ነበረ ያጎናጸፈው። ይህም በ 1970 ኛዎቹና በ 1980ኛዎቹ ዓመታት ፤ ከዩኒቨርስቲዎች ይጠበቅ ከነበረው ንዑስ ውጤት ይህኛው እመርታ ያሳዬ ነው።»)

የምሥራቅና ምዕራብ ጀርመንን የምርምር ተቋማት ለማዋኻድ ከባድ ሂደት እንደነበረ ባይካድም ሆፍማን እንዳስረዱት በተዋካደችው በዛሬዋ ጀርመን ሥፍር ቁጥር የሌላቸው የሚያጓጉም የምርምር ጣቢያዎችም ሆኑ ማእከላት ይገኛሉ።

እዚህ ላይ ፣ ሊካድም የማይገባው በቀድሞይቱ የጀርመን ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ በቱዑሪንገን የምትገኘው የና፤ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ፣ አቅርቦና አጉልቶ ማሳያ መነጽሮችን በመሥራት በዓለም ውስጥ የመሪነቱን ሥፍራ ይዛ የቆየች መሆኗ ነው። ካርል ዛይስ፣ ሾትና የንኦፕቲክ የተባሉት እውቅ ኩባንያዎች የሚገኙትም በየና ነው። የሳክሰኒ መዲና ድሬስደን በቁሳዊ የሳይንስ ዘርፍ የተወቀች ናት ። በዚያው በሳካሰኒ የምትገኘው ከተማ ፍራይበርግም የፀሐይን ኃይል ማጥመጃ ቁሳቁሶች በማምረት ሥም ያተረፈች ናት።

በበርሊን የተመሠረተው የማክስ ቦርን ተቋም የተሰኘው የጨረር ፊዚክስ ማእከልም፣ በዓለም ውስጥ እጅግ ከታወቁት መካከል አንዱ መሆኑ አልታበለም።

በምሥራቅና በምዕራብ ጀርመን መካከል የነበረው የኑሮ ደረጃ ልዩነትም ባለፉት 20 ዓመታት ገደማ እየጠበበ በመምጣት ወደ መስተካከሉ ላይ ነው። «አንድ የሆነ አብሮ በአንድነት ያድጋል» ተብሎ የተነገረው ራእይም እውን እየሆነ ነው።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ