1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 የምርጫ ቦርድ አባላት ጥቆማ እና የምርጫ ዝግጅት

ረቡዕ፣ ግንቦት 14 2011

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ከትናንት ጀምሮ እጩ የቦርድ አባላት ጥቆማ መጀመሩን ይፋ አድርጓል። ከሳምንታት በፊት የተወካዮች ምክር ቤት ባጸደቀው አዲስ የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ከተጠቆሙት እጩዎች ተመርጠው በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት የተወካዮች ምክር ቤት ያጸድቃል።

https://p.dw.com/p/3IuYu
Äthiopien Wahlen 2015
ምስል DW/E. Bekele

የእጩዎች ጥቆማ እስከ ግንቦት 22/ 2011ድረስ ይዘልቃል

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቦርድ አባልነት የሚመረጡ ግለሰቦችን የሚለምል ኮሚቴ ትናንት ይፋ ባደረገው መሠረት የእጩ አባላቱ ጥቆማ እስከ የፊታችን ግንቦት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ይዘልቃል። በተሻሻለው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መልሶ ማቋቋሚያ ሕግ መሠረትም ከዚህ ቀደም ዘጠኝ የነበረው የቦርዱ አባላት ቁጥር ወደ አምስት ዝቅ እንዲል ተደርጓል። ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከታዋቂ ግለሰቦች እና ከመሳሰሉት የተዋቀረው ኮሚቴ ነው ለምርጫ ቦርድ አባልነት የታጩትን ሰብስቦ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርበው። ይህ ከዚህ በፊት ያልተደረገ አዲስ አሠራር መሆኑን ለዶይቼ ቬለ (DW) የገለፁት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ ወይዘሪት ሶልያና ሽመልስ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት የተወካዮች ምክር ቤት እጩዎቹን እንደሚያጸድቅም አስረድተዋል። 
የምርጫ ቦርድ አባላትን የመምረጡ ሥራ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኃላፊነት እንዳልሆነ ያመለከቱት ወ/ሪት ሶልያና በአዲሱ ሕግ መሠረት አዳዲስ የምርጫ ቦርድ አባላት መሾማቸው እስከ ዛሬ ውሳኔ ሳያገኙ ለቆዩ ጉዳዮች መልስ ያስገኛል ይላሉ።
«ምርጫ ቦርድ ጋር ሊደረግ የነበረው አንደኛው ለውጥ በአጠቃላይ ሕጉ መውጣቱ ነበር። ሁለተኛው ለውጥ ደግሞ በዚያ ማሻሻያ መሠረት አዳዲስ አባላትን መሾም ነው። ስለዚህ ሁለተኛው ደረጃ ላይ ነው ያለው ማለት ነው። በአጠቃላይ ለምርጫ ቦርዱ ሥራ አዳዲስ የቦርድ አባላት መሾማቸው እስካሁን ሳይወሰኑ የቆዩትን የምርጫ ማካሄጃ ጊዜ፤ የተለያዩ የፖሊሲ እና የፖለቲካ ውሳኔዎች ሳይወሰኑ የቆዩት፣ ያልተሟላ ቦርድ ስላለ ስለሆነ እሱን ለማድረግ በጣም ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል።»
አሁን ሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት መሠረት በኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል። የምርጫ ቦርድ አባላት በአዲስ መልክ የማዋቀሩ ሥራ ተጀመረ እንጂ ገና አልተጠናቀቀም። "አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ ያሉት ቀሪ ጊዜያት በቂ ናቸው ወይ?" ከሚለው ሌላ በፖለቲከኞች መካከል በህገ መንግስቱ ላይ እንኳ የጋራ መግባባት ገና እንዳልተደረሰ የፖለቲካ ተንታኞች ያመለክታሉ። የምርጫ ቦርድ አባላት የመምረጥ እና የመሰየሙ ሂደትን ጨምሮ ዝግጅቱ በራሱ ጊዜ የሚወስድ መሆኑን ያመለከቱት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ጥናት ተቋም ባልደረባ የሆኑት የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አበበ አይነቴ ያም ቢሆን እንኳ ምርጫው በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በመካሄዱ ላይ የጋራ መግባባት እንደሌለ ይናገራሉ።
«በአጠቃላይ በተለያዩ የፖለቲካ ምሁራን እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በኩል ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ሰሌዳ መሠረት መካሄድ የለበትም የሚል እና መንግሥትን ጨምሮ ምርጫው መካሄድ አለበት የሚለው አስተሳሰብ ጎልቶ እንደወጣ ይሰማል። እናም በዚህ ላይ የጋራ መግባባት አልተፈጠረም። እሱ ባልተፈጠረበት ሁኔታ የምርጫ ዝግጅት ሂደቱ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ከወዲሁ ለማየት እና ለመገመት አስቸጋሪ ነው።» 
ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄዱት ምርጫዎች ውጥረት የበረታባቸው እንደነበሩ ይታወሳል። አሁን ባለው የምርጫ ቦርድ ዝግጅትም ሆነ የመረጋጋት ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ አስፈላጊዎቹ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተዋል ማለት ይቻል ይሆን? የፖለቲካ ተንታኙ ምርጫ ማካሄዱንም ሆነ አለማካሄዱን አስቸጋሪ ይሉታል።
«የምርጫ ዝግጅት ሂደት የሚባለው የመጀመሪያው በሀገሪቱ የሕግ የበላይነት ሲኖር፣ ትንሽ በተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የሚታሰብ ነገር ነው። የሕግ የበላይነት የሚባለውን ነገር ትንሽ የቅንጦት ያህል አድርገን ብንወስድ እና የመጨረሻ የመንግሥት ኃላፊነት የሚባለው ዜጎች ያለምንም ስጋት፣ ያለምንም ፍርሃት፣ ያለምንም መሸማቀቅ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸው ባልተከበረበት ሁኔታ በአንድ መልኩ ስለምርጫ ማሰብ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። በሌላ መልኩ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ምርጫውን አለማካሄድ ሀገሪቱን ወደሌላ አይነት የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ሊወስዳት ይችላል። ወይ ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊወስዳት ይችላል፤ ወይም አሁን በየቦታው እየተነሳ ያለውን ሥርዓተ አልበኝነት እና በጎበዝ አለቃ ሀገሪቱን ለመምራት የሚደረገውን ጥረት የበለጠ ሊያወሳስበው ይችላል።»
እንዲህ ካለው ሁኔታ ለመውጣት ደግሞ ቢያንስ ከእነድክመቱም ቢሆን ያለውን ሕገ መንግሥት መቀበል እና በቀጣይ የሚመሠረተው መንግሥት ሀገሩን በሕግ እንዲመራ ማመቻቸት እንደሚገባም ሃሳባቸውን ሰጥተዋል። ሕገ መንግሥቱ እንዲለወጥ የሚጠይቁ ወገኖች በሂደት ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ አምነው የጋራ መግባባት በሌለበት ግን ስለምርጫ ማሰቡ በራሱ አስቸጋሪ እንደሚሆንም አመልክተዋል። 

Karte Äthiopien englisch

ሸዋዬ ለገሠ

ተስፋለም ወልደየስ