1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ተቃውሞ እና የመዋዕለ-ንዋይ ጥፋት

ረቡዕ፣ ኅዳር 6 2010

የኢትዮጵያ መንግሥት ለአገሪቱ ደሕንነት ምክር ቤት ያቀረበውእና ሾልኮ ወጥቷል የተባለው ሰነድ እንደሚጠቁመው በአገሪቱ "የውጭም ሆነ የውስጥ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ እና መዳከም" ታይቷል። ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ የአገር ጎብኚዎች ቁጥር "በከፍተኛ ደረጃ" መቀነሱን፣ "በርካታ ቤቶች እና ንብረቶች መውደማቸውን" ሰነዱ አክሎ አትቷል።

https://p.dw.com/p/2nhar
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Englisch

ተቃውሞ እና የመዋዕለ-ንዋይ ጥፋት

አቶ ይኩኖአምላክ ይልማ ባለፈው ሳምንት በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አረርቲ ከተማ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እንዴት ወደ ትንሺቱ ባልጪ ተስፋፍቶ ፋብሪካ እስከ ማቃጠል እንደ ደረሰ አልተገለጠላቸውም። አቶ ይኩኖአምላክ ይልማ በተቃውሞው በተቀሰቀሰ ቃጠሎ ጉዳት የደረሰበት የሚን ሰን የእንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ 48 % ባለቤት የሆነው የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ ኃላፊ ናቸው።  "ፋብሪካው ከፍተኛ ጉዳት ነው የደረሰበት።" የሚሉት ኃላፊው "ለገበያ ያዘጋጀው ወደ 8,000 ሜትር ኩዩብ ቬነር ተቃጥሏል። በአውሮጳ የጥራት ደረጃ ያመረታቸው ሶስት ኮንቴነር ከሰሎች ተቃጥለዋል። ፋብሪካው አካላዊ ክፍሎ ባይነካም ተያያዥ አካሎቹ በሙቀቱ እና በእሳቱ ወላፈን ምክንያት ተቃጥለዋል።" ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ከወደ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የተሰማው ተቃውሞ ድንገተኛ ነበር። በተቃውሞው ጉዳት የደረሰበት የሚን ሰን የእንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የተመሰረተው በ2008 ዓ.ም. ነው። የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ 48% ቻይናውያን ባለሐብቶች ደግሞ 52% ድርሻ አላቸው። በ80 ሚሊዮን ብር የተቋቋመው ፋብሪካው የባሕር ዛፍ ግንድን በቀጭኑ እየላጠ ጣውላ ያመርታል። 136 ቋሚ 100 ጊዜያዊ ሰራተኞችም ነበሩት። ምርቶቹን በአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚፈልጉ ደንበኞቹ ያቀርባል።

"ሰልፉ የራስን ስሜት ለመግለፅ ኤሌክትሪክ አጣን መሰረታዊ {አገልግሎቶች} አልተሟሉልንም የመልካም አስተዳደር ችግራችን ይፈታ" የሚለው የተቃውሞ ጥያቄ አቅጣጫውን የቀየረው ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ይኩኖአምላክ "ቻይናዎቹ ተሸማቀዋል። ተበሳጭተዋል። አሁን ፋብሪካውን ጠግነው ወደ ሥራ እንዲገቡ ድርድር ላይ ነው ያለንው።" ሲሉ ያክላሉ።

አቶ ይኩኖአምላክ ፋብሪካው ለአካባቢው ነዋሪ የሥራ እድል ፈጥሯል፤ የአካባቢውንም የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ አነቃቅቷል ይበሉ እንጂ ከወደ አረርቲ ግን ጠጠር ያለ ቅሬታ ይደመጣል።

"ከዚህ ፋብሪካ የዚህ ወረዳ ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እስካልሆነ ድረስ አያስፈልገንም" የሚል አስተያየት በተቃዋሚዎች ዘንድ መደመጡን የአረርቲ ከተማ ነዋሪ ተናግረዋል። "እዚህ አካባቢ ላይ አንድ ፋብሪካ ሲመሰረት የአካባቢውን ወጣት ወደ ሥራ የማስገባት" ቀዳሚው ዓላማ ሊሆን ይገባል የሚሉት ተቃውሞውን በቅርበት የተከታተሉት የአይን እማኝ ያክላሉ። እርሳቸው እንደሚሉት በፋብሪካው የተቀጠሩ ወጣቶችም ቢሆን የሚከፈላቸው በቂ አይደለም። ሸንኮራዎችን ወደ አረርቲ አደባባይ እንዲያመሩ የገፋቸው ፋብሪካ እስከ ማቃጠልም የገፋቸው ግን ይኸ ብቻ አይደለም።

የምንጃር ጥያቄ

በአማራ ብሔራዊ ክልል የሚገኘው የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የጤፍ አገር ነው። ስንዴ፣ ድቤ ሽንብራ፣ ማሾ እና ሽንኩርት ጭምር ያመርታል። ከበርካታ አመታት ማንቀላፋት በኋላ መነቃቃት ያሳየችው የወረዳው ዋና ከተማ አረርቲ የመብራት መቆራረጥ ግን ነዋሪዎችን ማማረር ከያዘ ከራርሟል። "መብራት ከገባ በግምት አምስት አመት ስድስት አመት ይሆነዋል። የትም የኢትዮጵያ ክፍል መብራት ይጠፋል። እናቃለን። ግን አረርቲ ምንጃር ላይ ይለያል።" የሚሉት የአካባቢው የአካባቢው ነዋሪ ተዳፍኖ የቆየ ጥያቄን የቆሰቆሰው ይኸው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ነው ባይ ናቸው።

ሌላ የአካባቢው ነዋሪ እንደሚናገሩት ከኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት መቆራረጥ ባሻገር አስተዳደራዊ በደሎች እና በገበያው ላይ የሚታየው የመሰረታዊ ሸቀጦች እጥረት ዜጎችን ወደ ምሬት እና ተቃውሞ መርተዋል።

"የስኳር አቅርቦት የለም፤ የዘይት አቅርቦት የለም። ቆይቶም እንኳ ሲመጣ ለቤተሰብ እንኳ በቂ ያልሆነ ሥርጭት ነው የሚካሔደው። ያ ነገር ሕዝቡ እንዲሰላች እንዲመረው አድርጎታል።" የሚሉት የአረርቲ ከተማ ነዋሪ ተደራራቢ ችግሮች ተቃውሞውን "ወደ አመፅ እና ፋብሪካ እስከማቃጠል" እንዳደረሱት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያውያን ተቃውሞ ንብረት ሲያወድም የመጀመሪያው አይደለም። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሳምንት ለአገሪቱ ደኅንነት ምክር ቤት ያዘጋጀው እና ሾልኮ ወጥቷል የተባለው ሰነድ እንደሚጠቁመው "የውጭም ሆነ የውስጥ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ እና መዳከም" ታይቷል። ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ የአገር ጎብኚዎች ቁጥር "በከፍተኛ ደረጃ" መቀነሱን፣ "በርካታ ቤቶች እና ንብረቶች መውደማቸውን" ሰነዱ አክሎ አትቷል።

በ2009 ዓ.ም. የመጀመሪያ ስድስት ወራት ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ መዋዕለ-ንዋይ ከአመት በፊት ከነበረበት በ20% መቀነሱን ብሎምበርግ ጋዜጣ ዘግቦ ነበር።  ወቅቱ በተከታታይ ፖለቲካዊ ተቃውሞዎች ምክንያት አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የምትተዳደርበት ነበር።

ከወረዳ እስከ ፌድራል መንግሥቱ ያለው መዋቅር በዜጎች ዘንድ የሚነሱ ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያሳየው ዳተኝነት መሰላቸት እና ተስፋ መቁረጥ ሲፈጥር ይታያል። መንግሥታዊ መዋቅሩ ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች መፍትሔ መፍጠር ቀርቶ ለማዳመጥ ዝግጁነት ማጣቱ የከፋ ዋጋ ሲያስከፍለው ከርሟል። "ለዓመታት ለዘለቀ ችግር መፍትሔ በመጠየቅ በቂ እድል ሰጥተናል" የሚሉት የምንጃሩ ነዋሪ ምላሽ ግን አልተገኘም ሲሉ ይናገራሉ። "ችግሩን ለመፍታት የተሔደው እንቅስቃሴ እልባት ያላገኘው በሰላማዊ መንገድ ስላቀረብን ነው። ምን አልባት በዚህ መንገድ ብናቀርብ መፍትሔ እናገኛለን" የሚል ተስፋ በተቃዋሚዎች ዘንድ መፈጠሩን ታዝበዋል።

ምንጃሮች ዛሬም ለጠየቁት ጥያቄ ምላሽ እየጠበቁ ነው። የወረዳው ነዋሪዎች ከሰሜን ሸዋ ሹማምንት ጋር መምከራቸውን የነገሩን የአረርቲ ከተማ ነዋሪ በሒደት መፍትሔ ሊመጣ ይችላል የሚል እምነት አላቸው። ካልሆነ ግን ተቃውሞው ሊያገረሽ እንደሚችል እርግጠኛ ናቸው።

የሚን ሰን የእንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ከገጠመው ጥቃት በኋላ ተጎጂ የሆኑት የአካባቢው ነዋሪዎች መሆናቸውን አቶ ይኩኖአምላክ ይልማ ተናግረዋል። ፋብሪካው ተጠግኖ ወደ ስራ እንዲመለስ ቻይናውያኑን ባለድርሻዎች ለማሳመን ጥረት ላይ ነን የሚሉት ኃላፊው ጥቃቱ ሌሎች መሰል ባለወረቶች ወደ በአገሪቱ ለመስራት ያላቸው ፍላጎት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለዋል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ