1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምዕራባዉያኑን አቋም እንቆቅልሽ ይሉታል

Negash Mohammedሐሙስ፣ ነሐሴ 5 2008

ዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮጳ ሕብረት ትናንት በየፊናቸዉ እንዳስታወቁት ኢትዮጵያ ዉስጥ ሰዉ መገደል፤ መቁሰል መታሰሩን አሳዛኝ ብለዉታል።ግጭት ግድያዉን ለማቆምም «ሁለት» ያሏቸዉ ወገኖች እንዲወያዩ ጠይቀዋል።የበርሊኑ የፖለቲካ አቀንቃኝ ደረጀ መንገሻ የምዕራባዉያኑን አቋም እንቆቅልሽ ይሉታል

https://p.dw.com/p/1Jgk7

[No title]

ኢትዮጵያ ዉስጥ ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ የብዙዎችን ሕይወት ያጠፋዉ የአደባባይ ሰልፍ፤ ግጭትና ግድያ አሁንም ሙሉ በሙሉ አልበረደም።ዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮጳ ሕብረት ግጭት ግድያዉ እንዲቆም እና ተቀናቃኝ ሐይላት እንዲወያዩ ጠይቀዋል።ዉጪም ሐገር ዉስጥም የሚኖሩ ኢትዮጵያዉን ግን የምዕራባዉያኑን አቋም አጣጥለዉ ነቅፈዉታል።ኢትዮጵያዉያን የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ምዕራባዉያን መንግሥታት የሚያራምዱት እርስ በርሱ የሚቃረን አቋም ነዉ።ጥቅማቸዉ ካልተነካ በስተቀር ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚፈፀመዉን ግፍና በደል ከቁብ አይቆጥሩትም የሚሉም አሉ።

የአደባባይ ሰልፍ፤አመፅ፤ የፀጥታ ሐይላት የሐይል እርምጃም፤ ጋዜጠኛ ሐይለ መስቀል በሸዋም የለሕ እንደሚለዉ፤ ደረጃ፤ መጠን ሥፋቱ እንዳለፈዉ ሳምንት ማብቂያ አይደለም።ግን ትናንት እና ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ።

ዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮጳ ሕብረት ትናንት በየፊናቸዉ እንዳስታወቁት ኢትዮጵያ ዉስጥ ሰዉ መገደል፤ መቁሰል መታሰሩን አሳዛኝ ብለዉታል።ግጭት ግድያዉን ለማቆምም «ሁለት» ያሏቸዉ ወገኖች እንዲወያዩ ጠይቀዋል።የበርሊኑ የፖለቲካ አቀንቃኝ ደረጀ መንገሻ የምዕራባዉያኑን አቋም እንቆቅልሽ ይሉታል።

ጋዜጠኛ ሐይለ መስቀል ደግሞ ይጠይቃል።ይወያዩ የሚባሉት እነማን ናቸዉ? እያለ።የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ዩሱፍ ያሲን ደግሞ የምዕራባዉያንን አቋም እሁለት ይከፍሉታል።ምዕራባዉያኑ «ግድያዉ ይቁም ማለታቸዉን»-አንድ እና ተገቢ ሲሉት፤ ድርድር መባሉን ባንፃሩ «ዲፕሎማሲያዊ ፈሊጥ» እና «ትርጉም» የለሽ።

ዘገቦች እንደሚጠቁሙት በየሥፍራዉ የተቀጣጠለዉ ተቃዉሞ ዛሬም አልበረደም።ዳግም ሰዉ ይገደላል የሚለዉ ሥጋት ዉጥረቱም እንዳየለ ነዉ።አቶ ደረጀ እንደሚገምቱት ተቃዉሞዉi የሚቆመዉ ሕዝቡ ያነሳቸዉ ጥያቄዎች ሲመለሱ ብቻ ነዉ።

ጋዜጠኛ ሐይለ መስቀል እንደሚያምነዉ ምዕራባዉያን መንግሥት ቢፈልጉ፤የኢትዮጵያ መንግሥት ለሕዝቡ ጥያቄ ተገቢዉን መልስ እንዲሰጥ ወይም ግድያዉን እንዲያቆም ማድረግ አይገዳቸዉም ነበር።አቶ ዩሱፍ የምዕራባዉያኑን የእስካሁን አቋም «የዘገየ እና ትንሽ ይሉታል» ለከእንግዲሁ እንዲፈጥኑ እና አፀፋቸዉ ጠንከር እንዲል ደግሞ አብነቱ የኢትዮጵያዉያኑ ግፊት መጠናከር ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ