1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቲማቲም እና ቃሪያ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል

ዓርብ፣ መጋቢት 1 2009

የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈዉ ጥር ለመንግስት ሰራተኞች ያደረገውን የደመወዝ ስኬል ማስተካከያን ተከትሎ በተለያዩ መሰረታዊ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ንረት ተከስቷል፡፡ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪው እንደ ቲማቲም እና ቃሪያ ባሉ በብዙሃኑ ዘንድ በሚዘወተሩ አትክልቶች ላይ ጭምር ታይቷል፡፡

https://p.dw.com/p/2Yyeb
Äthiopien Israeli NGO brings high Quality seed to Ethiopian Farmers
ምስል Fair Planet

Ethiopians complain on food items Price hike (FINAL) - MP3-Stereo

በኦሮሚያ ክልል ነዋሪ የሆኑት የ40 ዓመት ጎልማሳ በ1983 ዓ.ም በነበረው አለመረጋጋት ድንበር አቋርጠው በሱዳኗ አነስተኛ ከተማ ከሰላ ላይ ተጥልለው ነበር፡፡ ያኔ ጥያቄ ቀረበላቸው፡፡

“ፈረንጆቹ ‘ወደ ሀገር ቤት የምትመለሱና ወደ ውጭ የምትሄዱ’ ሲሉ ‘እኔ ወደ ሀገሬ እመለሳለሁ፡፡ ወቅቱ ጥቅምት ነው፡፡ አገዳ ወይም እሸት እበላለሁ’ ብዬ ነበር የተመለስኩት” ይላሉ በፈገግታ ታጅበው፡፡  

አሁን በነጭ ጤፍ አምራችነቷ በምትታወቀው አድአ ወረዳ ተቀምጠው “ልጅነት ባይዘኝ እና የገጠር ልጅ ባልሆን ይሄኔ አውሮፓ ነበርኩ” ይላሉ ቁጭት በተቀላቀለው ስሜት፡፡ በቀድሞ ውሳኔያቸው እንዲጸጸቱ ካደረጓቸው ነገሮች አንዱ የኑሮ መወደድ ነው፡፡

“የኑሮ ወድነቱ በሚገርም ሁኔታ ከባድ ነው፡፡ ሐሙስ እኛ ጋር ገበያ ነው፡፡ ምግብ ቤት ነገር አለችኝ፡፡ እነግዳለሁ፡፡ አንድ ኪሎ ቲማቲም 35 ብር፣ ቃሪያ እንደዚያው 50 ብር፣ ምስር ከ50 እስከ 65 ብር፣ አንድ ኩንታል የአድአ ማኛ ጤፍ ከ2‚100 እስከ 2‚700 ብር ናቸው፡፡ ስንዴ ኩንታል 700 ብር ገደማ ነው፡፡ ሽምብራ አይቀመስም፡፡ እነዚህ የወጥ ነገሮች ከባድ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ፍየል፣ ዶሮ የቅንጦት ነው” ይላሉ በትናንትው ዕለት በአድአ የነበረውን የመብል ሸቀጦችን ዋጋዎች ሲዘረዝሩ፡፡

በኢትዮጵያ በምግብ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ማሻቀብ በመንግስታዊው የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ወርሃዊ ዘገባ ላይም ተመልክቷል፡፡ እንደ መስሪያ ቤቱ ዘገባ ከሁለት ወር በፊት 5 በመቶ የነበረው የምግብ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት ባለፈው የካቲት 7.8 በመቶ ገብቷል፡፡ በሀገሪቱ ያለው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ደግሞ በጥር ወር ከነበረበት 6.1 በመቶ በየካቲት ወደ 7 በመቶ ከፍ ማለቱን ጠቁሟል፡፡

ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ የሆነ አቶ አበበ አዲስ የተባሉ አድማጫችን ስለ ዋጋ ግሽበት ተከታዩን በዋትስ አፕ አድራሻችን ልከውልናል፡፡

Äthiopien Markt 2008
ምስል DW/G. Haile Giorgis

“የዋጋ ግሽበት ባስ [ብሎበታል]፡፡ ሊያቃጥለን ደርሷል፡፡ ሰው ከቲማቲም በታች ምን ይበላል? ከቃሪያ በታች ምን ይበላል? በዚህ ጾምስ ምን ይበላል? የኢትዮጵያ መንግስት እንደው ይህን ነገር መፍታት አልቻለም፡፡ እኛ ከምንኖርበት አካባቢማ የባሰ ሆኗል፡፡ እሳት ሆንብናል” ይላሉ በምሬት፡፡

እንደ አቶ አበበ ሁሉ በርካታ አድማጮቻችን በአካባቢያቸው ያለውን ሁኔታ በዋትስ አፕ አድራሻችንም ሆነ በፌስ ቡክ ገጻችን አጋርተውናል፡፡ አብዛኛው አስተያየት ሰጪዎቻችን በየአካባቢያቸው የዋጋ ንረት እንዳለ ነግረውናል፡፡ ብዙዎች አጽንኦት የሰጡት ቀደም ሲል በርካሽ ይገኙ የነበሩት ቲማቲም፣ ቃሪያ እና ጎመን ላይ የተደረገው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ነው፡፡ የተወሰኑ አድማጮቻችን  ለዋጋ መወደዱ አንዱ ምክንያት “መንግስት ለሰራተኞች ያደረገው የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ” ነው ሲሉ ሌሎች በበኩላቸው መንስኤው “ሰው ሰራሽ ነው” በማለት ነጋዴዎችን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ አንድ የጅማ አድማጫችን በምግብ ሸቀጦች ላይ “የዋጋ ንረቱ የተከሰተው ያለወቅቱ በዘነበው ዝናብ ነው” ብለዋል፡፡

የንግድ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ትዕግስት ዳኝነት መንስኤዎቹን እና መንግስት እየወሰደው ያለውን እርምጃ አስመልከቶ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

“ከመንግስት የደመወዝ ማስተካከያ ጋር አንዳንድ ነጋዴዎች ያለአግባብ [የዋጋ] ንረት አድርገዋል፡፡ አንደኛው ይሄ ነው፡፡ ሁለተኛ ከቲማቲም ጋር ተያይዞ የግብርና ሚኒስቴር መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በባለፈው ወራት በነበረ የአየር መለዋወጥ ወይም ውርጭ ምክንያት የቲማቲም እጥረት ከቦታው እንዳለ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ዋጋ ከማረጋጋት ጋር በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ አንዱ ስራ የንግድ ሚኒስቴር የመሰረታዊ ሸቀጦችን አቅርቦት በተመለከተ ከክልል ካሉ ንግድ ቢሮ ኃላፊዎች ጋር በቅንጅት በመስራት ዩኒዩኖችን በማሳተፍ የአቅርቦት ችግር እንዳይኖር ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛ የአላግባብ [የዋጋ] ንረት የሚፈጥሩ ነጋዴዎች ካሉ የመጀመሪያው ስራ ማስተማር ነው የሚሆነው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በዚህ የማይማሩ እና የማይስተካከሉ አካላት ካሉ ግን ያው ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ ይወሰዳል” ብለዋል፡፡   

የንግድ ሚኒስቴር ጉዳዩን የሚከታታል ኮማንድ ፖስት ማቋቋሙንም ወ/ሮ ትዕግስት ጨምረው ገልጸዋል፡፡ 

  

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ