1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምግብ ዋጋ መናር በታዳጊው ዓለም

ረቡዕ፣ መጋቢት 24 2000

በዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ላይ የተከሰተው የፊናንስ ቀውስ፣ የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር፣ የምግብ ፍጆት መጨመርና የእርሻ ምርቶች መወደድ ባለፉት ወራት ብዙ ሲያነጋግሩ ቆይተዋል። ብዙዎች የአፍሪቃ አገሮች በዚሁ ችግር ሲጠመዱ አሁን ደግሞ ደቡብ-ምሥራቅ እሢያ ውስጥ ዋናው የሕዝብ ቀለብ የሆነው የሩዝ ዋጋ ከመጠን በላይ ማደግ ለአካባቢው ሃገራት የራስ ምታት እየሆነ ነው።

https://p.dw.com/p/E0cI
ምስል AP

ለዓለም ገበያ ታላቋ ሩዝ አቅራቢ በሆነችው በታይላንድ የምርቱ ዋጋ ባለፉት ሶሥት ወራት ውስጥ ብቻ 30 በመቶ ጨምሯል። በወቅቱ አንድ ቶን ሩዝ ወደ 580 ዶላር ሲያሻቅብ በሌላ አነጋገር በሁለት ኪሎ አንድ ዶላር ማውጣቱ ነው። ይህ ደግሞ ለብዙሃኑ ከአቅም በላይ ነው፤ ጨርሶ የሚቀመስ አልሆነም። ታዲያ ሁኔታው አጣዳፊ ዕርምጃን መጠየቁ አልቀረም። በመሆኑም በዓለም ላይ ከታይላንድ ቀጥላ ሁለተኛዋ ታላቅ አምራች አገር ቪየትናምም የአገር ውስጡን አቅርቦትና የዋጋ መረጋጋትን ለማረጋገጥ የውጭ ንግድ ገደብ አድርጋለች።
ሌላዋ ካምቦጃ እንዲያውም ሩዝ ጨርሶ ወደ ውጭ እንዳይሸጥ ስታግድ በደቡብ-ምሥራቅ-እሢያ በሕዝብ ብዛት ታላቋ የሆነችው ኢንዶኔዚያ ደግሞ ነጋዴዎቿ በአገር ገበዮች እንዲወሰኑ የውጭ ንግድ ታክስ ለመጣል እያሰበች ነው። የሩዝ ምርት እጥረትና የዋጋው ከመጠን በላይ መናር የእሢያ የልማት ባንክ ቀደምት የኤኮኖሚ ባለሙያ ኢፍዛል አሊ እንደሚሉት በቀላሉ የሕዝብ ዓመጽን ሊቀሰቅስ የሚችል ጉዳይ ነው። “ይህን መሰሉ ሁኔታ ለመጀመሪያ በሚከሰትበት ጊዜ እጅግ አደገኛ ሊሆን ይችላል። የመደብ ትግልን ካስከተለ የሕብረተሰብ እርጋታን የሚያዛባ ነው የሚሆነው። ለዚህም ነው የደቡብ-ምሥራቅ-እሢያ መንግሥታት ለምግብ ዋጋ ጉዳይ የተለየ ክብደት የሚሰጡት”

ዛሬ ከዓለም 6,6 ሚሊያርድ ነዋሪ መካከል ግማሽ የሚሆነው ሩዝ ተቀላቢ ነው። እሢያ ውስጥ ደግሞ ከ 2,5 ሚሊያርድ ለሚበልጥ ሕዝብ ሩዝ ዋነኛው መሠረታዊ ምግብ መሆኑ ይታወቃል። በሌላ በኩል በዓለምአቀፍ ደረጃ የሩዝ ክምችት መጠን በወቅቱ ከሰላሣ ዓመታት ወዲህ ባልታየ መጠን ዝቅተኛ ሆኖ ነው የሚገኘው። በፊሊፒን ደሴቶች እጥረቱ ከአሁኑ ብዙዎችን ክፉኛ እየፈተነ ነው። 85 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት አገር አብዛኛውን የሩዝ ፍጆቷን ከውጭ በሚገባ ሩዝ መሸፈን ይኖርባታል። ይህም በዓመት ከሁለት ሚሊዮን ቶን አያንስም። በዋና ከተማይቱ በማኒላ የዓለምአቀፉ የሩዝ ምርምር ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ዱንካን ማኪንቶሽ እንደሚሉት የፊሊፒንስ ችግር ሰፊ በሆነ የእርሻ መሬት አለመታደል ነው።

“የፊሊፒንስ ችግር የራሷን የሩዝ ፍላጎት ለመሸፈን አለመቻል ነው። ለዚህም ምክንያቱ በተለይ መልክዓ-ምድራዊ ይዞታዋ ሆኖ ይገኛል። ከሰባት ሺህ የሚበልጡ ደሴቶችን የምትጠቀልለው ፊሊፒንስ ሩዝ ወደ ውጭ ከሚሸጡት ታላላቅ አገሮች ከታይላንድ ወይም ከቪየትናም ስትነጻጸር የእርሻ መሬቷ ሰፊ አይደለም። ከታይላንድ ሲነጻጸር ከግማሽ በታች ቢሆን ነው” የዋጋው መናር በተለይ እየጎዳ ያለው በተለይ ብዙሃኑን ድሃ የሕብረተሰብ ክፍል ነው። በዛሬው ጊዜ በፊሊፒንስ ብቻ አሥር ሚሊዮን ዜጎች የረሃብ ሰለቦች መሆናቸው ይታመናል። በቂ ገቢ አግኝቶ ቤተሰብን መቀለብ የመሳሰለውን የኑሮን መሠረታዊ ወጪ መሸፈኑ ከባድ የሆነባቸው አያሌዎች ናችው። የሩዝና የሌሎች መሠረታዊ ምርቶች ዋጋ መናር የብዙዎችን ኪስ እያራቆተ ነው።

ችግሩን የተገነዘበው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ተቋም በደቡባዊው ፊሊፒንስ የድሃ-ድሃ ተብሎ ለሚመደብ አንድ ሚሊዮን ገደማ የሚጠጋ ሕዝብ የምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥ የበኩሉን ዕርዳታ አቅርቧል። በደሴቲቱ የተቋሙ ፋላፊ ቫሌሪይ ጋርኒዬሪ እንዳስረዱት “የምግብ ምርቶች በየቤተሰቡ በጀት ላይ ታላቁን ድርሻ ይይዛሉ። እና የምግብ ዋጋ በሚንርበት ጊዜ ይሄው በተለይ በድሆች መጎዳት ነው የሚንጸባረቀው። ቀደም ሲል ሁኔታውን እንደምንም የተቋቋሙት ሁሉ አሁን ዋጋው በሶሥት ዕጅ ሲጨምር ለቤተሰባቸው በቂ ምግብ ለመግዛት አይችሉም”

ለሩዝ ክምችት ማቆልቆል አንዱ ምክንያት የፊሊፒኑ ዱንካን ማኪንቶሽ እንደሚሉት የባዮ-ኤነርጂ ፍላጎት በዓለም ላይ እየጨመረ መምጣት ነው። ለባዮ-ዲዝል አስፈላጊ የሆኑ ጥሬ ምርቶችን፤ የዘይት ተክሎችንና በቆሎን የመሳሰሉትን ለማብቀል የእርሻ መሬቶች ምግብ ማምረታቸውን ማቆማችው መስፋፋቱን ቀጥሏል። “መንግሥታቱ በአንድ በኩል፤ በፊሊፒንስም፤ የገበሬውን ገቢ ለማሻሻል ሲሉ ባዮ-ኤነርጂን ለማመንጨት የሚያገለግሉ ተክሎች እንዲስፋፉ ያበረታታሉ። በሌላ በኩል ብዙ ገበሬዎች ወደዚህ ገቢን የሚያዳብር የእርሻ ምርት ማዘንበላቸው ብሄራዊ የምግብ አቅርቦት ቀውስን ሊያስከትል የሚችል ነው”

በአጠቃላይ የሩዙ የዋጋ ንረት በደቡብ-ምሥራቅ-እሢያ ነዋሪዎች ዘንድ የለየለት ውዥምብር ባይባል እንኳ ብርቱ ስጋትን ነው ያስከተለው። የእሢያ ዓለምአቀፍ የፊናንስ ማዕከል በሆነችው በሢንጋፑር ሣይቀር የምርቱ እጥረት አሳሳቢ የዋጋ ንረትን ሲያስከትል፤ አንዱ ኪሎ ሶሥት ዶላር ገደማ መጠጋቱ ነው የሚነገረው፤ ነዋሪው የባሰ በመፍራት የጥድፊያ ግዢውን አጠናክሯል። እርግጥ መንግሥት በበኩሉ ሕዝቡ እንዳይደናገጥ ጥሪ ማድረጉ አልቀረም፥ ይሁንና ሰሚ ጆሮ ማግኘቱ፤ ስጋቱን ማለዘብ መቻሉ ለጊዜው የሚያጠራጥር ነው።

የምግብ ዋጋ መናር በአፍሪቃም የብዙሃኑን ሕልውና ይበልጥ ፈተና ላይ የጣለ ከባድ ችግር እየሆነ መሄዱን ቢቀር ያለፈው አንድ ዓመት በግልጽ አሣይቷል። በዓለም ላይ የነዳጅ ዘይት ዋጋ እያደገ በሄደበት በአሁኑ ወቅት በምግብ ዋጋ መናር የተነሣ የአደባባይ ተቃውሞ የተከሰተባቸውና የሕዝብ ምሬት መንጸባረቅ የያዘባቸው አገሮች ጥቂቶች አይደሉም። በቦርኪና ፋሶ፣፡ በሤኔጋልና በሞሪታኒያ የኑሮው ውድነት ብዙዎችን አደባባይ ሲያስወጣ በአይቮሪ ኮስትም መንግሥት የገነፈለውን የሕዝብ ቁጣ ለማብረድ ዛሬ ከውጭ በሚገቡ ቁልፍ ምርቶት ላይ የሚከፈለውን ታክስ አንስቷል። በኢትዮጵያም መንግሥት በቅርቡ የምግብ ምርቶች ዋጋን ለማለዘብ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ ማስታወቁ አይዘነጋም።

ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከባድ በሆነ የኑሮ ውድነት ተወጥሮ የሚገኝ ሲሆን ዘጠኝ ሚሊዮን ያህል የተራበ ሕዝብም በዚህ ዓመት አስቸኳይ ዕርዳታ ያስፈልገዋል። ይህ ሃቅ ጎልቶ የሚታየው መንግሥት ባለፉት አምሥት ዓመታት ያልተቋረጠ የአሥር ከመቶ የኤኮኖሚ ዕድገት መደረጉንና ዘንድሮ እንዲያውም 10,8 ከመቶ ዕድገት እንደሚጠበቅ በሚተነብይበት ወቅት ነው። የሆነው ሆኖ ዕድገቱ በሕዝብ ተጠቃሚነት ሲንጸባረቅ አይታይም። የኤኮኖሚ ዕድገት ከተነሣ የአፍሪቃ ምጣኔ-ሐብት በዚህ በ 2008 ዓ.ም. በአማካይ 6,2 ከመቶ ዕድገት እንደሚያሣይ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ኮሚሺንና የአፍሪቃ ሕብረት ባለፈው ምሽት አዲስ አበባ ላይ ባወጡት አዲስ የኤኮኖሚ ዘገባ ተንብየዋል።
ባለፈው 2007 አማካይ 5,8 ከመቶ የአጠቃላይ ምርት ዕድገት የታየበት የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ቀደም ያሉትን ዓመታት ስኬት ተከትሎ እንደሚራመድ ነው ዘገባው ያመለከተው። በ 2007 ቀደም ካለው ዓመት ሲነጻጸር ሰላሣ ሃገራት ከፍተኛ የኤኮኖሚ ዕድገት ቢያስመዘግቡም የዕድገቱ መጠን ግን ከአገር ወደ አገር፤ ከአካባቢ ወደ አካባቢ የተለያየ እንደነበርም ተጠቅሷል። ዘገባው አያይዞ እንዳመለከተው ይሁንና የአፍሪቃ በኤኮኖሚ ዕድገት ማገገም ትርጉም ያለው ማሕበራዊ ልማትን አላስከተለም፤ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን አልጠቀመም።

የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ዕድገት ዋነኛ መንኮራኩር ዓለምአቀፉ ፍላጎት መጨመሩና የምርቶች ዋጋ ከፍ ማለት ነበር። የመዋቅራዊው ግንባታ አያያዝ መረጋጋትና መሻሻል፣ የኤኮኖሚ ለውጥ ፍላጎት መጠናከር፣ የዕዳ መሰረዝ፣ የግል መዋዕለ-ነዋይ እንቅስቃሴ መጨመር፤ እንዲሁም በተለይ በምዕራብና በማዕከላዊው አፍሪቃ የፖለቲካ ውዝግቦች መቀነስ ነበሩ ተብሏል። ዘገባው የአሜሪካ ኤኮኖሚ ማቆልቆል፣ የምርቶችና የዋጋ በዓለምአቀፍ ደረጃ መቀነስ፣ የነዳጅ ዘይት ዋጋም መናር ከአንዳንድ አገሮች የፖለቲካ ሁኔታ አለመረጋጋት ጋር ተጣምሮ ለአዲሱ የዕድገት ትንበያ ፈታኝ እንደሚሆንም የሚያስገነዝብ ነው።

አፍሪቃ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በአማካይ ከ 5 እስከ 6 በመቶ ዕድገት ማድረጓ ብዙም አያጠያይቅም። ይሁንና መንግሥታቱም ሆኑ ዓለምአቀፉ ድርጅቶች የሚሉት ዕድገት በሕዝብ የኑሮ ሁኔታ መሻሻል ካልተከሰተ ትርጉም አይኖረውም። ውጤቱ ለጥቂቶች መካበት፤ ለብዙሃኑ የባሰ መደኽየት ከሆነ ግቡን እየመታ አይደለም። ከሣሃራ በስተደቡብ ያሉት አብዛኞቹ የአፍሪቃ አገሮች የወቅቱ ማሕበራዊ ሁኔታ እንደሚያሣየው ድህነትን በከፊል መቀነሱን የሚጠቀልለውን የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒየም ዕቅድ በቀሩት ሰባት ዓመታት ውስጥ ማሟላት መቻላችው ብዙ የሚያጠራጥር ነው።