1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎቹን የሚያባንኗቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች 

ረቡዕ፣ ሰኔ 27 2010

በየአመቱ ባለ ሁለት አሐዝ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት እያስመዘገበች ነው የተባለችው ኢትዮጵያ ስለ ምን የዕዳ ጫና አጎበጣት? ዓለም ያደነቀው የተባለው ፈጣን ዕድገት እንዴት ለዋጋ ግሽበት እጁን ሰጠ? የአገሪቱን የተዛባ የገቢ እና ወጪ የንግድ ሚዛን ማረቅ ለምን ተሳነው? በፍጥነት ለሚያድገው የአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር በቂ የስራ ዕድል ለምን አልፈጠረም?

https://p.dw.com/p/30qWp
Äthiopien Addis Chamber
ምስል Addis Ababa Chamber of Commerce & Sectoral Associations

የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎቹን የሚያባንኗቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት አካታች ካልሆነ ወደ ግጭት ሊመራ እንደሚችል ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ስጋት አላቸው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት አለማየሁ "ግጭት ውስጥ ከገባን ተመልሰን እዚሁ ጋ ለመቆም ከ20 እስከ 30 አመታት ይፈጅብናል" በማለት ያስጠነቅቃሉ። ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚለው የአገሪቱ ምጣኔ ሐብት በሁለት አሐዝ አለማደጉን የሰሯቸውን ጥናቶች እየጠቀሱ ሞግተዋል። የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ፕሮፌሰር አለማየሁ "በይፋ መንግሥት የሚለን ላለፉት 10 እና 12 ዓመታት 11 በመቶ ወይም ከ11 በመቶ በላይ ኤኮኖሚው አድጓል ነው። እኔ በሰራሑት ስሌት ያን ያክል የተጋነነ ዕድገት የለም" ሲሉ ተናግረዋል።

ለመሆኑ በየአመቱ ባለ ሁለት አሐዝ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት እያስመዘገበች ነው የተባለችው ኢትዮጵያ ስለ ምን የዕዳ ጫና አጎበጣት? ዓለም ያደነቀው የተባለው ፈጣን ዕድገት እንዴት ለዋጋ ግሽበት እጁን ሰጠ? የአገሪቱን የተዛባ የገቢ እና ወጪ የንግድ ሚዛን ማረቅ ለምን ተሳነው? በፍጥነት ለሚያድገው የአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር በቂ የስራ ዕድል ለምን አልፈጠረም?

በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ከፍተኛ የጥናት ባለሙያ ሆነው የሚያገለግሉት ዶክተር ሰኢድ ኑሩ የኤኮኖሚው የዕድገት ጥራት የታቀደለትን ዓላማ ለማሳካት እንቅፋት እንደሆነበት ገልጸዋል። ዶክተር ሰዒድ "ኮብል ስቶንም ሰርተን ሰው ገቢ አግኝቶ የደሞዝ ክፍያ ውስጥ ገብቶ ተደምሮ ዕድገት ይሆናል፤ ቤት ተሰርቶ ሕንፃ ተገንብቶ ዕድገት ይሆናል። ቤት ከተሰራ በኋላ ግን ማምረት ካልቻለ ሙት ካፒታል ነው። ለሚቀጥለው እስካላመረተ ድረስ ቀጣይ አይሆንም። ስለዚህ ይኼ የዕድገት ጥራት የምንለው ነገር ከመዋቅራዊ ለውጥ ጋር የተያያዘ ነው" ሲሉ አስረድተዋል።

Äthiopien Addis Chamber
ምስል Addis Ababa Chamber of Commerce & Sectoral Associations

ቅጠል በሉ ነብር?

በተባበሩት መንግስታት ካፒታል ዴቨሎፕመንት ፈንድ ከፍተኛ ፕሮግራም ዳይሬክተር ሆነው የሚያገለግሉት ዶክተር እዮብ ተስፋዬ ግን የአገሪቱ ምጣኔ ሐብት የሚመራበት እና እጅግ የተለጠጠ የሚባለው የዕድገት እና የለውጥ ዕቅድ ጉድለት ነበረበት ባይ ናቸው። "በአምስት አመት ውስጥ በውጭ ምንዛሪ ደረጃ እንኳ ብንሔድ የውጭ ንግዱ ከነበረበት 2 ቢሊዮን ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር እናደርሳለን የሚል ዕቅድ ነበረው። በጣም የተለጠጡ ዕቅዶች ናቸው። የደቡብ ኮሪያ ፣ ሲንጋፖር እና ማሌዥያ ኤኮኖሚዎች የምሥራቅ እስያ ነብር እንደሚባሉት የእኛንም ኤኮኖሚ የምሥራቅ አፍሪቃ ነብር እናደርገዋለን ተብሎ ነው የተነሳው። መሠረታዊው ነገር እዚህ ላይ ዕቅዱን ያወጡት ሰዎች የረሱት ነገር ምንድነው ቅጠል በል ነብር እንደሌለ አልተረዱም" ሲሉ ኢትዮጵያ ዕቅዱን ገቢራዊ ለማድረግ የሚያሻት ፋይናንስ እንዳልነበራት ተችተዋል። የኢትዮጵያ ሹማምንት ግዙፍ የመሠረተ-ልማቶች እና ስኳር እና ማዳበሪያን መሰል ሸቀጥ ማምረቻ በርካታ ፋብሪካዎች መገንባትን ጨምሮ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ሲነሱ በብድር ላይ ብቻ ማተኮራቸው ሁለተኛው ጉድለት ነው። ዶክተር እዮብ "ይኸን ዕቅድ ፋይናንስ ሊያደርጉ የሔዱበት መንገድ አንድ ብቻ ነው። በብድር ላይ የተመሠረተ ነው። አንድ በአገር ውስጥ ብድር ከባንኮች ሁለተኛ በገንዘብ ሕትመት [እንደ ብድር እንቆጥረዋለን]፣ ሶስተኛው በውጭ ብድር ላይ የተንጠለጠለ ነው። ከዚህ ሞዴል ውጪ መውጣት አልቻሉም" ሲሉ ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ መንግሥት ከተለያዩ ተቋማት የተበደረው ገንዘብ ግን ይዞ የመጣው ተጨማሪ ጫና ሆኗል። ዶክተር እዮብ "የብድር መብዛት ኤኮኖሚው ውስጥ ብር እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። ከአገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት የገንዘብ አቅርቦት ከፍ ብሎ እንዲንር አድርጓል። በአንድ ኤኮኖሚ ውስጥ ከአጠቃላይ ኤኮኖሚው [አጠቃላይ የአገር ውስጥ አመታዊ ምርት] በላይ የገንዘብ አቅርቦት ከወጣ የገንዘብ ግሽበት ይከሰታል። ሲከተል የነበረው የገንዘብ ፖሊሲ ልቅ የገንዘብ ፖሊሲ ነው። ማዕከላዊ ባንኩ ማዕከላዊ ባንክ ሳይሆን ማተሚያ ቤት ነበር ይቻላል" ሲሉ ይወቅሳሉ።

Äthiopien Addis Chamber
ምስል Addis Ababa Chamber of Commerce & Sectoral Associations

በዶክተር እዮብ ትንታኔ መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት የብር የምንዛሪ ተመንን ያዳከመው የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ድርሻም ለሽያጭ ያቀረበው በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ነው። ባለሙያው የመንግሥቱ ሹማምንት የባለሙያዎችን ማስጠንቀቂያ ለመሥማት ዝግጁ እንዳልነበሩ የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባዘጋጀው ውይይት ለተሳተፉ ተናግረዋል። "የውጭ ምንዛሪ እጥረት ይመጣል ሲባል ማንም ሰው መስማት አይፈልግም።  ይኼን ሊያማክሩ የተቀመጡ የባንክ ገዢዎች የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር አይመጣም በሚል ነው መንግሥት ተደፋፍሮ አንዳንዴም በጀብደኝነት ትላልቅ ዕቅዶች ውስጥ የገባው። የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቱን ይቀንሳል ተብሎ የተካሔደው የብርን የምንዛሪ አቅም የማዳከም ውሳኔ ምንም መፍትሔ ሳይሆን ሲቀር የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ድርሻ ወደ መሸጥ ተገባ። አገሪቱ አለኝ የምትላቸውን ብርቅዬ ኩባንያዎች ለሽያጭ አቅርባለች" ብለዋል ዶክተር እዮብ።

በዶክተር ሰኢድ ትንታኔ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት መነቃቃት የግል እና የመንግሥት ፍጆታ ጨምሯል። ኢትዮጵያውያን ከዕለታዊ ፍጆታዎች አልፎ ቅንጡ ቴሌቭዥኖች እና የእጅ ስልኮች ሸማች መሆናቸውን እየጠቀሱ "ገበያ መፈጠሩ ጥሩ ነው" የሚሉት ዶክተር ሰኢድ የአገሪቱ ምጣኔ ሐብት አንገብጋቢ ማሻሻያዎች ማድረግ ይጠበቅበታል ባይ ናቸው። ዶክተር ሰኢድ "በዚያ ልክ ማምረት የሚችል አገራዊ ተቋም መኖር አለበት። ወይም የውጭ ምንዛሪ ማስገባት አለብን። እንደዚህ አይነት የፍጆታ እቃዎችን ለምነን በምናመጣው እና በምንበደረው ገንዘብ" መሸመት አያወጣም ሲሉ ያስረዳሉ። ኢትዮጵያ በምጣኔ ሐብት ረገድ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የአምራች ኢንዱስትሪው በፍጥነት ሊያድግ፤ ግብርና ሊዘምን  እንደሚገባ አስረድተዋል።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ