1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሞሮኮና የፖሊሳርዮ ነፃ አውጭ ንቅናቄ ድርድር

ሰኞ፣ ሰኔ 11 1999

የምዕራብ ሰሀራ ጉዳይ ከዓለማችን የተረሱ ግጭቶች አንዱ እስከመሆን ደርሷል

https://p.dw.com/p/E0au

የሞሮኮ መንግስትና የፖሊሳርዮ ነፃነት ንቅናቄ ዛሬ ኒውዮርክ ውስጥ ቀጥተኛ ንግግር ያደርጋሉ ። ይኽው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አማካይነት የሚካሄደው ድርድር በመንግስትና በንቅናቄው መካከል ለለሰላ ሁለት ዓመታት የዘለቀውን ግጭት ያስወግዳል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል ። ለሁለት ቀናት የሚካሄደውን ንግግር የሚመሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ባንኪሙን የምዕራብ ሰሀራ መልዕክተኛ ፒተር ቫን ቫልሰም ናቸው ። በዚሁ ስብሰባ ላይ የአልጀሪያ እና የሞሪታኒያ ተወካዮችም ይገኛሉ ። እአአ በሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባት አምስት ነበር ሞሮኮ ምዕራብ ሰሀራን በኃይል ወደ ራስዋ ያቀላቀለችው ። በአልጀሪያ የሚደገፈው የፖሊሳርይዮ ነፃ አውጭ ንቅናቄም ይህን በመቃወም ግዛቲቱ ነፃ እንድትወጣ ሲታገል ቋይቷል ። በአሁኑ ሰዓት ግን የምዕራብ ሰሀራ ጉዳይ ከዓለማችን የተረሱ ግጭቶች አንዱ እስከመሆን ደርሷል ። እንደሌሎቹ ግጭቶች ችግሩ ጎልቶ ስለማይሰማ በብዙዎች ዘንድ ያለው አስተሳሰብ ሁኔታው ባለበት መልኩ ይቀጥላል የሚል ነው ። በፍሬድሪክ ኤበርት ድርጅት የሰሜን አፍሪቃ ተንታኝ ሀዮ ላንዝ
“የዓለማችን ማህበረሰብ ከዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ጋር ነው የሚኖረው ። ከአሁን በኃላ ምንም ጦርነት አይኖርም ከሚለው ጋር ። በአሁኑ ሰዓት የተኩስ አቁም አለ ፤ በዚህ ሁኔታም ህዝቡ መኖር ይችላል “
ተንታኙ ላንዝ ይህን ቢሉም የምዕራብ ሰሀራ ጉዳይ ሲጤን ችግሩ ደም አፋሳሽ አልነበረም ማለት አይቻልም ። ሞሮኮ እአአ በሺህ ዘጠኝ መቶ ሀምሳ ስድስት ነፃ ከወጣች አንስቶ በፎስፌት ማዕድን የበለፀገችው ምዕራብ ሰሀራ ትሰጠኝ ስትል ጥያቄዋን ከማንሳት ወደ ኃላ አላለችም ነበር ። ሞሮኮ ነፃ ከወጣች በኃላም ምዕራብ ሰሀራ የስፓኝ ቅኝ ነበረች ። እአአ በሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ ሶስትም የተወሰኑ ወጣቶች ታዋቂውን የፖሊሳርዮ ንቅናቄ መሰረቱ ። የንቅናቄው ዓላማም ምዕራብ ሰሀራን ነፃ ማውጣት ነበር ። ከአንድ ዓመት በኃላ ደግሞ ሞሮኮ ዘሄግ ለሚገኘው ለዓለም ዓቀፉ ፍርድ ቤት የምዕራብ ሰሀራን የይገባኛል ጥያቄ አቀረበች ። ፍርድ ቤቱም አንዳንድ የምዕራብ ሰሀራ ጎሳዎች ከሞሮኮው ንጉስ ጋር የተያያዘ የዘር ሀረግ እንዳላቸው ከማረጋገጥ በስተቀር ግዛቲቱ ለሞሮኮ ትሰጥ የሚል ውሳኔ ሳያሳልፍ ቀረ ። የምዕራብ ሰሀራ ጉዳይ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ እአአ በሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባት አምስት በግዛቲቱ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ለውጥ የሚያስከትል ሁኔታ ተፈጠረ ። የስፓኙ አምባገነን መሪ ጀነራል ፍራንኮ በሞቱበት በዚህ ወቅት ላይ የሞሮኮው ዳግማዊ ንጉስ ሀሰን ሰላማዊ ሰዎች ናቸው የታባሉ ቁጥራቸው ወደ ሶስት መቶ ሀምሳ ሺህ የሚጠጋ ሰዎች አደራጅተው ወደ ግዛቲቱ ላኩ ። በዚህ ጊዜም ምዕራብ ሰሀራ የነበረው የስፓኝ ጦር አንዳችም የመከላከል ሙከራ ሳያደርግ ሰዎቹን አስገብቶ ግዛቲቱን ለቆ ወጣ ። ይህም ለምዕራብ ሰሀራ ግጭት መነሻ ሆነ ። ሞሮካውያኑ ወደ ምዕራብ ሰሀራ ሲገቡ አስር ሺህ የሚሆኑ ሳሀራውያንን ከግዛቲቱ ወጥተው ወደ አልጀሪያዋ ቲንዱፍ ከተማ ተሰደዱ ። ከዚያን ጊዜ አንስቶም የፖሊሳርዮ ግንባር በደፈጣ ውጊያ ተሰማራ ። በመንግስትና በተቃዋሚዎች መካከል በተካሄደው ውጊያም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የጥቃት ሰለባ ሆነዋል ። ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶም ለምዕራብ ሰሀራ ውዝግብ መፍትሄ ለመሻት በርካታ ጥረቶች ቢደረጉም ከአንዱ በስተቀር አብዛኛዎቹ ውጤት አላስገኙም ። ከእስካሁኖቹ ጥረቶች አንድ ውጤት ያመጣው እአአ በሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና አንድ በተባበሩት መንግስታ ድርጅት አማካይነት የተካሄደው ድርድር ነው ። በዚሁ ድርድር የምዕራብ ሰሀራ ጉዳይ በህዝበ ውሳኔ እንዲፈታ ስምምነት ላይ ተደርሷል ። ይሁንና ይህ ስምምነትም ቢሆን እንከን አላጣውም ። ሁለቱ ወገኖች እስካሁን በህዝበ ውሳኔው መሳተፍ ያለበት ማን ነው በሚለው ነጥብ ላይ መግባባት አልቻሉም ። የመንግስታቱ ድርጅት ማን ነው ህዝበ ውሳኔ መስጠት ያለበት ለሚለው ግልፅ ነገር ባለማስፈሩ ጉዳዩ አሁንም በዕንጥልጥል ላይ ነው ። ከፖሊሳርዮ ነፃ አውጭ ንቅናቄ መስራቾች አንዱ የሆኑት ባሽር ኤዳልቺል
ድምፅ
“የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ህዝበ ውሳኔ መስጠት የሚገባውን መራጭ በግልፅ አላሳወቀም ። ስራውን ጀምሮታል ። ነገር ግን በህዝበ ውሳኔው የመሳተፍ መብት ያላቸው ሰሀራውያን የትኞቹ እንደሆኑ ግን አልወሰነም “
ይህ አንዱ ችግር ሲሆን ሞሮኮም አሁን ህዝበ ውሳኔውን በመቃወም ምዕራብ ሰሀራ በሞሮኮ ግዛት ስር አንድ ራስ ገዝ እንድትሆን ለፀጥታ ጥበቃው ምክርቤት ሀሳብ አቅርባለች ።ይህን ሀሳብ ደግሞ ፖሊሳርዮ አይቀበልም ። በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኘው የሁለቱ ወገኖች አቋም የሚታረቅ ባይመስልም ዛሬ ኒውዮርክ ውስጥ የሚካሂዱት ድርድር አዲስ ተስፋ ይፈነጥቅ ይሆናል የሚል ዕምነት ተጥሎበታል ።