1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሞት ቅጣት መጨመሩ

ረቡዕ፣ መጋቢት 28 2008

በዓለም አቀፍ ደረጃ በሞት የሚቀጡት ሰዎች ቁጥር እጅግ መጨመሩን ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው ዘገባ አሳየ።

https://p.dw.com/p/1IQIj
Deutschland Galgen im Neanderthal Museum Mettmann
ምስል picture-alliance/dpa/R. Weihrauch

[No title]

እንደ ዘገባው፣ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ቁጥሩ በአስደንጋጭ ሁኔታ ነው ከፍ ያለው። ለዚሁ ጭማሪ ምክንያቱ ምን ይሆን?


ባለፈው 2015 ዓ,ም በዓለም አቀፍ ደረጃ 1,634 ሰዎች ተገድለዋል። ይህ አኃዝ ከ2014 ጋር ሲነጻጸር በ50% ጨምሮዋል። በ2015 በሞት የተቀጡት ሰዎች ቁጥር ባለፉት 25 ዓመታት ከተፈ,ጸመው የሞት ቅጣት በልጦ ነው የተገኘው። ይህ ጉልህ ጭማሪ እጅግ እንዳሳሰባቸው በዓለም የሚፈጸሙ የሞት ቅጣቶችን የሚከታተሉት የአምነስቲ ባለሙያ ኪያራ ሳንጂዮርጂዮ ገልጸዋል። አምነስቲ ቁጥሩ በይፋ ከሚነገረው እንደሚበልጥ ያምናል፣ ምክንያቱም፣ የሞቱ ብይን እና ቅጣቱ በሚስጢር ከሚያዝባት ቻይና ይህንኑ በተመለከተ አንዳችም ይፋ መረጃ አይወጣም። እንደሚገመተው፣ በዚችው እስያዊት ሀገር በቻይና ባለፈው ዓመት ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሞት እንደተቀጡ ይገመታል። በዓለም ብዙ ሰዎችን በሞት በመቅጣት ቻይና በዓለም ቀዳሚውን ቦታ ይዛለች። ትክክለኛውን ቁጥር ማግኘት ግን አልተቻለም። በሞት የተቀጡ ሰዎች ቁጥር ከመጨመሩ ጎን፣ የሞቱን ቅጣት ተግባራዊ ያደረጉት ሀገራት ቁጥርም ባለፉት ጊዚያት ከፍ ብሎዋል። የሞት ፍርድ መስጠት ከሚፈቀድባቸው 94 ሀገራት መካከል በ2015 ዓ,ም ቅጣቱን የፈፀሙት ሀገራት 25 ነበሩ፣ በ2014 ዓ,ም ደግሞ 22 ሀገራት ብቻ ነበሩ። በ2015 ዓ,ም 90% ው የሞት ቅጣት የተፈጸመው በተለይ በኢራን፣ ፓኪስታን እና ሳውዲ ዐረቢያ ውስጥ ነው። በፓኪስታን 320 በሞት ተቀጥተዋል።
« ለምሳሌ፣ የፓኪስታን መንግሥት በ2014 ዓም በፔሻወር የተፈጸመውን አስከፊ ጥቃት ተከትሎ የሞት ፍርድ ብያኔዎችን እና የቅጣቱን ፍጻሜ እንደገና ለመጀመር ወስኖዋል። ከታህሳስ 2014 ዓለም ወዲህ ባለስልጣናቱ ሳያቋርጡ የሞት ቅጣቱን ተግባራዊ እያደረጉ ነው። ፓኪስታን ውስጥ በየቀኑ ሰዎች በምት እንደሚቀጡ ነው የምንሰማው። »
ፓኪስታን ውስጥ የሞት ፍርድ ከሚያስበይኑ 30 የወንጀል ዓይነቶች መካከል የሱስ አስያዥ ዕፀ ንግድ፣ በትዳር ላይ መማገጥ እና ክብረ ንፅሕናን መድፈር የመሳሰሉት በሞት ከሚያስቀጡ ወንጀሎች ጥቂቶቹ ናቸው። በአሁኑ ጊዜም በዓለም የሞት ቅጣታቸውን የሚጠባበቁ ብዙ ወንጀለኞች የሚገኙባት ቀዳሚዋ ሀገር መሆኗን የአምነስቲ ዘገባ አመልክቶዋል።
አምና ኢራን በአብዛኛዉ በዕፀ ንግድ የተወነጀሉ 1000 ሰዎች በሞት ቀጥታለች። በሞት ቅጣት በከፍተኛ ደረጃ ማለትም 76% ጭማሪ የታየው ግን በሳውዲ ዐረቢያ ሲሆን ብዙዎቹ በርሸና ወይም አንገታቸው በመቅላት ነዉ የተገደሉት ። አልፎ አልፎ ደግሞ አስከሬናቸው ለሕዝብ ለእይታ እንደቀረበ የአምነስቲ ዘገባ አመልክቶዋል።
በዘገባው መሰረት በ2014 ዓ,ም አንድም ሰው በሞት ያልቀጡ ስድስት ሀገራት፤ በ2015 የሞት ቅጣትን ፈጽመዋል። ለምሳሌ፣ ይላሉ ኪያራ ሳንጂዮርጂዮ፣
« ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ አንድም ሰው በሞት ሳትቀጣ የቆየችው ቻድ ባለፈው ዓመት የአሸባሪው ቡድን ቦኮ ሀራም አባላት ናቸው ያለቻቸውን አስር ሰዎች በሞት ቀጥታለች። ካሜሩንም የቦኮ ሀራም አባላት ናቸው ያለቻቸውን 98 ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ በይናለች። ቱኒዝያ፣ አልጀሪያ እና ግብፅም ባወጡት ልዩ የሽብርተኝነት ሕግ መሰረት የሞት ብይን አስተላልፈዋል። »
ይሁንና፣ እንደ አምነስቲ አስተያየት፣ የሞቱ ቅጣት ሀገራትን ከሽብርተኝነት አይከላከላቸውም፣ ሽብርተኝነትንም አያስቆምም። መንግስታት በርግጥ የቦምብ ጥቃቶችን ማስቆም ከፈለጉ የችግሮችን መንስዔ ለይተው ማወቅ እና ፅንፈኝነት እንዳይስፋፋ መስራት ነው ያለባቸው። የሞቱን ቅጣት እንደ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚመለከተው አምነስቲ የሞቱ ፍርድ አዘውትሮ ትክክለኛ ባልሆነ የፍርድ ሂደት እና ቁም ስቅል ሲበዛ በተገኘ መረጃ ላይ ተመስርቶ የሚሰጥ በመሆኑ አብዝቶ ነቅፎዋል። ከዚህ በተረፈም የሞት ቅጣትን ተግባራዊ ያደረጉት ፓኪስታንን እና ዩኤስ አሜሪካን በመሳሰሉ ሀገራት በፍርዱ ብይን አሰጣጥ ላይ በጣም ብዙ ስህተት እንደሚሰሩ እና ሰዎች በስህተት እንደሚገደሉ ዘገባው አሳይቶአል።
የሞቱ ቅጣት ቢጨምርም ይህን አሰራር የሚከተሉ ሀገራት ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ግን አምነስቲ ጥሩ ዜና ብሎታል። ባለፈው ዓመት ብቻ አራት ሀገራት ማለት ማዳጋስካር፣ ፊጂ ደሴቶች፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ እና ሱሪናማ የሞት ቅጣትን ከሕጋቸው ሽረዋል። በዚህም የሞት ቅጣትን የሻሩት የዓለም ሀገራት ቁጥር ወደ 102 ከፍ ብሎዋል። ከሰሀራ በስተ ደቡብ የሚገኙት አፍሪቃውያት ሀገራት ዉስጥም በሞት የተቀጡት ሰዎች ቁጥር መቀነሱ ተመልክቶዋል። ሳንጂዮርጂዮ እንደጠቆሙት፣ ጊኒ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኬንያ የሞት ቅጣትን ሊሽሩ ይችላሉ።

አን ሶፊ ብሬንድሊን/አርያም ተክሌ
አዜብ ታደሰ

Symbolbild Schwert Exekution Saudi-Arabien
ምስል picture-alliance/dpa/Abir Abdullah
Bangladesh Lahore Demonstration
ምስል Getty Images/AFP/A. Ali