1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሞዛምቢክ መንግሥት ተቃዋሚዎች የተደቀነባቸው ስጋት

ቅዳሜ፣ የካቲት 28 2007

በሞዛምቢክ ታዋቂው የመንግሥቱ ተቃዋሚ ፕሮፌሰር ዢል ሲስታክ ከጥቂት ቀናት በፊት የተገደሉበት ድርጊት ሰፊ ተቃውሞ ቀሰቀሰ። የተቃውሞ ወገኖች በሕገ መንግሥታዊው የሕግ ዘርፍ ላይ ያተኮሩት ፕሮፌሰር እና ጠበቃ ሲስታክን የገደሉት የገዢው ፓርቲ፣ «ፍሬሊሞ» አክራሪ ኃይላት ተጠያቂዎች ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ገልጸዋል። መንግሥት ይህን ወቀሳ አስተባብሏል።

https://p.dw.com/p/1Emv0
Trauer nach der Ermodung von Gilles Cistac in Maputo
ምስል Getty Images/Afp/Sergio Costa

በሞዛምቢክ መዲና ማፑቶ በሚገኘው የኤድዋርዶ ሞንድሌን ዩኒቨርሲቲ ለብዙ ዓመታት በሕግ ትምህርት ፕሮፌሰርነት የሰሩት የ55 ዓመቱ ዢል ሲስታክ በሀገሪቱ መንግሥት ላይ ሂስ አዘል አስተያየት ከመግለጽ ወደኋላ የማይሉ ቆራጥ ሰው እንደነበሩ በኢንተርኔት የሚወጣው «ኤት ቬርዳዴ» የተባለው «ኦንላይን »ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ኤሚልዶ ሳምቦ አስታውቀዋል።

እአአ በ1960 ዓም በፈረንሳይ የቱሉዝ ከተማ የተወለዱት ሲስታክ እአአ በ2010 ዓም ነበር የሞዛምቢክን ዜግነት የወሰዱት። በሕገ መንግሥታዊው የሕግ ዘርፍ ላይ ያተኮሩት የሕግ ፕሮፌሰር ሲስታክ በዚህ በተያዘው አውሮጳዊ ዓመት 2015 ጥር ወር ላይ ለ«ኤት ቬርዳ ኦንላይን » ጋዜጣ በሰፊው የሰጡት አንድ ቃለ መጠይቅ ከመንግሥት በኩል ብርቱ ወቀሳ ተፈራርቆባቸው ከቆየ በኋላ ባለፈው ማክሰኞ ባልታወቁ ሰዎች አራት ጥይት ነው የተገደሉት።

RENAMO-Hochburgen in Mosambik Karte

« በተባለው ቃለ ምልልስ ላይ ሲስታክ በሞዛምቢክ ሕገ መንግሥት ውስጥ «ሬናሞ» ሰፊ የራስ ገዝ አስተዳደር የሚኖራቸው ግዛቶች እንዲያቋቁም የሚፈቅድ የሕግ አንቀጽ አለ ሲሉ ያስታወቁ የመጀመሪያው ሰው ነበሩ። ይህ ያቀረቡት መረጃ በመላ ሞዛምቢክ ትልቅ ክርክር ነበር ያስነሳው። »

በሰበቡም ፣ የሞዛምቢክ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው፣ ሲስታክ በፌስቡክ በርካታ ማስጠንቀቂያ ደርሷቸው ነበር፤ «ኤት ቬርዳዴ ኦንላይን » ጋዜጣም እንዲሁ ከአንባብያን የጥላቻ እና የዛቻ ማስጠንቀቂያዎች እንደደረሱት ዋና አዘጋጁ ኤሚልዶ ሳምቦ ገልጸዋል።

የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በሚኖሩባት ሞዛምቢክ ውስጥ ሰፊ ራስ ገዝ አስተዳደር የሚኖራቸው ግዛቶች ይቋቋሙ የሚል ሀሳብ ማንሳት እንደ ትልቅ - እንደሚቆጠር ኤሚልዶ ሳምቦ አክለው አስረድተዋል።

ሞዛምቢክ እአአ ከፖርቱጋል ቅኝ አገዛዝ ከተላቀቀች ወዲህ መንበሩን ማፑቶ ባደረገ አንድ ማዕከላይ መንግሥት ነው የምትተዳደረው። 11 ዱ የሀገሪቱ ግዛቶች አስተዳዳሪዎችም የሚመረጡት በሀገሪቱ ፕሬዚደንት ሲሆን፣ ይህንኑ ሥልጣን ከነፃነት ጀምሮ የያዘው ገዢው የ«ፍሬሊሞ» ፓርቲ ነው። በሀገሪቱ ትልቁ የተቃውሞ ፓርቲ «ሬናሞ» ይህን መቀየር ይፈልጋል። ባለፈው ጥቅምት ወር በተካሄደው ምርጫ ባሸነፈባቸው ናምፑላ፣ ዛምቤዚ፣ ሶፋላ፣ ማኒካ እና ኒያሳ ግዛቶች፣ ካለ ማዕከላዩ መንግሥት ስምምነት፣ ካስፈለገም በኃይሉ ተግባር በመጠቀም ፣ ሰፊ ራስ ገዝ አስተዳደር የመመሥረት ዕቅድ ይዞዋል። የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ፊሊፔ ይኸው ንዩዚ የ«ሬናሞ» መሪ አፎንዞ ድላካማ ዕቅድ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በተደጋጋሚ በማስታወቅ፣ ዕቅዱ የሞዛምቢክን የግዛት ሉዓላዊነት ስጋት ላይ የሚጥል ሕገ ወጥ ተግባር መሆኑን ከማሳሰብ አልቦዘኑም። ይሁንና፣ ይኸው የፕሬዚደንቱ አባባል ትክክለኛ አለመሆኑን የሕግ ፕሮፌሰር እና ጠበቃ ሲስታክ አንድ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ በመጥቀስ በይፋ አጣጥለውታል።

Mosambik - Präsidentschaftskandidat Filipe Nyusi
ፕሬዚደንት ፊሊፔ ንዩዚምስል Getty Images/G. Guerica

የሲስታክ መገደል በብዙኃኑ የሞዛምቢክ ሕዝብ ዘንድ የፈጠረውን ቁጣ ለማብረድ የሞከረው የሀገሪቱ መንግሥት የሕግ ፕሩፌሰር ግድያን እንደሚያጣራ የሀገር አስተዳደር ሚንስቴር ቢያስታውቅም ምርመራው ወደፊት አለመራመዱን የማፑቶ ፖሊስ ቃል አቀባይ አርናልዶ ጬፎ ገልጸዋል።

የሲስካን ግድያ በተመለከተ እስካሁን አንድም ተጨባጭ ማስረጃ አልተገኘም። »

የሲስታክን መገደል በተመለከተ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ከሆኑት ጥቂቶቹ የገዢው ፓርቲ «ፍሬሊሞ» አባላት መካከል አንዱ ቴዎዶሮ ዋቲ ናቸው።

« ሲስታክ አንድ አስተያየት ነው የሰነዘሩት፣ ይህ አስተያየት ግን የ«ፍሬሊሞን » አመለካከት የማይያንፀባርቅ ነው። ይሁንና፣ የሌሎችን አስተያየት ማክበር አለብን። የሕግ የበላይነትን በሚያከብር መንግሥት ውስጥ አስተያየት በነፃ መስጠት የያንዳንዱ ዜጋ መብት ነው። »

ሞዛምቢክ ከብዙ ዓመታት ወዲህ በአሳሳቢ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ነው የምትገኘው። ባለፈው ጥቅምት ወር የተካሄደው ምክር ቤታዊ እና ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እንኳን ይህንን ውጥረት አላረገበም። እርግጥ፣ በምርጫው ገዢው ፓርቲ «ፍሬሊሞ» በሰፊ የድምፅ ብልጫ ማሸነፉ በይፋ ቢገለጽም፣ ታዛቢዎች በምርጫው ከባድ ትክክለኛ ያልነበሩ አሰራሮች መታየታቸውን ገልጸዋል። የሞዛምቢክ ብሔራዊ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ኩስቶዲዲዮ ዱማን የመሳሰሉ የመብት ተሟጋቾች እንዳስታወቁት፣ ልዩነቱ ከሲስታክ ግድያ በኋላ ሊሰፋ ይችላል።

«የሀገሪቱ መከፋፈል ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ ስር ሰዶዋል። የሲስካ ግድያ ሁላችንንም አስደንግጦናል። ይህ ሁኔታም በሀገሪቱ የቀጠለውን የፖለቲካ ውዝግብ ይበልጡን ሊያባብስ ስለሚችል ለደህንነታችን ተጨማሪ ጥበቃ እንደሚያስፈልገን የሚጠቁም ማስረጃ ሆኖናል። »

አንቶንዮ ካስካስ/አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ