1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሞ ኢብራሒም አምስት ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አፍሪቃዊ አሸናፊ አላገኘም

ረቡዕ፣ የካቲት 22 2009

በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ ኋላም በሰላማዊ መንገድ ሥልጣን ያስረከቡ የአፍሪቃ መሪዎችን አምስት ሚሊዮን ዶላር የሚሸልመው የሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን ዘንድሮ እንዳምናው ሁሉ መስፈርቶቹን የሚያሟላ አጥቼያለሁ ብሏል።

https://p.dw.com/p/2YTt5
Logo der Mo Ibrahim Foundation

No Ibrahim Prize awarded for African leadership - MP3-Stereo

የሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን ዘንድሮም ለሥመ-ጥሩው የአፍሪቃ የአመራር ስኬት ሽልማት መሥፈርቶቹን የሚያሟላ ማጣቱን አስታውቋል። በቀድሞው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ሳሊም አህመድ ሳሊም የሚመራው መራጭ ኮሚቴ ባለፉት ሶስት አመታት ሥልጣን ካስረከቡ መሪዎች መካከል አንዳቸውም ሽልማቱ አይገባቸውም ብሏል። ድርጅቱ የምሸልመው አጣሁ ሲል ሁለተኛ አመቱ መሆኑ ነው። መቀመጫውን ብሪታኒያ ያደረገው «ቻታም ሐውስ» የተባለው የፖለቲካ ጥናት ተቋም  የአፍሪቃ ክፍል ኃላፊ ዶክተር አሌክስ ቫይነስ የሞ ፋውንዴሽን ውሳኔ እምብዛም አልገረማቸውም። 
«የሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን ለአንድ ግለሰብ ሽልማቱን ሳይሰጥ ሲቀር ይኸ የመጀመሪያው አይደለም። ሽልማቱን ቢሰጡት ምቾት የማይነሳቸው ተዓማኒ እጩ እስኪያገኙ ይጠብቃሉ። እናም የዘንድሮው የተለየ አይደለም። እንዲያውም የሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን የተለመደ ተግባር እየሆነ ነው። እናም አልተገረምኩም። በዚህ አመት መራጮቹ ማንንም አላገኙም፤ በሚቀጥለው አመት የሆነ ሰው ይመለከቱ ይሆናል።» 
ዶ/ር ሳሊም አህመድ ሳሊም ገለልተኛው ኮሚቴ እጩዎቹን በጥሞና ከመረመረ በኋላ ለጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. ማንንም ላለመሸለም መወሰኑን ትናንት የሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን የቦርድ አመራሮች በተገኙበት ተናግረዋል። ታንዛኒያዊው ዲፕሎማት የሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን ሽልማት በጎርጎሮሳዊው 2006 ዓ.ም. ሲጀመር ከፍ ያሉ መሥፈርቶች የተዘጋጁለት ሆን ተብሎ እንደሆነም ገልጠዋል። ሳሊም አገሮቻቸውን ለማሻሻል ጠቃሚ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ጥቂቶችን ብቻ እናሞግሳለን፤ እውቅናም እንሰጣለን ሲሉ ተቋማቸው መሥፈርቶቹን የመከለስ እቅድ እንደሌለው ጠቁመዋል። 
ተቋሙ እንደሚለው፣ አፍሪቃውያን መሪዎች፤ ሥራ አስፈፃሚዎች እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ለሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን ሽልማት እጩ ለመሆን አራት መሰረታዊ መስፈርቶች ሊያሟሉ ይገባል። ባለፉት ሶስት አመታት (2014-2016) በሰላማዊ መንገድ ሥልጣን የለቀቁ፤ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ፤ በሕገ-መንግሥታቸው የተቀመጠውን የስልጣን ዘመን ቆይታ ብቻ ያገለገሉ እና ወደር የለው አመራር ያሳዩ መሪዎች ለሽልማቱ እጩ መሆን ይችላሉ። በእነዚህ መመዘኛዎች መሰረት የምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪቃ አገራት በቅርብ ጊዜ ተሸላሚ መሪ የማግኘት ተስፋ እንደሌላቸው ዶ/ር አሌክስ ቫይነስ እምነታቸው ነው። 
«በምርጫ እና የስልጣን ሽግግር በኩል በምዕራብ አፍሪቃ በታዘብነው ባለተስፋ ልንሆን ይገባል ብዬ አምናለሁ። ከመካከለኛው አፍሪቃ ወይም የታላላቅ ኃይቆች ቀጠና አገራት ለሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን ሽልማት በቅርብ ጊዜ እጩ ሆኖ መቅረብ የሚችል ይኖራል ብሎ ተስፋ ለመሰነቅ የሚያስችል አንዳች ምክንያት የለም። በኮንጎ ብራዛቪል እንዳየነው ፕሬዝዳንቶች ድጋሚ በምርጫ ለመወዳደር ሕገ-መንግሥት ይቀይራሉ። ቀጣናው ተስፋ የሚጣልበት አይደለም። የሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን ሊሸልማቸው የሚችል ውስን አካባቢዎች አሉ። ይሁንና ፣ አካባቢያዊ ተለዋዋጭነት መኖሩ ልብ ሊባል ይገባል። ማንኛውም ሰው በደቡብዊ አፍሪቃ እና የምዕራብ አፍሪቃ አገራት ባለ ተስፋ ሊሆን ይገባል። ማዕከላዊ አፍሪቃ፤የታላላቅ ኃይቆች ቀጠና እና የአፍሪቃ ቀንድ ግን ተስፋ የላቸውም። »
ዶ/ር አሌክስ ቫይነስ የጋና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ምናልባት በሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን እውቅና የሚያገኝ ተግባር ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል። 
በሱዳናዊው የቴሌኮም ዘርፍ ባለጠጋ ሞ ኢብራሒም የተቋቋመው ሽልማት እስካሁን አራት መሪዎችን ብቻ ሸልሟል። የናሚቢያው ሒፊኬፑንዬ ፖሐምባ በ2014፤ የኬፕ ቬርዴው ፔድሮ ፔሬዝ በ2011፤ የቦትስዋናው ፌስቱስ ሞጋዔ በ2008 እንዲሁም የሞዛምቢኩ ዮዓኪም ቺሳኖ በ2007 ዓ.ም. ይኸው ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ የነፃነት ታጋይ እና የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ በጎርጎሮሳዊው 2007 ዓ.ም የፋውንዴሽኑ የክብር ተሸላሚ ነበሩ።

Mo-Ibrahim-Index für Regierungsführung in Afrika, 29.09.2014 in London
ምስል Barefoot Live


እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ