1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሠብአዊ መብት ይዞታ በታላላቆቹ ሐይቆች አካባቢ

ሐሙስ፣ ጥር 19 2008

የኑኩሩንዚዛን አቋም በመቃወም አደባባይ የወጡ ሰዎችን ፀጥታ አስከባሪዎች ይገድሉ፤ያስሩ፤ያሰቃዩ ገቡ። አራት ራዲዩ ጣቢያዎች ተዘጉ።ነፃ ጋዜጠኞች የሠላዮችን ክትትል፤ የግድያ ዛቻ እና እስራትን ሽሽት ተሰደዱ።አስር የሲቢል ማሕበራት ታገዱ።በመቶ የሚቆጠሩ ሠላማዊ ሰዎች ተገደሉ

https://p.dw.com/p/1HlNn
ምስል picture-alliance/dpa/D. Kurokawa

[No title]

የታላላቆቹ ሐይቆች አካባቢ መንግሥታት የዜጎቻቸዉን ሠብአዊ መብት እንደሚረግጡ፤የፖለቲካ እና የመናገር ነፃነትን እንደሚደፈልቁ ሒዩማን ራይትስ ዋች አስታወቀ።ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ትናንት ባወጣዉ ዓመታዊ ዘገባዉ እንዳለዉ በጎሪጎሪያኑ 2015 የምሥራቅ አፍሪቃ የሠብአዊ መብት ይዞታ እጅግ የከፋ ነዉ።የአካባቢዉ መንግሥታት የዜጎቻቸዉን መብት እንዲያከብሩ ተማፅኗልም።ነጋሽ መሐመድ ዝርዝር ዘገባ አለዉ።

ርዕሠ-መንበሩ ኒዮርክ-ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘዉ የመብት ተማጓች ድርጅት እንደሚለዉ የታላላቆቹ ሐይቆች አካባቢ ሐገራት መንግሥታት በተሰናበተዉ የጎሪጎሪያኑ 2015 በየዜጎቻቸዉ ላይ የፈፀሙት ግድያ፤ ሥቃይ፤ ግፍ እና በደል ከቀዳሚዎቹ ዓመታት የከፋ ነዉ።ብሩንዲ፤ ሩዋንዳ እና ዩጋንዳ በምርጫ-ሥም፤ ኬንያ በፀረ-ሽብር ትግል ሰበብ ብዙ ሰዎች ተገድለዋል፤ ታስረዋል፤ ተገርፈዋል፤ ተሰደዋልም።

የቡሩንዲዉ የከፋ ነዉ።«አስደንጋጭ» ይሉታል የሁዩማን ራይትስ ዋች የአፍሪቃ ሐላፊ ዳንኤል በቀለ።ጨካኙ እርምጃ የተጀመረዉ ፕሬዝደንት ፔሩ ንኩሪንዚዛ ሕገ-መንግሥት ጥሰዉ ለሰወስተኛ ዘመነ-ሥልጣን እንደሚወዳደሩ ባለፈዉ ሚያዚያ ሲያስታዉቁ ነበር።የኑኩሩንዚዛን አቋም በመቃወም አደባባይ የወጡ ሰዎችን ፀጥታ አስከባሪዎች ይገድሉ፤ያስሩ፤ያሰቃዩ ገቡ።

አራት ራዲዩ ጣቢያዎች ተዘጉ።ነፃ ጋዜጠኞች የሠላዮችን ክትትል፤ የግድያ ዛቻ እና እስራትን ሽሽት ተሰደዱ።አስር የሲቢል ማሕበራት ታገዱ።በመቶ የሚቆጠሩ ሠላማዊ ሰዎች ተገደሉ።ርዕሠ-ከተማ ቡጁምቡራ ብቻ በጅምላ የተቀበረ የአንድ መቶ ሰዎች አስከሬን ተገኝል።ከ230 ሺሕ በላይ ሕዝብ ተሠደደ።

Human Rights Watch Jahresbericht 2015
ምስል picture-alliance/dpa

ብዙዎቹን የሚገድል፤ የሚያስር እና የሚያሰቃየዉ ኢምቦኔራኩሬ የተባለዉ የንኩሪንዚዛ ታማኝ ሚሊሺያ ጦር ነዉ።መገናኛ ዘዴዎች በንኩሪንዚዛ ላይ የሚሰነዘረዉን ትችት፤ ወቀሳ፤ ዉግዘት ሲያራግቡ የጎረቤታቸዉ አቻ ግን ደመኛቸዉ ፖዉል ካጋሚ ልክ እንደ ንኩሪንዚዛ ዘመነ-ሥልጣናቸዉን ለማራዘም ሕገ-መንግሥት እንዲቀየር አስወሰኑ።

ከጋሚ ከንኩሪንዚዛ ሁለት ነገር ዘይደዋል።ተቃዋሚዎቻቸዉን፤ የሲቢል ማሕበራትን፤ ነፃ መገናኛ ዘዴዎችን የደፈለቁት ሕገ-መንግሥት ከማስቀየራቸዉ በፊት በመሆኑ-አንድ፤ ሕገ-መንግሥት ያሻሩት የተማሩት በምርጫ የሚባለዉ ድራማ ከመደረጉ ከሁለት ዓመት በፊት-መሆኑ ሁለት።ጭልጭል የምትለዋን ነፃ መረጃ የሚያሰራጨዉን ኪንያሩዋንዳ የተሰኘዉን የቢቢስን ጣቢም-የኪጋሊዉ መሪ ዘግተዉታል።

ዩጋንዳ የሠላሳ-ዘመን ገዢዋን ዘመነ-ሥልጣን ለማራዘም የተዘጋጀባት ምርጫ ብሎ ግርግር ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን፤ የመብት ተሟጋቾችን፤ ነፃ ጋዜጠኞችን እና የመያድ ሠራተኞችን አበሳ-እያስቆጠረ ነዉ።የኬንያ መንግሥት ከሶማሊያዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ ጋር የገጠመዉን ዉጊያ በተለይ ፀረ-ሽብር ያለዉን ሕግ የሕዝቡን መብት ለመርገጥ ጥሩ-ሰበብ አድርጎታል።-እንደ ሑዩማን ራይትስ ዋች።

Uganda Burundi-Friedensgespräche in Entebbe
ምስል picture-alliance/AP Photo/S. Wandera

ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ እንደ ቀዳሚዎቹ ዓመታት አይክፋ እንጂ የጆሴፍ ካቢላን መንግሥት ሥራ እና አሠራርን የሚተቹ ፖለቲከኛ፤ ጋዜጠኞችና የመብት አቀንቃኞች «ሥፍራ» የላቸዉም-እንደ ሁዩማን ራይትስ ዋች ዘገባ።

 ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ