1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሣምንቱ የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 16 2001

ያለፈው ሣምንት በዓለም ዙሪያ በርከት ያሉ የአትሌቲክስ ውድድሮችም የተካሄዱበት ነበር። ለኢትዮጵያ አትሌቶችም የስኬት ሣምንት ነበር።

https://p.dw.com/p/GziA
ማርሤል ያንሰን፤ የሃምቡርግ የድል ዋስትና
ማርሤል ያንሰን፤ የሃምቡርግ የድል ዋስትናምስል picture-alliance/ dpa

በተለይ በአዳራሽ ውስጥ ሻምፒዮና የኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙዎች ቀደምት አትሌቶች ከክብረ-ወሰን ወደ ክብረ-ወሰን መሻገር እንደያዙ ቀጥለዋል። ከሣምንቱ አስደናቂ ውጤቶች መካከል መሠረት ደፋር በስቶክሆልም የአዳራሽ ውስጥ ውድድር ባለፈው ረቡዕ በአምሥት ሺህ ሜትር አዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን ያስመዘገበችበት ነበር። ኢትዮጵያዊቱ ድንቅ አትሌት ያሻሻለችው ጥሩነሽ ዲባባ ከሁለት ዓመታት በፊት ቦስተን ላይ አስመዝግባ የነበረውን ክብረ-ወሰን ነው።
መሠረት ደፋር ሩጫውን በአስደናቂ ቅልጥፍና በ 14 ደቂቃ ከ 24,37 ሤኮንድ ስትፈጽም ይህም ከቀድሞው ጊዜ በሶሥት ሤኮንዶች ገደማ የፈጠነ መሆኑ ነው። መሠረት በዚሁ ድሏ ከ 2003 ዓ.ም. ወዲህ በአዳራሽ ውስጥ ሳትረታ 18 ሩጫዎችን ማሽነፏ ሲሆን ጥቅጥቅ ብሎ በመላው የኤሪክሰን ግሎብ አሬና የተሰበሰበው ተመልካች የመጨረሻውን ዙር ቆሞ በማጨብጨብ ለግሩሟ አትሌት አድናቆቱን ገልጿል። በዚሁ ሩጫ ሩሢያዊቱ ማሪያ ኮኖቫሎቫ ሁለተኛ ስትወጣ የፖርቱጋሏ አናሊያ ሮዛም ሶሥተኛ ሆናለች።

በስቶክሆልሙ የአዳራሽ ውስጥ ውድድር በ 800 ሜትር ሩጫ ሩሢያዊው የኦሎምፒክ ሻምፒዮን የኦሎምፒክ ብር ሜዳይ ተሸላሚውን ሱዳናዊ ኢስማኢል-አሕመድ-ኢስማኢልን ሲያሽንፍ በአንድ ሺህ ሜትር ደግሞ ሌላው ሱዳናዊ አቡባከር ካኪ ባለድል ሆኗል። በሶሥት ሺህ ሜትር ሩጫ የፈረንሣዩን ቡአብዳላህ ታሂሪንና የካታሩን ጀምስ ኪሩዊን በማስከተል ኬንያዊው ፓውል ኮች ግሩም ድል ሲያስመዘግብ አውስትራሊያዊው የምርኩዝ ዝላይ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ስቲቭ ሁከር በ 5,86 ሜትር አሸናፊ ሆኗል። በተረፈ በወንዶች የከፍታ ዝላይ አሜሪካዊው ጄሤ ዊሊያምስ በ 2,30 ሜትር ሲያሸንፍ የሴቶች የርዝመት ዝላይ ባለድል የሆነችው ደግሞ ሩሢያዊቱ ኦልጋ ኩቼንኮ ነበረች።

የመሠረት ደፋርን ድንቅ ውጤት ከጠቀስን አይቀር ሣምንቱ ቀደም እንዳለው ሰንበት የአብርሃም ጨርቆስና የስንታየሁ ዕጅጉ የቫሌንሢያ ድል ሁሉ ሌሎች የኢትዮጵያ አትሌቶችም ግንባር ቀደም ሆነው የታዩበት ነበር። የ 25 ዓመቱ ደርቤ መርጋ በተባበሩት አረብ ኤሚሮች፤ በራስ-አል-ካልማህ በተካሄደ የአደባባይ ሩጫ በ 15 ኪሎሜትር ውድድር አዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን አስመዝግቧል። ኬንያዊው ፓትሪክ ማካው ደግሞ በግማሽ ማራቶን ሩጫ በዓለም ላይ እስካሁን ሁለተኛው በሆነ ፈጣን ጊዜ አሸንፏል። በነገራችን ላይ በዚህ ርቀት ከሶሥት ዓመታት ወዲህ የዓለም ክብረ-ወሰኑን ይዞ የሚገኘው የማራቶኑ ቁንጮ ሃይሌ ገ/ሥላሴ ነው። በሴቶች ግማሽ ማራቶን ድሬ ጡኔ አሸናፊ ሆናለች።

እንግሊዝ-በርሚንግሃም ላይም ባለፈው ቅዳሜ ዓለምአቀፍ የአዳራሽ ውስጥ ውድድር ተካሂዶ ነበር። በምርኩዝ ዝላይ አቻ የማይገኝላት ሩሢያዊት የለና ኢዚምባየቫ እንደተጠበቀው አሸናፊ ስትሆን የራሷን የአምሥት ሜትር የዓለም ክብረ-ወሰን ግን ለማሻሻል ሳትችል ቀርታለች። ኬንያውያን በወንዶች በ 800 እና 1,500 ሜትር ሩጫ ለድል ሲበቁ በሴቶች 3 ሺህ ሜትርም ቀደምቱ ነበሩ። ከዚሁ ሌላ ጃፓን-ዮኮሃማ ላይ ትናንት በተካሄደ በስድሥት ደረጃ የተከፈለ የማራቶን ርቀት የቡድን ውድድር አስተናጋጇ አገር አሸናፊ ሆናለች። ለጃፓን ድል ዋስትና የሆነችው የመጨረሻውን ደረጃ ሩጫ በቀደምትነት የፈጸመችው የኦሣካ ማራቶን አሽናፊ ዮኮ ሺቡኢ ነበረች።

በዚሁ ውድድር የኬንያ ቡድን ሁለተኛ፤ ሩሢያ አምሥተኛ፤ እንዲሁም አሜሪካ ሰባተኛ ሆናለች። ናይሮቢ ላይ ሰንበቱን በተካሄደ ዓለምአቀፍ አገር-አቁዋራጭ ሩጫ ደግሞ በወንዶች መሰስ ሞሶፕ በሴቶችም ፍሎሬንስ ኪፕላጋት፤ ሁለቱም ከኬንያ አሸናፊ ሆነዋል። ሁለቱ የትዳር ጓደኞች በሚቀጥለው ወር ዮርዳኖስ ላይ በሚካሄደው የዓለም አገር-አቁዋራጭ ሩጫ ውድድር የሚሳተፈውን የኬንያ ቡድን በግንባር ቀደምነት ይመራሉ።

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥ የሚካሄደው ውድድር የሻምፒዮንነቱን ፉክክር እያጠበበ መሄዱን ቀጥሏል። በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን እስከ ቅርቡ በ 12 ነጥቦች ልዩነት በፍጹም ልዕልና ይመራ የነበረው ባርሤሎና ከሣምንት-ሣምንት መንገዳገድ እየያዘ ነው። ባርሣ በገዛ ሜዳው በ 19ኛ ቦታ ላይ በሚገኘው ደካማ የከተማ ተፎካካሪው በኤስፓኞል 2-1 ሲረታ ሬያል ማድሪድ ሻምፒዮን የመሆን ተሥፋውን መልሶ እንዲያጠናክር ሁኔታው መልካም አጋጣሚ ሆኖለታል። ሬያል ማድሪድ በአንጻሩ ቤቲስን 6-1 በሆነ በለየለት ውጤት ሲያሸንፍ ይህም በተከታታይ ዘጠነኛ ድሉ መሆኑ ነው። ከሰንበቱ ውጤት በኋላ የባርሤሎና አመራር በሳባት ነጥቦች ብቻ የተወሰነ ሆኗል። ባርሤሎና ተጫዋቹ ሰይዱ ኬይታ ከእረፍት በፊት ተቀጥቶ ከሜዳ በመውጣቱ ግጥሚያውን በጎዶሎ መፈጸም ነበረበት። በተረፈ ሤቪያ አትሌቲኮ ማድሪድን 1-0 ሲያሸንፍ ራቅ ብሎ በሶሥተኝነት ይከተላል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በአንጻሩ ማንቼስተር ዩናይትድ የሊቨርፑልን ድክመት ተጠቅሞ አመራሩን ወደ ሰባት ነጥብ ከፍ ለማድረግ ችሏል። ማንቼተር ዩናይትድ ብላክበርን ሮቨርስን 2-1 ሲረታ ሊቨርፑል በበኩሉ በገዛ ሜዳው ከማንቼስተር ሢቲይ ጋር ባደረገው ግጥሚያ ከአኩል ለአኩል ውጤት ማለፍ አልቻለም። ባለፉት ሣምንታት መንሸራተት አዘውትሮ የነበረው ቼልሢይ ደግሞ በአዲስ የኔዘርላንድ አሠልጣኙ በጉስ ሂዲንክ አማካይነት ኤስተን ቪላን ግሩም በሆነ ጨዋታ 1-0 ሲያሸንፍ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ሊል በቅቷል። ኤስተን ቪላ አራተኛ ሲሆን አርሰናልና ኤቨርተን ደግሞ አምሥተኛና ስድሥተኛ ሆነው ይከተላሉ።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ የሻምፒዮናው ፉክክር እየጠበበ መሄዱን ቀጥሏል። በየሣምንቱ መፈራረቅ በያዘው የአመራር ፉክክር ቀደምት ለመሆን የበቃው የዚህ ሣምንቱ ተረኛ የቅርብ ተፎካካሪውን ሌቨርኩዘንን ትናንት 2-1 የረታው ሃምቡርግ ነው። ባለፈው ሣምንት በአስደናቂ ጨዋታ ቀደምቱን ቡድን ባየርን ሙንሺንን በማሽነፍ ለቁንጮነት በቅቶ የነበረው በርሊን በቮልፍስቡርግ ሲረታ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ተንሸራቷል። የመጀመሪያው ዙር የበልግ ሻምፒዮን ሆፈንሃይምም ቢሆን ከሽቱትጋርት ጋር ባካሄደው ግጥሚያ በ 3-3 ውጤት በመወሰኑ አመራሩን መልሶ መያዙ አልቀናውም።
ከሰንበቱ ግጥሚያዎች መካከል ውጤቱ ብዙም ያልተጠበቀው በባየርንና በኮሎኝ መካከል የተካሄደው ነበር። ኮሎኝ ባየርንን በገዛ ሜዳው ለዚያውም የበላይነት በማሣየት 2-1 ሲረታ ሣምንቱ ለአስተናጋጁ ክለብ የውርደት፤ ውጤቱን ከልብ ላልጠበቀው ለኮሎኝ ግን ከከተማው የካርኔቫል ፈንጠዝያ ጋር የተጣጣመ ፌስታ ነው የሆነው። አሠልጣኙ ክሪስቶፍ ዳውም ከጨዋታው በኋላ ባልተጠበቀው ድል ያደረበትን ስሜት እንዲህ ነበር የገለጸው።

“የምለውን በትክክል ማስቀመጥ እችል እንደሁ ገና እርግጠኛ አይደለሁም። ሆኖም ለእኔ መጪው ሻምፒዮን የሆነውን ቡድን ማሽነፍ የተለየ ነገር ነው”

ለባየርን ሙንሺን የሰንበቱ ሽንፈት መሪር ነው የሆነው። ቀለል ያለ ተጋጣሚውን በሜዳው ማሽነፍ ባለመቻሉ ከሊጋው አመራር መራቁ ግድ ሆኖበታል። በአጠቃላይ ከ 21 ግጥሚያዎች በኋላ ሃምቡርግ በ 42 ነጥቦች አመራሩን ሲይዝ ሆፈንሃይምና በርሊን በአርባ ነጥብ ሁለተኛና ሶሥተኛ ሆነው ይከተላሉ። ባየርን ሙንሺን በ 38 ነጥብ አራተኛ ነው፤ ሌቨርኩዝን ሁለት ነጥቦች ወረድ ብሎ በአምሥተኝነት ይከተላል። ግን ከአንደኛ እስከ ስድስተኛው ቦታ ያለው የነጥብ ልዩነት በስድሥት ብቻ የተወሰነ ሲሆን ሣምንት አሰላለፉ መልሶ ሊገለባበጥ የሚችል ነው። ስድሥቱም ክለቦች በሙሉ ሻምፒዮን የመሆን ተጨባጭ ዕድል አላቸው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ መላው ቀደምት ቡድኖች ጨዋታዎቻቸውን በማሸነፋቸው በሣምንቱ የተለወጠ ነገር የለም። ኢንተር ሚላን ከቦሎኛ 2-1፤ ጁቬንቱስ ከፓሌርሞ 2-0፤ ኤ.ሢ.ሚላን ከካልጋሪ 1-0 ሲሸናነፉ ፊዮሬንቲናና ቬሮና ደግሞ 2-1ተለያይተዋል። በአጠቃላይ ኢንተር በዘጠኝ ነጥብ ልዩነት ሊጋውን መምራቱን ይቀጥላል፤ ጁቬንቱስ ሁለተኛ፤ ኤ.ሢ.ሚላን ሶሥተኛ፤ ፊዮሬንቲና አራተኛ ነው።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ሻምፒዮኑ ኦላምፒክ ሊዮን ናንሢይን 2-0 ሲረታ የቅርብ ተፎካካሪዎቹ ከእኩል ለእኩል ውጤት ባለማለፋቸው አመራሩን ወደ ስድሥት ነጥብ ማስፋቱ ተሳክቶለታል። ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ ፓሪስ ሣን-ዣርማን ሁለተኛ፤ ማርሤይ ሶሥተኛ በመሆን ይከተላሉ። በኔዘርላንድ ሻምፒዮና አመራሩን እንደያዘ የቀጠለው አልክማር ጨርሶ የሚበገር አልሆነም። አልክማር የሰንበት ግጥሚያውን ሲያሸንፍ ሻምፒዮናው ሊጠናቀቅ አሥር ጨዋታዎች ቀርተው ሳሉ በዘጠኝ ነጥቦች ልዩነት አየመራ ነው።

ትዌንቴ-እንሼዴ ሁለተኛ ሲሆን የሚያስገርም ሆኖ ሁለቱ ቀደምት ክለቦች አያክስ አምስተርዳምና አይንድሆፈን ከታች ወደ ላይ ተመልካቾች ናቸው። በፖርቱጋል ሊጋ ፖርቶ በአራት ነጥብ ልዩነት ይመራል፤ ሁለተኛ ቤንፊካ ሊዛቦን ነው። የቀደምቱ ዲቪዚዮኖች ይዞታ ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ ከሞላ-ጎደል ይህን የመሰለ ሲሆን አውሮፓ ነገና ከነገ በስቲያም የተለያዩ ማራኪ ግጥሚያዎች የሚካሄዱባት መድረክ ናት። በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ተጣርተው የቀሩት 16 ቡድኖች በሙሉ ጠንካሮች ሲሆኑ ተከታዮቹ የጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎች የተመልካችን ስሜት ከመጠን በላይ የሳቡ ናቸው።

በነገው ምሽት ኢንተር ሚላን ከማንቼስተር ዩናይትድ፤ ኦላምፒክ ሊዮን ከባርሤሎና፤ አትሌቲኮ ማድሪድ ከፖርቶ፤ አርሰናል ከሮማ ይጋጠማሉ። በማግሥቱ ረቡዕ ደግሞ ቼልሢይ ከጁቬንቱስ፤ ሬያል ማድሪድ ከሊቨርፑል፤ ስፖርቲንግ ሊዝበን ከባየርን፤ እንዲሁም ቪላርሬያል ከፓናቴናኢኮስ አቴን ቀጣዮቹ ተጋጣሚዎች ናቸው። ታላቆቹን ግጥሚያዎች በዓለም ዙሪያ አያሌ ሕዝብ በቴሌቪዥን አማካይነት እንደሚከታተል አንድና ሁለት የለውም።

በቴኒስ ለማጠቃለል አሜሪካዊው ኤንዲይ ሮዲክ ትናንት ሜንፊስ ውስጥ በተካሄደ የፍጻሜ ግጥሚያ የቼክ ተጋጣሚውን ራዴክ ስቴፓኔክን በሁለት ምድብ ጨዋታ በመርታት አሽናፊ ሆኗል። በቡዌኖስ አይርስ ኦፕን ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ የስፓኙ ቶሚይ ሮብሬዶ የአርጄንቲና ተጋጣሚውን ሁዋን ሞናኮን ሲረታ ቦጎታ ላይ በተካሄደ የዓለም ቴኒስ ማሕበር ፍጻሜም እንዲሁ የስፓኛ ሆሴ-ማርቲኔዝ-ሣንቼዝ 6-3, 6-2 በሆነ የለየለት ውጤት አርጄንቲናዊቱን ጊዜላ ዱልኮን ለማሸነፍ በቅታለች።