1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሣምንቱ የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 23 2001

ዓለምአቀፉ የአዳራሽ ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድር ባለፈው ሣምንትም የሚደነቁ ውጤቶች የተመዘገቡበት ነበር። መሠረት ደፋር በጥቂት ቀናት ውስጥ ለሁለት አዳዲስ የዓለም ክብረ-ወሰኖች በቅታለች።

https://p.dw.com/p/H48k
ከመሃል፤ የብሬመን ተከላካይ ናልዶ
ከመሃል፤ የብሬመን ተከላካይ ናልዶምስል AP

ከኢትዮጵያ ድንቅ የመካከለኛና የረጅም ርቀት ሩጫ ከዋክብት አንዷ መሠረት ደፋር የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር በፊታችን ነሐሴ በሚካሄድበት በዚህ ዓመት ብርቱ ጥንካሬ ማሣየቷን እንደቀጠለች ነው። መሠረት ከሣምንት በፊት በስቶክሆልም ዓለምአቀፍ የአዳራሽ ውስጥ የ 5 ሺህ ሜትር ሩጫ አዲስ ክብረ-ወሰን ስታስመዘግብ ባለፈው ሐሙስም ፕራግ ላይ በተካሄደ ውድድር በተመሳሳይ ሁኔታ የሁለት-ማይል ባለድል ሆናለች። ኢትዮጵያዊቱ አትሌት ፕራግ ላይ ያሻሻለችው ከአንድ ዓመት በፊት ቦስተን ላይ ያስመዘገበችውን የራሷን ክብረ-ወሰን ነበር። በጥቂት ቀናት ውስጥ ሁለት የዓለም ክብረ-ወሰን፤ እጅግ የሚደነቅ ነው።

በፕራጉ ውድድር ወጣቱ አብርሃም ጨርቆስም በ 5 ሺህ ሜትር ሩጫ ኬንያዊ ተፎካካሪውን ፓውል ኮችን ቀድሞ ሲያሽንፍ በካና ዳባ ደግሞ ሶሥተኛ ሆኗል። ይህም ለኢትዮጵያ አትሌቶች ተጨማሪ ስኬት ነው። በተረፈ በ 800 ሜትር ሱዳናዊው ኢስማኢል-አሕመድ-ኢስማኢል ሁለት ኬንያውያንን አስከትሎ ሲያሸንፍ የአገሩ ልጅ አቡባከር ካኪም በሺህ ሜትር ሩጫ ባለድል ሆኗል። በምርኩዝ ዝላይ አሸናፊ የሆነችው አሁንም አቻ ያልተገኘላት የሩሢያ የዓለም ሻምፒዮን የለና ኢዚንባየቫ ነበረች። ከዚሁ ሌላ በወንዶች የ 60 ሜትር ሩጫ የብሪታኒያው ክሬይግ ፒከሪንግ ቀዳሚ ሲሆን በዚሁ አጭር ርቀት መሰናክልም አሜሪካዊው ዴክስተር ፋውልክ አሸናፊ ሆኗል።

ጃፓን ከተማ ኦትሱ ላይ ትናንት በተካሄደ የማራቶን ሩጫ ኬንያዊው ፓውል ቴርጋት አሸናፊ ሆኗል። ቴርጋት ያሸነፈው በስፍራው ሁለት ጊዜ ባለድል የነበረውን የስፓኝ ተፎካካሪውን ሆሴ ሪዮስን በመጨረሻው ኪሎሜትር ላይ ቀድሞ በማምለጥ ነው። የትናንቱ ውድድር ለቴርጋት በዚህ ዓመት የመጀመሪያው ሲሆን ኬንያዊው አትሌት በሁለት ሰዓት ከአራት ደቂቃ ከ 55 ሤኮንድ ከሃይሌ ገብረ ሥላሴ ቀጥሎ በዓለም ላይ የሁለተኛው ፈጣን የማራቶን ጊዜ ባለቤት መሆኑ ይታወቃል። ሁሴ ሪዮስ ሩጫውን በሁለተኝነት ሲጨርስ ኤርትራዊው ያሬድ አሥመሮም ደግሞ ሶሥተኛ ወጥቷል።

ሌላው በትናንቱ ዕለት ስፓኝ ውስጥ የተካሄደው የባርሤሎና ማራቶን በአንድ የአየርላንድ ሯጭ ሞት የተነሣ ሃዘን የጋረደው ሆኖ አልፏል። የ 27 ዓመቱ ተወዳዳሪ ኮሊን ዳን በልብ ችግር ምክንያት የሞተው 34 ኪሎሜትር ያህል ከሮጠ በኋላ ነው። የቀይ መስቀል የጤና ባለሙያዎች ፈጥነው ከስፍራው ቢደርሱም ሊያተርፉት አልቻሉም። ለማንኛውም ሩጫው በታቀደው መሠረት ሲጠናቀቅ ኬንያዊው ጆንስተን ቼቢ አሸናፊ ሆኗል። በዚሁ ሰንበት ቦስተን ላይ በተካሄደ የአሜሪካ የአዳራሽ ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ የሁለት ጊዜው የኦሎምፒክ ሜዳይ ተሸላሚ ቴረንስ ትሬምል በ 60 ሜትር መሰናክል ሩጫ የዓመቱን ፈጣን ሰዓት አስመዝግቧል።

በዚሁ ውድድር በሴቶችም ያሸነፈችው በቤይጂንግ ኦሎምፒክ ተሰናክላ የሜዳሊያ ዕድሏን ያጣችው አሜሪካዊቱ የአዳራሽ ውስጥ የዓለም ሻምፒዮን ሎሎ ጆንስ ነበረች። በሴቶች ምርኩዝ ዝላይ የኦሎምፒክ የብር ሜዳይ ተሸላሚዋ ጄን ስቱቺንስኪ አዲስ ብሄራዊ ክብረ-ወሰን በማስመዝገብ አሸንፋለች። በሣምንቱ አጋማሽ አቴን ላይ ተካሂዶ በነበረ የዳራራሽ ውስጥ ውድድርም የአሜሪካ ወንዶችና ሴት አትሌቶች በ 60 ሜትር ሩጫ ጎልተው ሲታዩ የኬንያና የሩሢያ ተወዳዳሪዎችም ጥሩ ውጤት አስመዝግበዋል። ሰንበቱን አውስትራሊያ-ሢድኒይ ላይ በተካሄደ ውድድር ደግሞ የአገሪቱ የምርኩዝ ዝላይ የዓለም ሻምፒዮን ስቲቭ ሁከር 5,95 ሜትር በመዝለል አሸንፏል።

እግር ኳስ

ባለፈው ሣምንት አጋማሽ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አያሌ የቴሌቪዥን ተመልካቾችን ትኩረት የሳቡ የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ግጥሚያዎች ተካሂደዋል። በመጨረሻዎቹ ክለቦች መካከል በተካሄዱት ግጥሚያዎች በተለይ የእንግሊዝ ክለቦች የተለየ ጥንካሬ ሲያሳዩ እንዳለፈው ዓመት ሁሉ እስከመጨረሻው የመዝለቅ ትልቅ ዕድል ያላቸው ነው የሚመስለው። ቼልሢይ ጁቬንቱስን 1-0 ሲረታ ሊቨርፑልም የስፓኙን ሻምፒዮን ሬያል ማድሪድን በገዛ ሜዳው በተመሳሳይ ውጤት አሸንፏል። ሌላው በሻምፒዮናው ሊጋ ውድድር የተሣካ ሣምንት ያሳለፈው የእንግሊዝ ክለብ ሮማን 1-0 የረታው አርሰናል ነበር።

ማንቼስተር ዩናይትድ ደግሞ ከኢጣሊያው ሻምፒዮን ከኢንተር ሚላን ጋር በውጭ ሜዳ ባዶ ለባዶ በመለያየት ወደፊት ለመዝለቅ አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል። የተቀሩት የስፓኝ ክለቦች ከሬያል ሽንፈት ባሻገር በሙሉ ከእኩል ለእኩል ውጤት አላለፉም። ቪላርሬያል ከፓናቴናኢኮስ አቴን 1-1፤ አትሌቲኮ ማድሪድ ከፖርቶ 2-2፤ እንዲሁም ኦላምፒክ ሊዮን ከባርሤሎና 1-1 ተለያይተዋል። በአንጻሩ ከሁሉም በላይ አስተማማኝ ድል የተጎናጸፈው ስፖርቲንግ ሊዝበንን 5-0 ያከናነበው የጀርመኑ ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺን ነው። የመልሶቹ ግጥሚያዎች ይበልጥ ፈታኝና ማራኪ እንደሚሆኑ የሣምንቱ ጠባብ ውጤቶች ከወዲሁ የሚያመለክቱ ናቸው።

በ UEFA ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎች ደግሞ የፈረንሣይ ክለቦች አይለው ሲታዩ ከጀርመን አራት ተወዳሪዎች ሁለቱ ከወዲሁ ተሰናብተዋል። በዚህ ውድድር ብዙዎች ተመልካቾችን ያስደነቀው በከዋክብት የተመላው የኢጣሊያ ክለብ ኤ.ሢ.ሚላን የጀርመን ተጋጣሚውን ብሬመንን 2-0 ከመራ በኋላ በመጨረሻ ለዚያውም በገዛ ሜዳው 2-2 ሆኖ በአጠቃላይ ውጤት ከውድድሩ መውጣቱ ነው። በተረፈ 16 ክለቦች ከአሥር ቀናት በኋላ ለሚካሄደው ቀጣይ ውድድር ሲያልፉ ባለፈው ሐሙስ በወጣው ዕጣ መሠረት ከሚገናኙት ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው። ቬርደር ብሬመን ከሣንት ኤቲየን፤ ኡዲኔዘ ካለፈው ዓመት ሻምፒዮን ከሣንት ፔተርስቡርግ፤ ኦላምፒክ ማርሤይ ከአያክስ አምስተርዳም፤ ሃምቡርግ ከጋላታሣራይ ኢስታምቡል!

በዚሁ ወደ የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች መደበኛ ግጥሚያዎች እንመለስና ሰንበቱ መሪዎቹ ቡድኖች በአብዛኛው ደክመው የታዩበት ሆኖ አልፏል። እርግጥ የነጥቡ ልዩነት መጥበብ ሻምፒዮናውን ይበልጥ አጓጊ የሚያደርግ ነው። በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ከጥቂት ሣምንታት በፊት እስከ 12 ነጥብ ደርሶ የነበረው የባርሤሎና አመራር ወደ አራት ነጥብ አቆልቁሏል። ባርሤሎና ከዚህ የደረሰው በአትሌቲኮ ማድረድ በመሽነፉ ነው። የቅርብ ተከታዩ ሬያል ማድሪድ በአንጻሩ ኤስፓኞልን 2-0 በመርታት በተከታታይ ባገኘው አሥረኛ ድል የሁኔታው ተጠቃሚ ሆኗል። እስከቅርቡ ለባርሤሎና የለየለት መስሎ የታየው ሻምፒዮና በሁለቱ ክለቦች የጦፈ ፉክክር የሚቀጥል ነው የሚመስለው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንችተር ዩናይትድ አንድ ጨዋታ ጎሎት በሰባት ነጥብ ልዩነት ይመራል። ሁለተኛው ሊቨርፑል በሚድልስቦሮህ 2-0 ሲረታ የሻምፒዮንነት ተስፋው ቀስ በቀስ እየመነመነ ነው። ቼልሢይ በአንጻሩ ዊጋን አትሌቲክን በማሸነፍ በጎል ልዩነትም ቢሆን ሊቨርፑልን ከሁለተኛው ቦታ ለመፈንቀል በቅቷል። ኤስተን ቪላና አርሰናል ወረድ ብለው ይከተላሉ። በኢጣሊያ ሊጋ ኢንተር ሚላን ከሮማ 3-3 ብቻ ሲለያይ አመራሩ ከዘጠኝ ወደ ሰባት ነጥብ ዝቅ ብሏል። የኢንተር ድክመት የበጀው ናፖሊን 1-0 ላሸነፈው ለጁቬንቱስ ነው። ኤ.ሢ.ሚላን በአንጻሩ ከሣምንቱ አጋማሽ የ UEFA ክስረቱ በኋላ በሣምፕዶሪያ 2-1 ተሸንፎ በጣሙን አቆልቁሏል። ከኢንተር የሚለዩት አሁን 12 ነጥቦች ናቸው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ሄርታ-በርሊን ከሣምንት በፊት ለሃምቡርግ አስረክቦ የነበረውን አመራር እንደገና ለመጨበጥ ችሏል። ሃምቡርግ ትናንት በቮልፍስቡርግ 3-1 ሲረታ በርሊን ወደ አመራሩ የተመለሰው ሙንሺንግላድባህን 2-1 በማሽነፍ ነው። በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የቀናው ባየርን ሙንሺን በሌላ በኩል ለዚያውም በገዛ ሜዳው ከ 15ኛው ደቂቃ ጀምሮ በጎዶሎ የተጫወተውን ብሬመንን ማሸነፍ ተስኖት ባዶ-ለባዶ ሲለያይ የሰንበቱ አቆልቁዋይ ቡድን ነው። ዳኛው የብሬመኑን ብራዚላዊ ተከላካይ ናልዶን ከሜዳ ያስወጣበት ሁኔታ ብዙ እያከራከረ ነው። በአጠቃላይ በርሊን አንደኛ፤ ሃምቡርግ ሁለተኛ፤ ሆፈንሃይም ሶሥተኛ ሲሆኑ፤ የሣምንቱ ዋነኛ ተጠቃሚ ወደ አራተኛው ቦታ ብቅ ያለው ቮልፍስቡርግ ነው። ሻምፒዮኑ ባየርን ሙንሺን ግን ወደ አምሥተኛው ቦታ ወርዷል።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን አመራሩን እንደያዘ የቀጠለው ኦላምፒክ ሊዮን በእኩል ለእኩል ውጤት በመወሰኑ በተከታታይ ለስምንተኛ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን በያዘው ግቡ ሁለት ጥቃሚ ነጥቦችን አጥቷል። በተረፈ በኔዘርላንድ ሻምፒዮና ዘንድሮ አልክማርን የሚያቆም አልተገኘም። አልክማር በዚህ ሰንበትም ግሮኒንገንን 3-0 ሲረታ ውድድሩ ሊያበቃ ዘጠን ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ በዘጠኝ ነጥቦች ይመራል። በፖርቱጋል ሻምፒዮና በአንጻሩ የፖርቶ አመራር ከስፖርቲንግ ባዶ ለባዶ በመለያየቱ ወደ ሁለት ነጥብ ሊያቆለቁል በቅቷል።

ቴኒስ

አሜሪካዊው ማርዲይ ፊሽ ትናንት ፍሎሪዳ-ዴልሬይ-ቢች ላይ በተካሄደ ዓለምአቀፍ ፍጻሜ ግጥሚያ የሩሢያ ተጋጣሚውን ኤቭጌኒይ ኮሮሌቭን በሁለት ምድብ ጨዋታ አሸንፏል። ፊሽ በዚህ ውድድር በማሸነፍ ከስድሥት ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው አሜሪካዊ መሆኑ ነው። በሜክሢኮ የአካፑልኮ ዓለምአቀፍ ውድድር ደግሞ የስፓኙ ተወላጅ ኒኮላስ አልማግሮ ፈረንሣዊውን ጌል ሞንፊልስን በማሸነፍ ለሁለተኛ ተከታታይ ድሉ በቅቷል። በሴቶች ፍጻሜ ቬኑስ ዊሊያምስ የኢጣሊያ ተጋጣሚዋን ፍላቪያ ፓኔታን አሸንፋለች። በሌላ የዱባይ ሻምፒዮና የሰርቢያው ኮከብ ኖቫክ ጆኮቪች የስፓኝ ተጋጣሚውን ዴቪድ ፌሬርን በሁለት ምድብ ጨዋታ በመርታት ካለፈው ሕዳር ወር ወዲህ ለመጀመሪያ ድሉ በቅቷል።

በቢስክሌት እሽቅድድም ለማጠቃለል የቤልጂጉ ተወላጅ ቶም ቡነን ትናንት በአገሩ ከኩርን-ብራስልስ-ደርሶ-መልስ እሽቅድድርም የወቅቱን የመጀመሪያ ድል ተጎናጽፏል። ቡነን የ 2005 ዓ.ም. የዓለም ሻምፒዮን ነው። 194 ኪሎሜትር ርቀት ባለው ውድድር ሁለት መቶ ገደማ የሚጠጉ ቢስክሌተኞች ሲሳተፉ የአውስትሪያው በርናርድ አይዝልና የብሪታኒያው ጀረሚይ ሃንት እሽቅድድሙን ሁለተኛና ሶሥተኛ በመሆን ፈጽመዋል። በዚያው በቤልጂግ ባለፈው ቅዳሜ ተካሂዶ በነበረ የጌንት ከተማ ዙር ውድድር ደግሞ ከ 205 ኪሎሜትር በኋላ የኖርዌዩ ተወላጅ ቶር ሁስሆፍድ አመራሩን ይዟል። በኢጣሊያ የሣርዲኒያ ዙር ውድድርም ዳኒየሌ ቤናቲ አራተኛውን ደረጃ የ 147 ኪሎሜትር እሽቅድድም በማሸነፍ በአጠቃላይ ነጥብ እየመራ ነው።