1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አድማው የተጠራው የገቢ ግብር፤የፖለቲከኞችን አያያዝ እና የድንበር ማካለልን በመቃወም ነው

ረቡዕ፣ ነሐሴ 17 2009

ለአምስት ቀናት ተጠርቷል የተባለው የኦሮሚያ ክልል የስራ ማቆም አድማ ከአሰቦት እስከ በዴሳ ከሰበታ እስከ ምሥራቅ ሐረርጌዋ ቆቦ ድረስ ጫናው ተሰምቷል። የአይን እማኞች እንደሚሉት ሱቆች ተዘግተዋል፤የመጓጓዣ አገልግሎትም ተቆራርጧል። መደበኛ ሥራቸውን ለመከወን ሱቃቸውን የከፈቱ ጭሮን በመሳሰሉ ከተሞች በተቃዋሚዎች ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል 

https://p.dw.com/p/2iijc
Äthiopien Geschäfte streiken wegen Steuergesetz in Oromiya (Ambo)
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

ቃለ ምልልስ ስለ ኦሮምያው አድማ እና ተቃውሞ ከዘጋቢያችን ጋር

ከአዲስ አበባ ጅቡቲ በተዘረጋው አውራ ጎዳና ላይ የምትገኘው አሰቦት ገበያዋ ቀዝቅዞ የየጸጥታ ኃይሎች ሲዘዋወሩባት ውለዋል። የከተማዋ ነዋሪ እንደሚሉት በተለምዶ ባጃጅ ተብለው የሚጠሩት ባለሶስት እግር ታክሲዎች የወትሮ ሥራቸውን አይከውኑም። የሕዝብ መጓጓዣ አውቶቡሶች ከመናኸሪያ ጠፍተዋል። 
"እንግዲህ ዛሬ የአሰቦት ከተማ እንዳለ ሱቆቹ ዝግ ነው። የልብስ፤የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች ዝግ ናቸው። አንድ መኪና መናኻሪያ ውስጥ የለም። ባጃጆቹም እንዳለ የሉም። መኪኖቹም የሉም። ወዲያ ወዲህ እየሮጡ ያሉት ፖሊሶች ብቻ ናቸው። ሌላ ጊዜ እዚህጋ ጫት በጣም ይሰራ ነበረ። 15 የማያንሱ መኪናዎች ናቸው ጫት ጭነው ወደ አፋር ከዚህ የሚወጡት። ያ ጫት ግን ዛሬ እንዳለ የለም።"
አሰቦትን ጸጥ ረጭ ያደረጋትን የሥራ ማቆም አድማ ሐሮማያም ሰምታለች። የከተማዋ ነዋሪ የግብይት ማዕከላት መዘጋታቸውን ከሌሎች አካባቢዎች የሚገቡ ሸቀጦችም አለመኖራቸውን ይናገራሉ።"ምንም የሚንቀሳቀስ ሰው የለም። ሁሉም እንዳለ ዝግ ነው። ከጠዋት ጀምሮ አንድ የተከፈተ በር የለም። ትናንትና ገበያ ሞቅ ያለ ነው። አገሪቷ በጫት ትታወቃለች። ሻይ ቅጠል አልገባም ዛሬ።"
ከአዲስ አበባ ወደ አምቦ እና ነቀምት የሚጓዙ ተሽከርካሪዎችም እንደ ወትሮው አገልግሎቶቻቸውን መስጠት አልሆነላቸውም። ለሥራ ወደ ሰበታ ብቅ ብዬ ነበር የሚሉት የአካባቢው ነዋሪ የተጠራውን የሥራ ማቅም አድማ ጥሷል የተባለ የሕዝብ መጓጓዣ አውቶቡስ በወጣቶች ጥቃት ተፈፅሞበታል።
"ለስራ ወደ ሰበታ እና ወደ ቡራዩ ሔጄ ነበር። ሱቆች እና መጓጓዣ የለም። አለም ገና ሰበታ የኦሮሚያ ቄሮዎች አንድ አውቶቡስ ላይ እርምጃ ወሰዱ። አውቶቡሱ የሕዝብ መመሪያ ጥሶ ነበር።"
በምሥራቅ ሐረርጌዋ ቆቦ ከተማ የጸጥታ ኃይሎች የተዘጉትን ሱቆች ለማስከፈት ሲሞክሩ ማርፈዳቸውን የአይን እማኞች ተናግረዋል። የየከተሞቹ ነዋሪዎች እንደሚሉት ምግብ ቤቶች፤ጫት ቤቶች እና መደብሮች ተዘግተው ውለዋል። የሥራ ማቆም አድማው በማኅበራዊ ድረ-ገፆች እና በውጪ አገራት በሚገኙ የተቃዋሚ መገናኛ ብዙኃን መተላለፉን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። ላለፉት ሁለት አመታት ተቃውሞ እና ኹከት በታየበት የኦሮሚያ ክልል አሁን እንዳዲስ የተጠራው የሥራ ማቆም አድማ የገቢ ግብር፤በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞች አያያዝ እና የድንበር ማካለልን ለመቃወም ያለመ ነው።
በዴሳ እና ጭሮ ላይ የሥራ ማቆም አድማውን ችላ ብለው አገልግሎት ለመስጠት የሞከሩ ጥቃት ገጥሟቸዋል። በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የጭሮ ከተማ ነጋዴ እንደሚሉት ሱቆቻቸውን በመክፈታቸው የተቃዋሚዎች፤ በመዝጋታቸው ደግሞ የጸጥታ ኃይሎች ዒላማ ሆነዋል። 
በዶይቼ ቬለ የፌስ ቡክ ገፅ ባደረግንው ውይይት ሙሴ ተፈራ የተባሉ የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚ "ከሰሜን በኩል ዛሬ አዲስ አበባ ገብቻለሁ። ምንም የተለዬ ነገር አላዬሁም!" ብለዋል። ጃፋር ቢልሱማ ደግሞ "እኔ ምኖርበት አከባቢ ጠዋት ላይ የተወሰኑ የሰፈር ሱቆች ተክፍቶ ነበር። ነገር ግን ቄሮዎች በሰጡት ማሰጠንቀቂያ መሠረት ወድያዉኑ ተዘግቷል፡፡" የሚል አስተያየት አስፍረዋል። ውጭ የሚኖሩ እና ሀገር ውስጥ ቄሮ በሚል ስም ይንቀሳቀሳሉ የተባሉ ኃይላት የጠሩትን የሥራ ማቆም አድማ በአንዳንድ ከተሞች እና አካባቢዎች የሚኖረው ህዝብ  ተቀብሎ  ዛሬ አድሞ ሲውል በሌሎች አካባቢዎች ግን የወትሮው እንቅስቃሴ ብዙም አለመደናቀፉን የአዲስ አበባ ዘጋቢያችን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር ነግሮናል። 

Äthiopien Proteste | Ambo Town
ምስል DW/M. Yonas Bula

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር 

እሸቴ በቀለ 

ነጋሽ መሐመድ