1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

Merga Yonas Bula
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 27 2009

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ካቢኔ አባላት ትላንት ባካሄዱት አስቸኳይ ስብሰባ በክልሉ ያለዉን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ 6,6 ቢሊየን ብር እንዲመደብ መወሰናቸዉ ተሰምቷል።

https://p.dw.com/p/2VLz2
Oromo Proteste in Äthiopien
ምስል Oromia Media Network

Employment Budget for Oromia - MP3-Stereo

በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የሚመራዉ የኦሮሚያ የሥራ ዕድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ምክር ቤት የተሰኘዉ በዛሬዉ ዕለት ባደረገዉ ስብሰባ ባጠቃላይ 1.273 ሚልዮን የሚሆን የሥራ ዕድል የመፍጠር እቅድ እንዳፀደቀ በኦሮሚያ የሥራ ዕድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አዋሉ አብዲ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል።

መንግሥት የሥራ ዕድል ለመፍጠር ስልትና መመሪያ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ቢቆይም የተፈለገዉ ደረጃ ላይ መድረስ አለመቻሉንም አቶ አዋሉ ይናገራሉ።

በቅርቡ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት አቶ ሙላቱ ተሾመ መንግሥት ለሥራ ፈጠራ 10 ቢሊዮን በጀት ማዘጋጀቱን ይፋ አድርገዉ ነበር።  አሁን የተገኘዉ 6.6 ቢሊዮን ብር ከተለያዩ ምንጮች መምጣቱን የሚናገሩት አቶ አዋሉ፤ ከተባለዉ 10 ቢሊዮን ኦሮሚያ ድርሻዉን ወስዷል ይላሉ።

ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት በሙያቸዉ ወይም መሥራት በሚችሉበት አካባቢ የምልመላ፣ የስልጠናና የማደራጀት ሥራዎች እየተሰሩ ነመሆኑን አቶ አዋሉ ይናገራሉ። 
ይሁን እንጅ በክልሉ የሚኖሩ አንዳንድ ወጣቶች ይህ የተበጀተ ገንዘብ በክልሉ ተከስቶ የነበረዉን የፖለቲካ ቀዉስ ለማረጋጋት ተብሎ የታቀደ እንጅ ከመሠረቱ ለወጣቱ ሥራ ፈጠራ ተብሎ አይደለም ይላሉ።

በኦሮሚያ መስተዳደር ስር በምትገኘዉ የከሚሴ ከተማ  ነዋሪ የሆኑት ስማቸዉ እንዳይጠቅስ የፈለጉት ግለሰብ ቀደም ሲል መምህር እንደነበሩ ገልጸዉ አሁን ግን ሥራ አጥ ነኝ ይላሉ። «እዉነት ለመናገር ስለ ገንዘቡ እስካሁን የሰማሁት ነገር የለም። ግን ይህ መንግስት ለማህበረሰቡ የሚፈይደዉ ነገር የለም» በማለት እኝህ ግለሰብ አስተያየታቸዉን ሰንዝረዋል።

ሌላዉ የአዳማ ነዋሪ የሆኑት የኦሮሚያ ክልል ለሥራ ፈጠራዉ የመደበዉን ገንዘብ መስማታቸዉን ተናግረዉ ባለፈዉ ዓመትም ክልሉ ተመሳሳይ ቃል ገብቶ ሳያሳካ ቀርተዋል ሲሉ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል።ይህ ለወጣቶች የታቀደ ሳይሆን በክልሉ ያለዉን አለመረጋጋት ለማብረድ ነዉ ይላሉ።

አቶ አዋሉ ግን ሥራ የመፍጠሩ ጉዳይ አሁን አገሪቱ ዉስጥ ከተፈጠረዉ የፖለቲካ ተቃዉሞ ጋር አይያዝም ይላሉ።

በክልሉ እንደሚኖሩ የገለፁ ግለሰቦች ጉዳዩን በተመለከተ በዶቼ ቬለ ድረ ገፅ ላይ አስተያየታቸዉን አጋርተውናል። «ጥሩ መንገድ ነው ነገር ግን ይሄ ብቻ በቂ አይመስለኝም። ምክንያት የሰብአዊ መብት ረገጣ ጭምር መሠራት ያለበት ጉዳይ ስለሆነ በተጨማሪ ይሄ ተሐድሶ በተደጋጋሚ ሚነሳው በወሬ ሳይሆን መሬት ላይ መውረድ አለበት፣» ያሉ ሲኖሩ ሌሎች ደግሞ «መንግሥት የወጣቱን ጥያቄ መቼ ተረድቶ ነው ገንዘብ የሚመድበው? የሚመሥለኝ ለአፍ መዝጊያ የሚሆን ነው የመደበው»።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሰ