1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የሥራ ፈላጊዎች ምዝገባ በአዲስ አበባ

ዓርብ፣ ጥር 26 2009

የኢትዮጵያ መንግሥት ቤት ለቤት በመዘዋወር ስራ ፈላጊዎችን እየመዘገበ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሰራተኞች በአዲስ አበባ ከተማ ቤት ለቤት በመዘዋወር ሥራ ፈላጊዎችን በመመዝገብ ላይ ናቸው። ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥት መሰል ምዝገባዎች ማካሔዱን የሚያስታውሱት ወጣቶች ግን እርምጃው ከምዝገባ ስለማለፉ ጥርጣሬ አላቸው።

https://p.dw.com/p/2WsdX
Addis Ababa (Äthiopien)
ምስል picture alliance/landov

M M T/ Addis Ababa city administration is registering job seekers - MP3-Stereo

አዲስ አበባ ከተማ ሥራ ፈላጊ ዜጎቿን እየመዘገበች ነው። የከተማዋ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ እከ አመቱ መጨረሻ ድረስ ከ60,000-70,000 የሚደርሱ ሥራ ፈላጊዎችን ለመመዝገብ ማቀዱን አስታውቋል። መንደር ለመንደር ተዘዋውረው የመኖሪያ ቤት አንኳኩተው ሥራ ፈላጊዎችን ከሚመዘግቡ መካከል አንዱ አቶ ገዳሙ አስረስ ናቸው። በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የወረዳ 01 የሰራተኛ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ ፅ/ቤት ሰራተኛ ናቸው። በጥቃቅንና አነስተኛ፤በሰራተኛ እና ማህበራዊ እንዲሁም ሴቶች እና ስፖርት ፅ/ቤቶች ትብብር በዘመቻ ሁሉንም ሥራ ፈላጊዎች እየመዘገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

በአዲስ አበባ ከተማ በመምህርነት የሚያገለግሉት አቶ ሰጠ ተበጀም የመንግሥት ሰራተኞች ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ ሥራ አ ጦችን በመመዝገብ ላይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። የከተማ አስተዳደሩ ባሉት ሁሉም የመንግሥት አደረጃጀት  በኩል ምዝገባው እየተካሔደ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሰጠ ጉዳዩ አዲስ እንዳልሆነ ይናገራሉ። የምርጫ ወቅት ሲደርስ ሥራ አጦችን መለየት፤ማደራጀት እና ሥልጠና መስጠት የተለመደ እንደሆነ የሚያስታውሱት አቶ ሰጠ «በርካታ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት የመሥሪያ ቦታ እና የብድር አቅርቦ እጦት» ምክንያት ወጣቶቹ ወደ ሥራ እንደማይገቡ ተናግረዋል።
የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ፅ/ቤት ሰራተኛው ምዝገባው በተለይ በወጣቶች ዘንድ የተደበላለቀ አቀባበል እንደተደረገለት ይናገራሉ። «ብዙ ጊዜ እንመግባለን ትላላችሁ ነገር ግን ተግባራዊ አታደርጉትም።» የሚሉትን ጨምሮ ጉዳዩን በመልካም ስሜት የተቀበሉትም መኖራቸውን ገልጠዋል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ለወራት የዘለቀ ተቃውሞ ከገጠመው በኋላ በዚህ ዓመት መጀመሪያ በተለይ ለወጣቶች የሥራ ፈጠራ የሚውል የ10 ቢሊዮን ብር መመደቡን ገልጦ ነበር። በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በኩል በበጥቅምት ወር ይፋ የተደረገው የ10 ቢሊዮን ብር እቅድ እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም።  እቅዱ ተግባራዊ ይደረግበታል የተባለው የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅም ወደ ተወካዮች ምክር ቤት የተመራው በጥር መገባደጃ ነው። የሥራ ጉዳይ የሚያንገበግባቸው ወጣቶች የምዝገባውን ነገር ቢሰሙም እርግጠኛ መሆን የተሳናቸው ይመስላል። 

በዶይቼ ቬለ የፌስቡክ ማሕበራዊ ድረ-ገፅ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ያሰፈሩት አብዱረዛቅ ጠይብ «መንግስት ይህን ያደረገው እንዲህ አደረገ ተብሎ የህዝብ አመፅ የሚቆምለት ስለመሰለው ባይሆን ኖሮ ባለድርሻ አካላቱ የሚሰሩትን በደል ወርዶ ይቆጣጠር ነበር።» ብለዋል። ግርማ ሞገስ በበኩላቸው «ኢህአዴግ 10 ቢሊየን ብር ስራ አጥነትን ለመፍታት በጀት መድቢያለሁ ያለዉ በስራ አጥ ወጣቶች ስም የራሱን አባላት ለማጠናከር እና አዳዲስ ደጋፊዎችን ለማፍራት እንዲሁም በየቦታዉ የተቀሰቀሱበትን ህዝባዊ ተቃዉሞወች ለማፈን በማሰብ ነዉ፡፡» ሲሉ ኃሳባቸውን አስፍረዋል። የሥራ ፈላጊዎች ምዝገባውን «በጣም ደስ ይላል» ያሉት ገዛኸኝ ንጉሴ «ወደ ዞን ከተሞችም እንቅስቃሴዉ ቢቀጥል በየቤቱ የስራ ፍላጎት ከበቂ በላይ እያላቸዉ ግን ከተቀመጡበት የሚያስነሳቸዉ ሰዉ ያጡ ብዙዎች ናቸዉ/ነን፡፡» ሲሉ አክለዋል።