1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሥርዓተ አልበኝነት እና አድማ ስጋት ያጠላበት የአውሮጳ ዋንጫ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 4 2008

ትናንት በድምቀት በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ የተጀመረው የአውሮጳ ዋንጫ በሥርዓተ-አልበኝነት እና በአውሮፕላን አብራሪዎች የስራ ማቆም አድማ ስጋት ውስጥ እየተካሄደ ነው።

https://p.dw.com/p/1J4xu
Frankreich Marseille Fans werfen Bierflaschen
ምስል Getty Images/C. Court

ትናንት ምሽት አዘጋጇ ፈረንሳይ እና ሮማኒያ ያደረጉት የመክፈቻ ጨዋታ 2 ለ1 ተጠናቋል። ፈረንሳይ ኦሊቨር ዥሩ እና ዲሚትሪ ፓዬት ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች አሸናፊ ሆናለች። ቦግዳን ስታንቹ ለሮማኒያ የማስተዛዘኛዋን አንድ ጎል ከፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል። ዛሬ ስዊዘርላንድ ከአልባኒያ ተጋጥማ አንድ ለምንም አሸንፋለች። ዌልስ ከስሎቬኪያ፣ እንዲሁም ፣በደቡባዊ ፈረንሳይ የማርሴል ከተማ እንግሊዝ ከሩሲያ ይጫወታሉ።

የፈረንሳይ ፖሊሶች የአውሮጳ ዋንጫን ለመታደም ከተለያዩ አገሮች ከተመሙ ደጋፊዎች የሥርዓተ-አልበኝነት ችግር ገጥሟቸዋል። በትናንትናው ዕለት በማርሴል ከተማ የእንግሊዝ እና ሩሲያ ደጋፊዎች በቀሰቀሱት ኹከት ዘጠኝ ደጋፊዎች ለእስር ተዳርገዋል። ስድስቱ ክስ እንደሚመሰረትባቸው ፖሊስ አስታውቋል። የጸጥታ ኃይሎች የሰከሩትንና ራቁታቸውን የቡድን ጠብ የጀመሩ ደጋፊዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተጠቅሟል። በማርሴል ከተማ ቪየ ፖርት በተባለ አካባቢ በተቀሰቀሰው ኹከት ደጋፊዎቹ የቢራ ጠርሙሶች ሲወራወሩ የተስተዋሉ ሲሆን ፖሊሶች ምግብ ቤቶች እና ሱቆች እንዲዘጉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ከወራት በፊት ከተፈጸመው አሰቃቂ የሽብር ስጋት ያልተላቀቀችው ፈረንሳይ በማርሴል ብቻ 1,000 ገደማ የፖሊስ መኮንኖች አሰማርታለች። የጸጥታ ኃይሎች ወደ 50,000 ገደማ የሚሆኑ የእንግሊዝ እና ወደ 20,000 የሚጠጉ የሩሲያ ደጋፊዎች ተጨማሪ ኹከት እንዳይቀሰቅሱ ከፍተኛ ቁጥጥር በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የሁለቱ አገራት ደጋፊዎች የዛሬውን ጨዋታ ለመታደም ወደ ስታንድ ፌሎድሮሜ ስታዲየም በተቃራኒ አቅጣጫ እንዲጓዙ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

Frankreich Marseille Fans Randallieren
ምስል Getty Images/C. Court

በዛሬው እለት የፈረንሳይ አውሮፕላን አብራሪዎች ለአራት ቀናት የሚዘልቅ የስራ ማቆም አድማም ጀምረዋል። ኤር ፍራንስ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ በረራዎችን ጨምሮ በዛሬው ዕለት መከናወን ከነበረባቸው በረራዎች አንድ አምስተኛው መሰረዙን አስታውቋል።የፈረንሳይ መንግስት በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ ላይ ሊያደርግ ያቀደውን ማሻሻያ በዋናነት የሚቃወመው የአገሪቱ የሰራተኛ ማህበር ኃላፊ ፊሊፕ ማርቴኒዝ በአውሮጳ ዋንጫ ውድድር ሊወነጀሉ እንደማይገባ አስታውቀዋል።

ለአንድ ወር የሚዘልቀው እና በአስር ከተሞች ለሚካሄደው የአውሮጳ ዋንጫ ውድድር 90,000 ገደማ የግል የጸጥታ ጥበቃ ሃይሎች ተሰማርተዋል። ከእነዚህ መካከል 13,000 በፓሪስ ብቻ የተሰማሩ ናቸው። ውድድሩ ወደ ሁለት ሚሊዮን የውጭ አገር ጎብኚዎች እንደሚኖሩት ቢጠበቅም የሽብር ጥቃት እና የጎርፍ አደጋ ስጋትም አጥልቶበታል።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ