1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የራስታዎች አማራጭ ግብርና-ዘዴ

ሐሙስ፣ ኅዳር 10 1996
https://p.dw.com/p/E0g8
ከዘመናት በፊት ጀምረው ኢትዮጵያን መንፈሳዊ ሀገራቸው አድርገው የሚኖሩት፣ ራሳቸውን “ራስተፈሪየንስ” ወይም በአሕጽሮት “ራስታ” ብለው የሚጠሩት ብሔረሰቦች ይህችው የምርጫ ሀገራቸው ከምትገኝበት የረሃብ ፍርርቅ ለማላቀቅና አማራጩን የግብርና ዘዴ ለማሳየት ጥልቅ ፍላጎት እንዳላቸው ሰሞኑን በሰፊው ተዘግቦላቸዋል። ይህንኑ በማስመልከት ዛሬ የምናቀርበው ሐተታ ስለዚሁ ብሔረሰብእ የግብርና ልማት ዓላማ ዓለምአቀፍ ዜናምንጮች ያስተላለፉትን መረጃ ነው መሠረት የሚያደርገው።

እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የምር አትኩሮት ሳያገኙ የቆዩት ራስታዎች፣ አሁን መንግሥታዊ ባልሆነው ድርጅታቸው አማካይነት አማራጩን የግብርና ሥነቴክኒክ በማሳየትና በማስለመድ፣ የወጣቶች ዕድገት መርሐግብሮችንም በመዘርጋት የሕዝቡን አመለካከት ለመለወጥ ነው የተነሳሱት። “እኛ ራስታዎች ቀኑን ሙሉ ረጌ ሙዚቃ ብቻ ከማቀንቀንና ማሪሁዋና ከማጤስ በስተቀር ሌላ ነገር የማንፈይድ መስለን የምንታይበትን የተሳሳተ አመለካከት ለማስወገድ ነው የምንፈልገው፣ እኛ ከምር የተነሳሳን ትጉሃን የልማት ሠራተኞች ነን” ይላል የራስታዎቹ ዓለምአቀፍ ፈደራሲዮን ሰብሳቢ ራስ ካቢንዳ የሚያጎሉት ማስገንዘቢያ።

እንደሚታወቀው፣ ራስተፈሪየንስ ወይም ራስታዎቹ መንፈሳዊ የኑሮ መካን ያደረጓት፣ ከአዲስ አበባ ደቡብ በ፪፻፳ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን ከተማ ሻሸመኔን ነው። ዛሬ እዚያው እንደሰፈሩ የሚገኙት ቤተሰቦች አንድ-መቶ ያህል ናቸው። ራስታዎቹ በሐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ-መንግሥት በ፲፱፻፵ ነበር ወደ አፍሪቃ ለመመለስ በነበራቸው ፍላጎት መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስፈር የበቁት።

የእነርሱ ዓለምአቀፍ ፈደራሲዮን ባሁኑ ጊዜ ሻሸመኔ ውስጥ ሁለት ትምህርትቤቶችን የሚያካሂዱ ሲሆን፣ ክእነዚሁ አንዱ ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ ሌላው ደግሞ በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ለሚማሩት ወጣቶች የተመደበ እንደሆን ታውቋል። አሁን ድርጅቱ እንደገለፀው ከሆነ፣ በ፭፻ ሄክታር መሬት ላይ አንድ አርአያ/ማለት ማሳያና ማላመጃ የግብርና ማዕከል ለመክፈት ዕቅድ ቀርቧል። ከዚህም በላይ፣ የፈደራሲዮኑ ቅርንጫፍ በሆነው በኃይለሥላሴ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሥር ፪፻ ተማሪዎችን የሚያገለግል አንድ የኮምፒውተር ማዕከል ለመክፈት ዕቅድ እንዳለም ነው የተገለፀው። ካቢንዳ እንደሚሉት፣ መንግሥት ለአርአያው የግብርና ማዕከል ፭፻ ሄክታር የሚደርስ መሬት እንዲመድብ ፈደራሲዮኑ እየጠየ መሆኑን አሁን ይፋ አድርጎታል። በዚያው አርአያ የግብርና ጣቢያ አማካይነት የተሻለና አማራጭ ግብርና እንዳለ ለኢትዮጵያውያኑ ገበሬዎች ለማሳየት፣ በዚያው ማሳያ የእርሻ ማዕከላት ላይ ከውጣቶቹ ጋር አብሮ ለመሥራት ነው የተፈለገው። ለዚሁ አማራጭ የግብርና ታታሪነት አስፈላጊው ጥሬ እቃ በአካባቢው የሚያመች እንደመሆኑ መጠን፣ የአርአያ እርሻውን ማዕከል የምግብ ማዕከል ለማድረግ ነው ያው ድርጅቱ የተነሳሳው። ለዚሁ የልማት ፕሮዤ የሻሸመኔው ማዘጋጃ-ቤት ፈቃድ የሰጠ እንደመሆኑ መጠን፣ አሁን የፈደራዊው መንግሥት እሺታ ነው የሚጠበቀው ይላል የድርጅቱ መግለጫ። የድርጅቱ ተጠሪ ካቢንዳ እንደሚሉት ከሆነ፣ ለመረጃውና ለመገናኛው ሥነቴክ’ኒክ ፕሮዤም ነው ቀዳሚው ትኩረት የሚሰጠው። ለዚሁ የመረጃ ሥነቴክንክ ማስፋፊያ ፕሮዤ ፪፻ ኮምፒውተር-መሣሪያዎች በልገሳ ሊቀርቡ እንደሚችሉ ስለሚጠበቅ፣ መንገዱን ትምህርት-ሚኒስቴር እንዲያቃናው አሁን የሚጠየቅ መሆኑም ነው የተገለፀው።

ብሔረሰቡ እንደሚለው፣ ራስተፈሪያዊነት ወይም ራስታነት እንዲያው የሃይማኖት ጉዳይ ብቻ አይደለም፥ የሕይወት ዘይቤም ነው። ራስታዎች በድህነት፣ በጭቆናና በኑሮ ሚዛን ዝንፈት አንፃር በግልጽ የመናገርና የመታገል ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል፤ የተገመደ ፀጉራቸውም ፍትሕን ለሚሻው አመጽ ምልክት ሆኖ ነው የሚታየው። በማሪሁዋናው እጽ የሚጠቀሙት፣ ለመንፈሳዊ ስሜትና ለመድኃኒትነት ዓላማ መሆኑን ያስገነዝባሉ። በሥጋ ፈንታ እፀዋትን ብቻ ቀለብ የሚያደርጉት እነዚሁ ራስታ-ብሔረሰቦች ያለ ጨው፣ ያለቅመም የተበሰለ ተፈጥሮአዊ እህል ነው የሚመገቡት፤ ከዚህም በላይ አልኮሆል፣ ቡና፣ ወተትና ለስላሳ መጠጥ እነርሱ ዘንድ ነውር ነው።

ግን፣ የራስታዎቹ ፈደራሲዮን አመራር እንደሚለው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡ እስካሁን ድረስ የአኗናራቸውን መስመር ስላልተረዳላቸው ማፌዣ እንዳደረጋቸው የተሰማቸው ብዙ ራስታ-ወጣቶች የተገመደ ፀጉራቸውን እስከመቁረጥ ነበር የደረሱት። አሁን ግን፣ ኢትዮጵያውያን ከራስታዎች ይማሩ ዘንድ የጊዜው ጥሪ እንደሆን የሚሰማቸው የፈደራሲዮኑ ሰብሳቢ ራስ ካቢንዳ እንደሚያስገነዝቡት፣ ሀገሪቱ በያመቱ በረሃብ መፋጠጥ የለባትም፣ ለዚህ የረሃብ አደጋ ድግግም ምክንያት፣ መንስኤ መኖር አለበት፣ ይህን’ኑ መንስኤ ማጤንና ማስወገድ ግዴታ ነው።

የዚሁ የራስታ ብሔረሰብእ ፈደራሲዮን በአማራጭ ግብርና ፕሮዤዎቹ ኣማካይነት ለገበሬዎች ምክር በመስጠት፣ በአንድ ቅንጣት ሰብል ላይ የሚመረኮዘው አለቅጥ ያጋደለው የእርሻ ልምድ እየተተወ፣ በዚህ ፈንታ የአዝርእት ልማት ፍርርቅ እንዲኖር፥ የእርሻው መሬት ለምሳሌ ለልይዩ የአትክልት ዓይነቶች፣ ለጎመናጎመን፣ ለፍራፍሬ እፀዋት እና ለአበባ እህሎችም ምርት መዋል እንዳለበት ያስገነዝባል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው፣ ድርጅቱ እንደሚለው፣ ሕጻናት ከኣታክልትና ከፍራፍሬ በሚያገኙት ቪታሚንና ማእድን ቁስ አማካይነት የለማና የዳበረ አእምሮ ሊኖራቸው የሚበቁት። ለአበባ እህሎችም ግብርና ተመሳሳዩ ከፍተኛ ትርጓሜ ነው የሚሰጠው።

ድርጅቱ የሚነቅፈው ሌላው የግብርና ፀባይ፣ የማዳበሪያ ቅመማትንና የፀረአረም ልክ-አልባ ግብዓትን የሚመለከት ነው። በድርጅቱ አመራር አመለካከት መሠረት፣ የግብርናው ሥራ የሚተከልበት የንጥረነገሩ ግብዓት አንደኛ የውጭን ምንዛሪ የሚያሟጥጥ፣ ሁለተኛ አፈርን የሚበክል ነው የሚሆነው። እንዲያውም፥ ይኸው የንጥረነገር ግብዓት የአፈርን ጥራት እያመናመነ፣ ከ፲ እስከ ፲፭ ዓመታት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ የአፈሩን ምርታማነት ሙሉ በሙሉ የሚደመሰስና በዶ የሚያደርግ ነው የሚሆነው። በአእላፋት ሚታሰብ ግዙፍ የከብት መንጋ የመላት ኢትዮጵያ ለአፈሩ ማዳበሪያ በጎጅው ንጥረነገር ፈንታ በፍጉ አቅርቦት መጠቀም በተገባትም ነበር ይላል የድርጅቱ ማስገንዘቢያ። በዘመናዊው ተፈጥሮአዊ ግብርና አማካይነት የረሃብ ድግግም እንዲወገድ ድህነት እንዲቀረፍ እና በማኅበራዊው ኑሮ ውስጥ እኩልነት እንዲጠናከር ዓይነተኛ ዓላማው መሆኑን ያስረዳል ለአማራጩ ግብርና ፕሮዤ የተነሳሳው የራስታ ብሔረሰብ ፈደራሲዮን መግለጫ።