1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሬሚታንስ ሚና በኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 19 2003

በበለጸጉ ሃገራት የሚኖሩ ከታዳጊው ዓለም በተለያየ ምክንያት የፈለሱ ሠራተኞች ለወገኖቻቸው የሚልኩት ገንዘብ ሬሚታንስ ከዓመት ወደ ዓመት ለብዙዎች ይበልጥ የሕልውና ዋስትና እየሆነ ነው።

https://p.dw.com/p/RKcz

ይሄው ገንዘብ ዛሬ በበለጸጉ መንግሥታት ከሚቀርበው ይፋ ዓለምአቀፍ የልማት ዕርዳታ ሲበልጥ ለብዙዎቹ አዳጊ አገሮች ሁለተኛው ታላቅ የፊናንስ ምንጭም ነው። በኢትዮጵያስ ሁኔታው ምን ይመስላል?

ፈላሽ ሠራተኞች ወደ አዳጊው ዓለም የሚልኩት ገንዘብ ለኤኮኖሚ ዕድገትና ለማሕበራዊ ኑሮ መሻሻል የሚያደርገው አስተዋጽኦም እየጨመረ መሄዱ የተሰወረ ነገር አይደለም። በዓለም ባንክ ግምት በ 2009 ዓ.ም. በጠቅላላው ወደ ታዳጊ ሃገራት የተሻገረው የሬሚታንስ ገንዘብ 316 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋ ነበር። በእሢያ ክፍለ-ዓለም ቀደምቱ ተጠቃሚዎች ሕንድ፣ ፊሊፒንስና ቻይና ሲሆኑ በዚህ መልክ እያንዳንዳቸው በዓመት የሚያገኙት ገን’ዘብ ከሃያ ቢሊዮን ዶላር ይበልጣል።

ፊሊፒንስን ብቻ እንኳ እንደ ምሳሌ ብንወስድ ይሄው ገነብ ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቷ ዘጠኝ በመቶው ገደማ መሆኑ ነው። በላቲን አሜሪካና በካራይብም ሬሚታንስ በአካባቢው ኤኮኖሚ ላይ ያለው ሚና በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ከሶሥት ዓመታት በፊት ለምሳሌ ከ 66 ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ ገንዘብ አካባቢው ሲገባ ከዚሁ አብዛኛው፤ 75 በመቶውም ከዩ.ኤስ.አሜሪካ ነበር። በድምሩ ዓለምአቀፉ ቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይና ይፋው የልማት ዕርዳታ ተደምረው እንኳ አይደርሱበትም።

በአፍሪቃ ደግሞ ባለፈው ዓመት ዋነኛዋ ተቀባይ በአሥር ቢሊዮን ዶላር ናይጄሪያ ነበረች። ከተል ብለውም ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሤኔጋልና ደቡብ አፍሪቃም ከአንድ እስከ ሶሥት ቢሊዮን ዶላር አግኝተዋል። ኢትዮጵያም ከቀደምቱ አሥር የአፍሪቃ አገሮች አንዻ መሆኗ ነው። ባለፈው 2010 ዓ.ም. ወደ አገሪቱ የገባው የሬሚተንስ ገንዘብ 387 ሚሊዮን ዶላር ይጠጋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በእንግሊዝና ቋንቋ የሚታተመውን የአዲስ-ፎርቹን ጋዜጣን አዘጋጅ አቶ ታምታር ገ/ጊዮርጊስን አነጋግረናል፤ አድምጡ!


አቶ ታምራት! በበለጸገው ዓለም ውስጥ የሚኖሩና የሚሠሩ የታዳጊው ሃገራት ተወላጆች በተለይም ዘመድ ለመደገፍ ወደመነጩባቸው አካባቢዎች ብዙ ገንዘብ ነው የሚልኩት። ይሄው ገንዘብ ደግሞ በተለያዩት ሬሚተንሱ በሚገባባቸው አገሮች በልማት አስተዋጽኦውና ማሕበራዊ ኑሮን በማሻሻል ረገድም ያለው ሚና እየጠነከረ ነው የመጣውው። ለመሆኑ በኢትዮጵያ ይሄ በምን ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው?

ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ገንዘብ አብዛኛው ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓና ከመካከለኛው ምሥራቅ ነው የሚመነጨው። እንዴት ነው ገንዘቡ የሚውለው የዕለት ከዕለት ኑሮን ለመቋቋም ለፍጆታ ብቻ ነው ወይስ ቢቀር በመለስተኛ ንግድ ደረጃ እንኳ በመዋዕለ-ነዋይ መልክ ሥራ ላይ ሲውል ይታያል ወይ?

የዓለም ባንክ ባቀረበው ግምት መሠረት ባለፈው 2010 ዓ.ም. ከባሕር ማዶ ኢትዮጵያ የገባው ሬሚታንስ 387 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ይደርሳል። ለመሆኑ ገንዘቡ በሚላክላቸው ሰዎች ዘንድ የኑሮ መሻሻልን ለመታዘብ ይቻላል ወይ?

መንግሥትም የውጭ ምንዛሪ ሰሚያስፈልገው ከባሕር ማዶ የሚላከው ገንዘብ እየጨመረ መሄዱን እንደሚመኝ አንድና ሁለት የለውም። እርግጥ ወደ ኢትዮጵያ የሚሻገረው ሬሚታንስ የአገሪቱን ኤኮኖሚ በሰፊው ጥገኛ አድርጓል ለማለት አይቻልም። ቢሆንም በደፈናው የሚናቅ አይሆንም። እንበል ገንዘቡ አገር ባይገባ ወይም ቢቀር በኤኮኖሚው ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ ነው የሚኖረው?

አቶ ታምራት! በሌላ በኩል በተለይም ገንዘቡ ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርታቸው ሰፊውን ድርሻ ይዞ የሚገኝባቸውን አገሮች እንደ ምሳሌ በመውሰድ ገንዘቡ መላኩ ጥገኝነትን ያስተምራል፤ አገርን በማልማት ራስ የመቻሉን ፍላጎት የሚያዳክም ነው የሚሉ ትችቶችም መሰንዘራቸው አልቀረም። ይህ ምን ያህል ትክክለኛ ነው?

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ