1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሮሒንግያዎች ሥቃይ

ሐሙስ፣ ጳጉሜን 2 2009

ዓለም አቀፉ ድርጅት ያነጋገራቸዉ ስደተኞች እንደሚሉት የምያንማር ወታደሮች የሮሒንግያ ሙስሊሞችን በጥይት ይገድላሉ፤ ይደበድባሉ፤ መኖሪያ ቤታቸዉን ያቃጥላሉም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ በሮሒንግያ ሙስሊሞች ላይ የሚፈፀመዉ ግፍ የአካባቢዉን ሠላም እና ፀጥታ ሊያዉከዉ እንደሚችል ባለፈዉ ማክሰኞ አስጠንቅቀዉ ነበር።

https://p.dw.com/p/2jXks
Rohingya in Myanmar und Bangladesch
ምስል picture-alliance/dpa/M.Alam

የምያንማር መንግስት ጦር የሚፈፅምባቸዉን ግድያ፤ ግፍና በደል በመፍራት በ10 ቀናት ዉስጥ ወደ ባንግላዴሽ የተሰደዱት የሮሒንግያ ሙስሊሞች ቁጥር ከ164ሺ መብለጡን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ። ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) ዛሬ እንዳስታወቀዉ ካለፈዉ ነሐሴ 19 ጀምሮ ባንግላዴሽ የሚገቡት ስደተኞች ቁጥር አለቅጥ በመብዛቱ ለአስተናጋጅዋ ባንግላዴሽ ከባድ ፈተና ሆኗል። UNHCR እንደሚለዉ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሌሎች ስደተኞች የምያንማርን ድንበር አልፈዉ ባንግላዴሽ ለመግባት እየሞከሩ ነዉ። ዓለም አቀፉ ድርጅት ያነጋገራቸዉ ስደተኞች እንደሚሉት የምያንማር ወታደሮች የሮሒንግያ ሙስሊሞችን በጥይት እየመቱ ይገድላሉ፤ ሌሎቹን ይደበድባሉ፤ መኖሪያ ቤታቸዉን ያቃጥላሉም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ በሮሒንግያ ሙስሊሞች ላይ የሚፈፀመዉ ግፍ የአካባቢዉን ሠላም እና ፀጥታ ሊያዉከዉ እንደሚችል ባለፈዉ ማክሰኞ አስጠንቅቀዉ ነበር።
«ሊሸከሙት የማይችሉትን ግፍ፤ ሥቃይ እና መከራን የሸሹ 125ሺሕ ሰዎች (እስካሁን) ባንግላዴሽ ዉስጥ ከለላ አግኝተዋል። በርካታ ሰዎች ከሚደርስባቸዉ ግፍ ለማምለጥ ሲሞክሩ ሕይወታቸዉን አጥተዋል። የሮሒንግያዎች ብሶት፤ የሚደርስባቸዉ መከራ ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል። አካባቢዉን ለማወክ መሠረታዊ ምክንያት መሆኑ ሊካድ አይገባም።»
የምያንማር መንግሥት አማፂያንን እዋጋለሁ በሚል ሽፋን በሮሒንግያ ሙስሊሞች ላይ የሚፈፅመዉን ግፍ እንዲያቆም የተለያዩ መንግሥታት ቢጠይቁም እስካሁን ድረስ ተቀባይነት አላገኙም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ ሌሎች ማሕበራትም ሆኑ መንግሥታትም በምያንማር መንግስት ላይ እርምጃ ለመዉሰድ አልቃጡም።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ