1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰላም ኖቤል ለአዉሮጳ ኅብረት

ዓርብ፣ ጥቅምት 2 2005

የኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ በዛሬዉ ዕለት ለአዉሮጳ ኅብረት የሰላም ኖቤል ሽልማቱን ሰጥቷል። የሽላማት ኮሚቴዉ ኅብረቱ በአዉሮጳ በጠላትነት ይተያዩ በነበሩ ሀገሮች መካከል ለፈጠረዉ መልካም ግንኙነትና ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲህ ሰላም እንዲሰፍን ለተጫወተዉ ሚና ሽልማቱን መስጠቱን አስታዉቋል።

https://p.dw.com/p/16PII
ምስል picture-alliance/dpa

ሽልማቱ የኅብረቱ መሪዎች ለሚያከናዉኑት ተግባር እንደማበረታቻ ሲቀበሉት ተቺዎች በአንፃሩ ቀልድ ነዉ ሲሉ ተሳልቀዋል። ጀርመንን አንድነት በማስከበር ለአዉሮጳ ኅብረት አባልነት ለማብቃት ትልቅ ሚና መጫወታቸዉ የሚነገርላቸዉ የ82 ዓመቱ የጀርመኑ የቀድሞ መራሄ መንግስት ሄልሙት ኮል ሽልማቱን አድንቀዋል። ከግሪክ፤ ከብሪታንያና ከፈረንሳይ በአንፃሩ የዩሮ ተቺዎች ፌዝ ሲሉ አጣጥለዉታል።

የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ኾዜ ማኑዌል ባሮዞ ህብረቱ ለኖቤል ሰላም ሽልማት በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
« የኖቤል ሰላም ኮሚቴ የዘንድሮውን የኖቤል ሰላም ሽልማት ለአውሮጳ ህብረት ለመስጠት መወሰኑ ትልቅ ክብር ነው። ይህ የኖቤል ሰላም ሽልማት ለአምስት ሚልዮኑ የህብረቱ አባል ሀገራት ዜጎች፡ ለአባል ሀገራቱ በጠቅላላ፡ እና ለህብረቱ ተቋማትም ጭምር ክብር ነው። ለዜጎቹ እና ለመላ ዓለም ጥቅም ለማስገኘት እየሰራ ለሚገኘው ልዩ ፕሮዤም ዕውቅና የሚሰጥ ነው። »

የአውሮጳ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ጀርመናዊው ማርቲን ሹልዝ ሽልማቱ ለጠቅላላ የህብረቱ አባል ሀገራት ዜጎች መሆኑን በማመልከት በኮሚቴው ውሳኔ እጅግ እንደተደሰቱ ገልጸዋል። የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ሽልማቱ ህብረቱ ለነጻነት መስራቱን ማቋረጥ እንደሌለበት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
« በዚህም የተነሳ ለዚህ ሰላም፡ ለዴሞክራሲና ለነፃነት ሁሌ እንዳዲስ ጠንክረን መስራታችንን፡ መጣራችንንና መልፋታችንን መቀጠል እንዳለብን መዘንጋት የለብንም። »
የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ኦሎንድም ሽልማቱ ለአውሮጳ ህብረት መሰጠቱ የህብረቱ መሪዎች ሰላም የሰፈነባት የተባበረች፡ ትክክለኛና ጠንካራ አውሮጳ መስራታቸውን እንዲቀጥሉ የሚያበረታታ ትልቅ ክብር ነው ብለዋል። ሽልማቱ ለአውሮጳ ህብረት መሰጠቱን አንድ የኖርዌይ ድርጅት ትርጉም አልባ በሚል በመቃወም ሀገሩ የህብረቱ አባል ለመሆን አዝማሚያ አሳየች ባለው ጉዳይ ላይ አዲስ ክርክር ቀስቅሶዋል።

EU Norwegen Friedensnobelpreis 2012 an EU Jose Manuel Barroso in Brüssel
ሆዜ ማኑዌል ባሮሶምስል dapd

ገበያዉ ንጉሤ

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ