1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የክስ ሂደት

ሰኞ፣ ሰኔ 29 2007

የኢትዮጵያ መንግስት ሊቢያ ዉስጥ በግፍ የተገደሉ ኢትዮጵያዉያንን ለመዘከር የጠራዉን የአደባባይ ሠልፍ በማወክ ከተከሰሱ የሰማዊ ፓርቲ አባላት መካካል ሶስቱ ዛሬ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጣቸዉ።

https://p.dw.com/p/1Fte4
Äthiopien vor der Wahl Blaue Partei Anhänger in Addis Abeba
ምስል Reuters/Tiksa Negeri

[No title]

ራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስካማዊ መንግሥት (ISIS) ብሎ የሚጠራዉ ቡድን ኢትዮጵያዉን ስደተኞችን መግደሉን በመቃወም የተጠራዉን ሠልፍ አዉካችኋል ተብለዉ የታሰሩት አስራ-አምስት ነበሩ። ከነዚሕ መካከል የተወሰኑት ሲፈረድባቸዉ፤ ሌሎቹ እየተሟገቱ ነዉ።

በሊቢያ ራሱን አይ.ኤስ. በማለት የሚጠራው ታጣቂ ቡድን የወሰደውን እርምጃ ለማውገዝ የኢትዮጵያ መንግሥት ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ በጠራው ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ረብሻ በመፍጠር፣ በመሳደብና ድንጋይ በመወርወር የተከሰሱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው የአንድ ወር ቀጠሮ ተሰጣቸው። በተመሳሳይ ክስ ማረሚያ ቤት የከረሙትና ባለፈው ሳምንት በዋስትና የተፈቱት ወይዘሪት ወይንሸት ሞላ ማቲያስ መኩሪያ፤ብሌን መስፍን እና ተዋቸው ዳምጤ የተባሉት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በተመሳሳይ የህግ አንቀጽ መከሰሳቸውን ተናግረዋል።

የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ስለሺ ፈይሳ ሚያዝያ 14 ቀን ከተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ጋር በተያያዘ ከታሰሩ 15 የፓርቲው አባላት መካከል ከስድስት ወር እስከ ሶስት አመት እስር የተበነባቸው እንደሚገኙ ተናግረዋል።

«በአባላት ደረጃ የታሰሩት ከ 15 አያንሱም። የተወሰኑት ተፈተዋል። የሶስት አመት ተኩል ፍርድ የተፈረደበትና ሸዋሮቢት የሄደ ወጣት ናትናኤል አለምዘውድ የሚባል ልጅ አለ። የስምንት ወር እስራት የተፈረደባት የሁለት ልጆች እናት የሆነች ወይዘሮ ንግስት ወንድ ይፍራው የምትባል የፓርቲያችን ንቁ አባልም አለች።»

Äthiopien Addis Abeba Anti ISIS Protest
ምስል Getty Images/AFP/Abubeker

በ2007 ምርጫ በአዲስ አበባ ከተማ ወረዳ 7 ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው በእጩነት ተመዝግበው በእጣ ከውድድሩ ሳይገቡ የቀሩት ወይዘሪት ወይንሸት ሞላ የእስልምና እምነት ተከታዮች በአንዋር መስጊድ አቅራቢያ ባካሄዱት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በተፈጠረ ግጭት ተሳትፎ አድርገዋል በሚል ለእስር ተዳርገው ነበር። ወይዘሪት ወይንሸት ሞላ ከአሁኑ ክስ በአምስት ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ቢለቀቁም ሐምሌ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ተመልሰው ከችሎት ይቆማሉ።

Trauer um IS-Opfer in Äthiopien
ምስል DW/E. Bekele

ወይዘሪት ወይንሸት ሞላ፣ኤርሚያስ ፀጋዬ፣ዳንኤል ተስፋዬና ቤተልሔም አካለወርቅ በየፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምብድ ችሎት ሰኔ 15 ቀን 2007 የተበየነባቸውን የሁለት ወር ቅጣት ካጠናቀቁ በኋላ ከማረሚያ ቤት ሲወጡ በፀጥታ ኃይሎች ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን አስቆጥቶ ነበር። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ክስተቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት የህግ የበላይነትን እየሸረሸረ ነው ሲል መተቸቱ አይዘነጋም።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ