1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የሰሜኑ ጦርነት ኤኮኖሚያዊ ዳፋ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 26 2013

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት "የኤኮኖሚ አሻጥር በመፍጠር" የከሰሷቸው የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እየወሰዱ ነው። የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር 50 ሺሕ 450 የንግድ ድርጅቶች መታሸጋቸውን አስታውቋል። መስሪያ ቤቱ ባወጣው መረጃ መሠረት 1 ሺሕ 520 የንግድ ተቋማት ፈቃዳቸው የተሰረዘ ሲሆን 257 ደግሞ ታግደዋል

https://p.dw.com/p/3zn1b
Video Still TV Magazin The 77 Percent
ምስል DW

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የሰሜኑ ጦርነት ኤኮኖሚያዊ ዳፋ

የኢትዮጵያ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር "የኤኮኖሚ አሻጥር በመፍጠር" የተከሰሱ 50 ሺሕ 450 የንግድ ድርጅቶች መታሸጋቸውን አስታውቋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባወጣው መረጃ መሠረት 1 ሺሕ 520 የንግድ ተቋማት ፈቃዳቸው የተሰረዘ ሲሆን 257 ደግሞ ታግደዋል። 80 ሺሕ 641 የንግድ ድርጅቶች ማስጠንቀቂያ በጽሁፍ ተሰጥቷቸዋል።

ይኸ የመንግሥት እርምጃ ተግባራዊ ከሆነባቸው መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አንዱ ነው። የአስተዳደሩ የንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ ባለፈው ሳምንት መገባደጃ በሰጡት መግለጫ "የኤኮኖሚ አሻጥር ሲሰሩ ነበሩ"  የተባሉ አንድ ሺሕ 886 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ እንደተወሰደ ተናግረዋል።

"657 ንግድ ድርጅቶች ላይ ፈቃዳቸውን የመሠረዝ ሥራ ተሰርቷል" ያሉት ኃላፊው "የንግድ ሕግ እና አዋጅን ጠብቀው የማይሰሩ ከዚህም ባሻገር ለሕብረተሰባችን ጤና ጠንቅ በሆነ መንገድ የንግድ እንቅስቃሴያቸውን ሲያከናውኑ በነበሩ 64 የንግድ ድርጅቶች ላይ ክስ የመመሥረት ሥራ ተሰርቷል" ሲሉ የተወሰደውን እርምጃ አብራርተዋል።

ባለሥልጣናቱ ተከስቷል ያሉትን የኤኮኖሚ አሻጥር ለመቆጣጠር የወሰዷቸው እርምጃዎች ግን እነዚህ ብቻ አይደሉም። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ለ90 ቀናት የቤት ኪራይ ጭማሪ ማድረግ የሚከለክል ደንብ አጽድቋል። ከነሐሴ 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ገቢራዊ በሆነው ደንብ መሠረት "የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መጨመርም ሆነ ተከራይን ከቤት ማስወጣት ለ90 ቀናት የተከለከለ" መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ይፋ አድርጓል። የመዲናዋ አስተዳደር እንዳለው "ለተጨማሪ ቀናት ክልከላው ሊራዘም ይችላል።"

በዋና ከተማዋ ካለፈው ሐሴ 7 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የመሬት አስተዳደር ተቋማት፣ የመሠረተ ልማት ቅንጅት እና ግንባታ ፈቃድ ባለስልጣን እንዲሁም አስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች የመሬት እና የመሬት ነክ አገልግሎቶች ላልተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ እንዳይሰጡ ትዕዛዝ ተላልፏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ ሁሉም ባንኮች መሬት፣ ቤት እና ሕንፃን ጨምሮ መያዣ በመጠቀም የሚሰጥ ብድር እንዲያቆሙ ውሳኔ አሳልፎ ነበር።

በኢትዮጵያ የኤኮኖሚ አሻጥር እየተፈጸመ ነው ወይም ሊፈጸም ይችላል የሚለው ክስ በተደጋጋሚ መደመጥ የጀመረው ህወሓት እና የፌድራል መንግሥቱ ውጊያ ከገጠሙ በኋላ ነው። በአዲስ አበባ ከነጋዴዎች ጋር በተካሔደ ውይይት ላይ የዋና ከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ "ኤኮኖሚ ሻጥር ላይ የሚሰራው ሥራ ገንዘብ ለማግኘት ብቻ አይደለም። በአንድ በኩል አገርን ለማፈራረስ የታለመውን ዓላማ በገንዘብ ለመደገፍ በደንብ ሒሳብ ሰርተው የተነሱበት እንደሆነ ማየት ችለናል" ብለው ነበር።

Äthiopien | Dire Diwa | Geschlossene Läden
ከአዲስ አበባ ባሻገር በቤኒሻንጉል ጉምዝ እና የደቡብ ክልሎችን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የዋጋ ጭማሪ አደረጉ የተባሉ ላይ እርምጃ ተወስዷል። ምስል Mesay Teklu/DW

ጫና የበረታበት ኤኮኖሚ

በትግራይ ውጊያ ከመቀስቀሱ በፊት የኮሮና ወረርሽኝ በኤኮኖሚው ላይ ጫና ማሳደሩን የሚያስታውሱት በጀርመኑ የፍራይቡርግ ዩኒቨርሲቲ አርኖልድቤርግሽትራሰር ማዕከል የፖለቲካል ኤኮኖሚ ተመራማሪው ዶክተር ቤኔዲክት ካምስኪ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ  የበረታበትን የመጀመሪያ አንድ አመት ኢትዮጵያ ደህና ማለፏን ይናገራሉ።  "ከ2019 በመጠኑ ዝቅ ቢልም በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የውጭ መዋዕለ ንዋይ የተቀበለች አገር ነበረች" የሚሉት ተመራማሪው የአፍሪካ ነጻ አኅጉራዊ የንግድ ቀጠና ጅማሮ እና "ኢትዮጵያን ለውጭ ባለወረቶች እና የአገር ውስጥ ባለሐብቶች ተስፋ ሰጪ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ እና በማምረቻው ዘርፍ የሚፈጠረውን የሥራ ዕድል ለመጨመር የታቀደው የአገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ" አዎንታዊ ዕድሎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የውጊያ መቀስቀስ ከሌሎች ምክንያቶች ጋር ተደማምሮ በኤኮኖሚው ላይ ጫና ማሳደሩን የተናገሩት ዶክተር ቤኔዲክት "ትልቁ ችግር ባለፉት አመታት እንደሆነው ሁሉ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ነው። በአሁኑ ወቅት ሁሉም ነገር እየተወደደ ነው ማለት ይቻላል። በዋና ከተማዋ የምግብ እና የመጓጓዣ ዋጋ ጨምሯል። ቀደም ብሎ የነዳጅ ዋጋ ጨምሮ ነበር። ኪራይ እየጨመረ ነው። ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ ደሞዝ እያደገ አይደለም። ኢትዮጵያ ከውጪ በምታስገባው ሸቀጥ ላይ በዋናነት ጥገኛ በመሆኗ በተለይ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍ ያለ ተጽዕኖ አሳድሯል። በዚያ ላይ ግጭቱን ስንመለከት ለሕግ ማስከበር ተልዕኮው፣ ለጦሩ፣ ጠቅላይ ምኒስትሩ እንዳሉት በትግራይ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት እና በመላ አገሪቱ ሰዎችን ለመመመገብ መንግሥት ያወጣው ወጪ ተደማምሮ የውጭ ምዛሪ አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል" ሲሉ ያብራራሉ።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በይፋ የተቀሰቀሰው ውጊያ ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ ከለት ወደ ዕለት እየጨመረ ሔዷል። በትግራይ ኤሌክትሪክ እና ቴሌኮምን የመሳሰሉ መሠረዊ አገልግሎቶች እንደተቋረጡ ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ ባለፈው ሳምንት ለጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት እንደተናገሩት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ሌሎች አንድ ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ነፍሳቸውን ለማቆየት ምግብ፣ ውኃ እና መጠለያ የመሳሰሉ ሰብዓዊ ዕርዳታ ጠባቂ ሆነዋል። ጉቴሬሽ የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት የትግራይ ቀውስ ላይ በመከረበት ስብሰባ በሰጡት ማብራሪያ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ "ግጭቱ በኤኮኖሚ ላይ ከባድ ጫና አሳድሮ የጦርነትን ከንቱነት በድጋሚ እያመለከተ ነው። ውጊያው እስካሁን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ከአገሪቱ ካዝና አራቋቷል። ዕዳ እየጨመረ ነው። ብድር የማግኘት ዕድል እየደረቀ ነው። የዋጋ ግሽበት ጨምሯል። መሠረታዊ የምግብ ግብዓቶች አቅርቦት እየተመናመነ ሔዷል" ሲሉ ተደምጠዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰው ግጭቱ ለኢትዮጵያ አንድነት እና ለቀጠናው መረጋጋት ሥጋት መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጸው የተኩስ አቁም እንዲደረስ ቢወተውቱም እስካሁን ይኸ ነው የሚባል መፍትሔ አልተገኘም።

የውጊያ አውድማው ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ከተስፋፋ በኋላ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸው ቀጥሏል። ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማትን ጨምሮ መሠረታዊ የአገልግሎት ተቋማት ለዝርፊያ እና ውድመት ተጋልጠዋል።

የፖለቲካል ኤኮኖሚ ተመራማሪው ቤኔዲክት ካምስኪ ግጭቱ በጊዜው ኹነኛ መፍትሔ ካልተገኘለት ሌሎች የኤኮኖሚ ዕቅዶች ላይ ጭምር ዳፋ እንደሚኖረው ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። "የመጀመሪያው የቴሌኮም ፈቃድ ጨረታ በስኬት ተጠናቋል። ሁለተኛው ፈቃድ ለጨረታ ሊቀርብ በሒደት ላይ ነው። በተመሳሳይ ጊዜ ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ነች ወይ የሚለውን ጉዳይ እንደገና እያጤኑት እንደሆነ ታዝበናል። የተረጋጋች አይደለችም። ግጭቱ በአገሪቱ አብዛኛው ክፍል አለመረጋጋት ሊፈጥር ይችላል። ይኸ ደግሞ የሚመጡ ኢንቨስተሮች በሥራ ላይ ሊገጥማቸው የሚችለውን ሥጋት ይጨምራል። በአሁኑ ወቅት ሁለት አበይት ጉዳዮች እየተከናወኑ ናቸው። አንደኛው የቴሌኮምዩንኬሽን ዘርፉን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ማድረግ ሲሆን የኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪን ወደ ግሉ ዘርፍ ማዛወር ወይም እንደገና ማዋቀር ናቸው። የስኳር ኢንዱስትሪው በኦሮሚያ እና በትግራይ የመንግሥት ይዞታ የሆኑ ፋብሪካዎች አሉት። ይኸ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት ነበር። እነዚህ አካባቢዎች ሁሉ ብዙ ባለወረቶች መረጋጋት እስኪኖር ኢንቨስትመንታቸውን እንደገና ሊያጤኑ የሚችሉባቸው ናቸው። እነዚህ ግዙፍ ኢንቨስትመንቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በትክክለኛው ጊዜ ካልመጡ ይኸ የማሻሻያ ሐሳቡ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል" ሲሉ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ