1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰሜን ንፍቀ ክበብና ክረምቱ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 27 2002

በሰሜን ንፍቀ ክበብ የክረምቱ ወራት እጅግ የጠነከረ ብርድ ማምጣቱ በመንገዶችና በመጓጓዣ ስልቶች ላይ ያስከተለዉ ችግር ሳይፈታ የሰዎችን ህይወት መቅጠፉን ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/LLVF
ምስል AP

በኔፓል ሳምንት ባስቆጠረዉ ቁር 18ሰዎች መሞታቸዉ ተነግሯል። ለዘንድሮዉ ከባድ ክረምት በወጉ ያልተዘጋጁ የተባሉት አብዛኛዎቹ የብርዱ ሰለባዎች ምንዱባንና ቤት አልባ ሰዎች መሆናቸዉ ተዘግቧል። የኔፓን የአየር ጠባይ ትንበያ ማለትም የሜቲሪዎሎጂ እንደሚለዉ ለወትሮዉ በአገሪቱ በዚህ ወር ከተለመደዉ በ15ዲግሪ ሴልሲየስ የወረደ የአየር ንብረት ነዉ ያለዉ። እንደዘርፉ ገለፃ ከሆነም ጭጋጋማዊ አየር በመጪዉ ቀናትም ቀጣይነት ይኖረዋል። ያም በመንገዶች፤ በአየርና በምድር መጓጓዣ ስልቶች ላይ ሁሉ በሚኖረዉ ተፅዕኖ በርካታ በረራዎች ሊሰረዙ ግድ ነዉ። በአገሪቱም በርካታ ሰዎች ቅዝቃዜዉ ባስከተላቸዉ የተለያዩ ህመሞች ምክንያት በርካቶች ወደሃኪም ቤት እየሄዱ ነዉ።

በተመሳሳይ አዉሮጳን ቆፈን ያስያዘዉ ቅዝቃዜ ከዜሮ በታች 25 ዲግሪ በተመዘገበባት ፖላንድም ክረምቱ ከጀመረበት ከህዳር ወር አንስቶ እስካሁን የ122ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። ከሟቾቹ አብዛኛዎቹ በ35 እና 50ዓመት መካከል የሚገኙ መኖሪያቸዉን ጎዳና ያደረጉ ጎልማሶች ሲሆኑ ለህልፈተ ህይወታቸዉ ምክንያት የሆነዉ ከተለመደዉ በታች የወረደዉ የሰዉነት ሙቀት መጠናቸዉ መሆኑ ተገልጿል። ፖሊስ እንደሚለዉ አብዛኞቹ ብርዱን ለመቋቅም ይመስላል ሰክረዉ ነበር። ፖላንድ ከባድ የክረምት ወቅት ከሚያሳልፉ የአዉሮጳ አገራት አንዷ ስትሆን በቅርቡ ባስተናገደችዉ ጠንካራ የክረምት ወራት ማለትም በአዉሮጳዉያኑ 2005 እና 2006 233 ሰዎች በብርድ ምክንያት ህይወታቸዉ ማለፉ ተመዝግቧል። ዘገባዎች እንደሚሉት ከሆነ በክረምቱ ወራት በፖላንድ የሰዉ ህይወት በዚሁ መዘዝ ማለፉ ያን ያህል አዲስ የሚባል አይደለም። የዘንድሮዉን ለየት የሚያደርገዉ ገና ክረምቱ ከገባበት ወቅት ጀምሮ ቅዝቃዜዉ በመጠንከሩ ወደ80 የሚገመቱትን ለህልፈት መዳረጉ ነዉ። አዉሮጳዉያኑ የተንሰራፋዉ የክረምቱ ብርድ በስዊዘርላንድ አልፕስ ተራራ ላይ በበረዶ እየተንሸራተቱ በመዝናናት ላይ በነበሩ ወገኖች ላይ የበረዶ ናዳዉ ከተራራዉ አናት ወርዶ ቢያንስ 10ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀሩ ፖሊስና የነፍስ አድን ሰራተኞች ገልጸዋል። የበረዶ ናዳዉ በግማሽ ሰዓት ልዩነት ተከታትሎ የወረደዉ ባሳለፍነዉ እሁድ ሲሆን የተረፉ ሰዎች ካሉ በሚል የእርዳታ ሰራተኞች በአካባቢዉ ተሰማርተዋል። በሄሊኮፕተርና በአነፍናፊ ዉሾች የሚታገዘዉ ቡድን ከብዙ ጥረት በኋላ በረዶ የተጫናቸዉ ስምንት ሰዎችን ከነህይወታቸዉ አትርፈዋል። እንዲያም ሆነ ከተራፊዎቹ አንዳንዶቹ ለርዳታ ወደስፍራዉ ከሄዱት መካከል አንዱን ዶክተር ጨምሮ በአስጊ ሁኔታ ላይ ስለነበሩ ሃኪም ቤት ከገቡ በኋላ የሶስቱ ህይወት አልፏል። ዶክተሩ የመጀመሪያዉ የበረዶ ናዳ የጎዳቸዉን ሰዎች ለማትረፍ እዚያ መድረሱን ተከትሎ በወረደዉ የበረዶ ናዳ መጎዳቱ ተመልክቷል። አሁንም አደጋዉ ከገጠማቸዉና በበረዶ ሸርተቴ ስፖርት ከሚዝናኑት መካከል አንድ ጀርመናዊና አንድ የስዊዝ ዜጋ አልተገኙም። እንዲያም ሆኖ በአካባቢዉ ባለዉ አደገኛ የአገር ጠባይ ምክንያት ትናንትናም ፍለጋዉን መቀጠል እንዳልተቻለ ነዉ ዘገባዎች የሚያመለክቱት። በዚያዉ በስዊዘርላንድ ተራራማ አካባቢዎች ለበረዶ ሸርተቴ ስፖርት የተሰባሰቡ የተለያዩ አገራት ዜጎችን ይመራ የነበረ አስጎብኚ ተመሳሳይ የበረዶ ናዳ አጋጥሟቸዉ ሌሎቹ ሲተርፉ አስጎብኚዉ ህይወቱ ማለፉ ተሰምቷል። የሰዉየዉ አካል በሰማንያ ሴንቲሜትር የበረዶ ክምር ተሸፍኖ እንደነበር ነዉ የተነገረዉ።

በብሪታንያም እንዲሁ እየጠነከረ የሚታየዉ ቅዝቃዜ በረዷማዉን የአየር ጠባይ አባብሶ እንደሚቀጥል የአየር ንብረት ትንበያዉ ያዉ እያመለከተ ነዉ። ትናንት እንደተሰማዉ የበረዶ ጥርቅም ከሰሜናዊ ስኮትላንድ ወደሎንዶን እያመራ ነዉ። ያም የከተማይቱን ዙሪያ ገባ በበረዶ እንደሚያለብስ ይጠበቃል። ቅዝቃዜዉም ባለዉ ላይ ከፍ እንደሚል ነዉ በባለሙያዎች የተገመተዉ። በተመሳሳይ ስኮትላንድና ሰሜን አየርላንድም የጠነከረ ቅዝቃዜ እንደሚገጥማቸዉ ማስጠንቀቂያ ተላልፏል። በነገራችን ላይ በየጎዳናዉ እንደአሸዋ የሚከመረዉን በረዶ የሚያቀልጠዉ አንድም ጨዉ አንድም ለዚሁ ሲባል እንዳያንሸራትት የሚደረገዉ ጎላ ያለ አሸዋ ነዉ። እንዲህ ባለዉ ከባድ ቅዝቃዜ ለአዉቶሞቢሎች ነፍስ ዘርቶ እንዲንቀሳቀሱ የሚረዳዉን ባትሪ ከማርጋት አልፎ ስለሚያድርቅ በየማለዳዉ የሚያጋጥመዉ ችግር ቀላል የሚባል አይደለም። ለዚሁ ችግር ለምሳሌ በሎንዶን አንድ የሞተር አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ በትናንትናዉ ዕለት ብባ 22 ሺ የድረሱልን የስልክ ጥሪ መቀበሉን አስታዉቋል። እዚህ ጀርመን ከአዉሮጳዉያኑ አዲስ ዓመት አንስቶ ዳግም ጎዳናዉን የሸፈነዉ በረዶ በየቦታዉ እንዳለ ሆኖ ቅዝቃዜዉ ለክረምቱ የሚሆኑትን ሞቃት ልብሶች አልፎ አጥንት ዘልቆ የሚሰማ ዓይነት ሆኗል። የሙቀት መጠኑም ከዜሮ በታች በርካታ ዲግሪዎች የወረደ ነዉ።

China Wetter Schnee in Peking
የቤጂንግ በረዶምስል AP

በእስያም እንዲሁ ከስድስት አስርት ዓመታት በኋላ የወረደዉ በረዶ በቤጂንግና ሴዑል አዉሮፕላኖች መሬት እንዲይዙ በሺዎች የሚቆጠሩት ትምህርት ቤቶችም እንዲዘጉ አስገድዷል። በቤጂንግ አዉሮፕላን ማረፊያ ብቻ ወደ1,200 በረራዎች ተሰርዘዋል አንዳንዶቹም ሰዓታቸዉ ተዛብቷል። በሳምንቱ ማለቂያ በቤጂንግ የወረደዉ በረዶ 30ሴንቲ ሜትር ሲሆን ትናንት ደግሞ ሰማዩ ጥርት ብሎ መታየቱ ተዘግቧል። እንዲያም ሆኖ በሰሜናዊ ቻይና ተጨማሪ በረዶ እንደሚወርድ ይጠበቃል። በቤጂንግና በአካቢዉ ወደ30 ዋና ጎዳናዎች ሊዘጉ ግድ ሆኗል፤ የየከተማዉ ዉስጥ መንገዶችም እንዲሁ በበረዶ ተሸፍነዋል። በጎዳና ላይ ስርዓት ለማስከበርም 5,000 በጎ ፈቃደኞች ተሰማርተዋል። 3,500 ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸዉም ተማሪዎች አዲሱን የአዉሮጳ ዓመት ተከትሎ ለተጨማሪ የእረፍት ወቅት በየቤታቸዉ ተከተዋል። ቅዝቃዜዉም ከዜሮ በታች 16 ዲግሪ ደርሷል ነዉ የተባለዉ። በሰሜናዊቷ ሃሎንጊያንግ ክፍለ አገር የሙቀት መለኪያ መሳሪያዉ ከዜሮ በታች 36 ዲግሪ ላይ ማመልከቱም ተነግሯል።

በደቡብ ኮሪያ ዋና ከተማ ሴዑል ወርዶ 28ሴንቲ ሜትር የደረሰዉ በረዶ አገሪቱ እንዲህ ያለዉን መረጃ መመዝገብ ከጀመረችበት ከአዉሮጳዉያኑ 1937ወዲህ የመጀመሪያ መሆኑን የአገሪቱ የአየር ጠባይ ትንበያ መስሪያ ቤት አስታዉቋል። ዙሪያ ገባዉን እንደብርድ ልብስ የሸፈነዉ በረዶም በርካታ የአገር ዉስጥና 40ዓለም ዓቀፍ በረራዎች እንዲሰረዙ ግድ ብሏል። በአዉራ ጎዳናዎች ላይም እንዲሁ በረዶዉ ያስከተለዉ የትራፊክ መጨናነቅ ሰራተኞች በሰዓቱ በየስራ ገበታቸዉ እንዳይገኙ እንቅፋት ሆኗል። የአገሪቱ የከተማ አስተዳደርም ከዋና ዋና መንገዶች ላይ በረዶዉን እንዲያነሱ 3,500 ሰራተኞችና 1,200 ተሽከርካሪዎችን ማሰማራቱን አመልክቷል። እንደ ደቡብ ኮርያ የአየር ጠባይ ትንበያ መስሪያ ቤት መረጃ ከሆነም በሰሜን ኮርያ የወረደዉ በረዶ እስከ ስምንት ሴንቲ ሜትር ይደርሳል። ጃፓን ዉስጥ ደግሞ ተራራማ በሆነዉ ማዕከላዊ ግዛት አካባቢ ከባድ በረዶ ወርዶ የአንድ ሰዉ ህይወት ሲጠፋ ሁለቱ ደግሞ የገቡበት አልታወቀም። ሌሎች ሰባት ደግሞ ትራቺ የተሰኘዉን ተራራ ለመዉጣት ሲሞክሩ በበረዶና ቅዝቃዜዉ ተይዘዉ ከተኮራመቱበት ነፍስ አድኖች ድርሰዉላቸዉ ህይወታቸዉን ታድገዋታል። የቅዝቃዜዉ መጠን ጨምሮ ከታየባቸዉ አገራት መካከል በህንድ ሰሜናዊ ክፍል 40ሰዎች መሞታቸዉን ባለስልጣናት አስታዉቀዋል። በአሜሪካን ዋሽግተንና ምስራቃዊ የባህር ዳርቻዎች አካባቢ የበረዶ ዉሽንፍር ስፋራዉን እንደነጭ ብርድ ልብስ ጀቡኖታል። ከ38 እስከ 64ሴንቲ ሜትር ከፍታ ያለዉ ይህ በረዶ ከቅዝቃዜዉ ባሻገር ንፋስ እንደሚኖረዉ ነዉ የተተነበየዉ።

Flash-Galerie Wintereinbruch in Deutschland
በረዶና የትራፊክ ጭንቅንቅ በጀርመንምስል picture alliance / dpa

ሸዋዬ ለገሠ/አርያም ተክሌ