1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰሞኑ የተቃውሞ እንቅስቃሴ እና ጥቃት

ዓርብ፣ ጥቅምት 21 2012

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ አንስቶ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እና ጥቃት ለብዙዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል። ከሁለት መቶ የሚበልጡ ተጎድተዋል፤ የንብረት ውድመትንም አስከትሏል።

https://p.dw.com/p/3SJEX
Äthiopien Daniel Bekele
ምስል DW/S. Muchie

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፤ የሃይማኖት ተቋማት ስብስብ፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ እና ሌሎችም ድርጊቱን የፈፀሙ እና እንዲፈፀም ምክንያት የሆኑት ተጣርቶ ለሕግ እንዲቀርቡ ባወጧቸው መግለጫዎች አሳስበዋል። የፍትህ ጥሪውን አስመልክቶ  በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ ወገኖች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፤  ተሽ ደብሊዩ ተሰማ በፌስቡክ፣ «እንደ ቀድሞ የሮጠ ላይ መተኮስም፣ እንደ አሁኑ ደግሞ የሚያርድን በዝምታ ማለፍ ሳይሆን ወደ መሃል፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን ያግዛል።» በማለት ሃሳባቸውን በአጭሩ ሲገልፁ ፤ ሃሳ አስታጥቄ በበኩላቸው በፌስቡክ፤ «መንግሥት የት አለ? የለም። እግዚአብሔር ብድሩን ይከፍላል ቢዘገይም የሚቀድመው የለምና ።» ብለዋል። ሲራክ ተመስገን ደግሞ በትዊተር፤ ««በተለይ ጥቅምት 13 እና 14 ለደረሰው ጥፋት መነሻ ከሆነው «ተከብቤያለሁ» በሚል ለመንግስት አካል ማሳወቅ ሲገባው ወደ ህዝቡ ከረጨው ግለሰብ ጀምሮ በየደረጃው በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ አደጋ ያደረሱ ሰዎች በሙሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ…» ብለዋል።  ዳንኤል ሽፈራው በእንግሊዝኛ፤ «ልብ ሰባሪ እና አሳፋሪ አጋጣሚ፤ ይህ መቆም አለበት» ሲሉ በፌስቡክ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በላይ ማናዬም በዚሁ በትዊተር፤

«መጀመሪያ ጥቃት ይከፍቱብሃል። ጥቃቱ ሲከፈትብህ በቅርብ የፀጥታ አካል ቢኖርም በዝምታ ያይሃል ወይም ያስጠቃሃል። በዚህ ሁሉ ጥቃት ራስህን ተከላክለህ በሕይወት ስለተረፍክ ደግሞ እስር ይጠብቅሃል። ናዝሬትን ጨምሮ ብዙ አካባቢዎች እየሆነ ያለው ይህ ነው!» ሲሉ ጽፈዋል። ማሂ የአርሴማ ልጅ በፌስቤቡክ እንዲህ አሉ፤ « መቆጣጠር እየተቻለ በተደጋጋሚ ብዙ እልቂት ጥፋት ጥቃት አይፈጠርም ነበር እስቲ በሀገራችን ምንም ሳይፈጠር ቀድመን ተቆጣጥረናል የሚሉበትና የህግ የበላይነት የሚከበርበትን ጊዜ እንዲያሰማን ፈጣሪ ይርዳን!! ስለሆነው ነገር ውስጣችን ቆስሎዋል ያማል የንፁሀን ደም ይጮሀል ፈጣሪ ፍርዱንም ይሰጣል!!!»

Symbolbild Facebook
ምስል Getty Images/AFP/L. Bonaventure

አንተነህ አንተነህ ደግሞ «መከላከያ ሠራዊታችን የአቅምም ሆነ የቴክኒክ ችግር የለበትም ከኛ አልፎ ለአፍሪካ ቀንድ የሚሰራ ብቁ ሰራዊት ነው። ነገር ግን ግጭቶች በሚነሱበት ወቅት የበላይ ትዛዝ እስኪሰጥ እርምጃ ላይወስዱ ይችላሉ ችግሩ ይሄ ይመስለኛል ስለዚህ ሕጉ መስተካከል ያለበት ይመስለኛል።» ሲሉ በዚሁ በፌስቡክ ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያወጣውን መግለጫ የተመለከቱት ኢዮብ ገለታ በበኩላቸው  በፌስቡክ፤ « ይሄ ጉዳይ ዳንኤል በቀለ በኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመዘንበት ወሳኝ ወቅት ነው፡፡ ምርመራው በፍጥነት በእውነትና በሚዛናዊነት ተደርጎ የሆነው ነገር አንድም ሳይቀር ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም ይፋ መደረግ አለበት፤ ይህ ሲሆን ብቻ ነው ፍትሕ ሊኖር የሚችለው፤ ሀገሪቱም ልትቀጥል የምትችለው፡፡» ብለዋል። አርአያ ተስፋዬ ደግሞ፤ « የህዝብ እልቂት በየትኛውም ቦታ ሊያሳዝነን ሊያሳስበን ይገባል። በጉምዞች እልቂት ሃይ ባይ ቢኖር ኖሮ እዚህ ደረጃ አይደርስም ነበር። አሁንም ተጠያቂነቱ በሁሉም ቦታ፣ በሁሉም ህዝቦቸ ላይ የፈፀሙትን ማካተት ይኖርበታል።» የሚል ማሳሰቢያቸውን በፌስቡክ አስነብበዋል።

በጥቃቱ ሕይወታቸው ያለፈ ወገኖች ብዛትን በመለከተ ደግሞ ጌታው ዘውዱ በፌስቡክ ፤ «ከ70-80 ብሎ መረጃ አለ እንዴ? ለምንስ ሲባል የአንድ ሠው ሕይዎት በከንቱ ይጠፋል? መንግስት ተቀዳሚ ሥራው የህዝቦችን ደህንነት (በሕይዎት፣ በጤና፣ በኢኮኖሚ) እንድሁም ማህበራዊ ዋስትና የማረጋገጥ ግዴታም አለበት። ይህን ያልፈፀመ መንግሥት ሳይሆን ቡድን ነው ያውም ዜጎቹ በሚከፍሉት ግብር የሚዝናና።» ሲሉ ጠይቀዋል። አብርሃም አበበ ደግሞ በፌስቡክ እንዲህ ብለዋል፤ «ከየአቅጣጫው ከዓመት በፊት በጁዋር ላይ በተለይም ደግሞ ኦሮሞ ጠል በሆኑ ሚዲያዎች የተከፈተው የጥላቻ ዘመቻ የዚህ ሁሉ ህዝብ እልቂት ምክኒያት ሆኑዋል።»

USA New York UN Generalversammlung | Sahle-Work Zewde
ምስል Reuters/C. Allegri

በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ አስተያየታቸውን በፌስቡክ ያካፈሉት ደግሞ ማቴዎስ ገለቦ ለሚታ ናቸው፤ ከሰጡት ረዥም አስተያየት በአጭሩ እናካፍላችሁ፤ «ወቅታዊ ዘመቻው ቅድሚያ ስለህዝብ ሰላምና ደህንነት መሆን አለበት!! » በማለት ጀመሩ ማቴዎስ፤  « ብዙዎች ወሬ፣ አሉባልታ፣ ሀሜት ሌላም ሌላም ላይ ዘምተው ህዝብን ከህዝብ አጋጭተዋል፡፡ የንጹሐን ደም ሲፈስም ጣታቸውን በሌሎች ላይ ቀስረዋል። በዘመቻቸውም ክቡር የሆነው የዜጎች ሕይወት በየሜዳው ሲቀጠፍና ሲወድቅ በየዕለቱ እያየን ነው፣ ለዘመናት ያፈሩት ሀብትና ንብረትም በአንዲት ሌሊት ሙሉ በሙሉ ሲወድምም ታይቷል። በእነዚያ ሰይጣናዊ ሥራዎች የዜጎቻችን ጩኸት ከመቼውም በላይ ዛሬ ላይ በርትቷል፡፡ አሁን ግን ዘመቻው መሆን ያለበት ስለህዝብ ሰላምና ደህንነት ነው፡፡ የህዝብ አስተዳደሩ፣ የሀገር ሽማግሌውና የጎሳ መሪው፣ የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮችና ሰባኪዎች፣ የምሁሩ ኃይል፣ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በፌስቡክ ላይም ሆነ በሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተጠመዱ አክቲቪስቶች፣ የተለያዩ ሚዲያዎች፣ ባህላዊ መዋቅሩ፣ በአጠቃላይ መላው የሀገርቷ ህዝቦች አሁን ላይ ጩኼታችንና ዘመቻችን ስለህዝብ ሰላምና ደህንነት መሆን አለበት፡፡ » በማለት ሰፋ ያለ ምክራቸውን አስነብበዋል።  በዚህ ጉዳይ ላይ ከተሰጡት አስተያየቶች የብዙዎችን ትኩረት የሳበው ደግሞ ፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በትዊተር ያሰፈሩት አስተያየት ነው፣

«ዘርና ሃይማኖት ለፖለቲካ ጥቅም እንዲውሉ ሲደረግ፤ ንጹሀን ዜጎቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉና ሲንከራተቱ ስናይ ስሜትን ለመግለጽ ቃላት ያጥራል: ለቅሶ፣ ድንጋጤና ሥጋት የብዙዎችን በር አንኳኩቷል ሃዘናቸው ሃዘኔ/ሃዘናችን ነው:: ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ሲባል ልናሰምረው እና ልናከብረው የሚገባን ቀይ መስመር ተጥሷል። አገራችንን ካንዣበበባት ክፉ አዳጋ ለማዳን ሁላችንም ሚና አለን። የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው። ቀይ መስመር መጣስ የለበትም እንበል::» ይላል የፕሬዝደንቷ አስተያየት። ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች የተቀሰቀሰው ተቃውሞ የ78 ሰዎችን ሕይወት እንዳጠፋ፤ ከጉዳዩ ጋር በተገናኘም 407 ሰዎች መታሰራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

Instagram-Icon
ምስል picture-alliance/xim

ባለፈው ዓመት 2011 ሰኔ 15 ቀን በአማራ ክልል ባለሥልጣናት እና በፌደራሉ የሀገር መገላከያ ሠራዊት በላዮች ላይ ከተፈፀመው ግድያ ማግስት በአማራ ክልል እና በአዲስ አበባ በርከት ያሉ ዜጎች መታሰራቸው ይታወሳል። ታሳሪዎቹ በሽብር ድርጊት መጠርጠራቸው ተገልጾ ምርመራ ሲካሄድ ቆይቶም ክስ ሳይመሰረትባቸው በገንዘብ እና በመታወቂያ ዋስትና መፈታታቸውም እየተሰማ ነው። በዚህ ሳምንትም ከ20 በላይ ታሳሪዎች በተመሳሳይ መልኩ ተፈትተዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይህን አስመልክቶ   የኢትዮጵያ መንግሥት የፀረ ሽብሩን ሕግን አላግባብ መጠቀም  ቀጥሏል ሲል ተችቷል። የተለያዩ ወገኖችም በዚሁ ላይ አስተያየታቸውን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስነብበዋል። በፌስቡክ «እንዲህ በመታወቂያ ዋስ ለመልቀቅ ይህን ያህል ወራት ያለአላግባብ በእስር ማሰቃየት የግፍ ግፍ ነው። ለማንኛውም እንኳን ከእስር ተፈታችሁ።» ያሉት እሸቱ ሆማ ኬኖ ናቸው፤ ዳዊት እንደሻው ደግሞ በትዊተር፤ ይህ ከመጀመሪያውም መታሰራቸው ስህተት እና በሀሰት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያረጋግጣል፤ መንግሥት አሁን ሊለቃቸው የወሰነው በአሁኑ ወቅት የህዝብ ተቃውሞ ስለገጠመው አቅጣጫ ለማስለወጥ ነው።» ሲሉ በእንግሊዝኛ አስተያየታቸውን አስነብበዋል። ኑሃሚን ቆንጆ፤ «አይ ለውጥ"ጋዜጠኛና ሰላማዊ የፓለቲካ አመራርሮች አሸባሪ እየተባሉ ይታሠራሉ፤ ባንጻሩ ደግሞ አሽባሪ በመንግሥት ጥበቃ ይሽሞነሞናል።» ብለዋል በፌስቡክ። በዚሁ በፌስቡክ ኢሌኒ ቀለመወርቅ፤ «ድሮም ያለምክንያት ነው ያሰሯቸው። ሕግ የለም እንጂ ቢኖር ለምን እንዳሰሩና ለምን እንደፈቱ መጠየቅ ነበረባቸው። ግን ምን ዋጋ አለው በግፍ አስረው ሲፈቱን እናመሰግናለን፣ አማራጭ የለንማ። ያበሳጫል።» ብለዋል።

ሸዋዬ ለገሠ