1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰብዓዊ መብት ተመልካቹ ድርጅት የHuman Rights watch ዓመታዊ ዘገባ

ዓርብ፣ ጥር 4 1999
https://p.dw.com/p/E0hS

ዩናይትድ ስቴትስ በሽብርተኝነት የያዘቻቸውን ተጠርጣሪዎች ያለ አንዳች ፍርድ ጎዋንታናሞ እስር ቤት ካወረደች ትናንት አምስት ዓመት ተቆጠረ ። በዚህም Human Rights watch የተባለው የሰብዓዊ መብት ተመልካች ድርጅት የቡሽ አስተዳደርን የሰው ልጆችን መብት በመጣስ በግንባር ቀደምትነት ወንጅሏል ። ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ ትናንት ባወጣው ዓመታዊ ዘገባው ሰብዓዊ መብትን ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የአውሮፓ ህብረት የመሪነቱን ስፍራ ከመያዝ ይልቅ ወደ ኃላ ሲል በመታየቱም ወቅሷል ። ከአፍሪቃ የሰብዓዊ መብት ገፈፋ እጅግ የተስፋፋበት ዳርፉር መሆኑን የገለፀው Human Rights watch በኢትዮጵያና በኤርትራም የሰብዓዊ መብት አያያዝ ወደ ባሰ ሁኔታ መሸጋገሩን አውስቷል ። ስለአፍሪቃ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ለዶይቼቬለ ቃለምልልስ የሰጡት የድርጅቱ ዋና ዳሬክተር Kenneth Roth በሌላ በኩል በሁለት ሺህ ስድስት በአፍሪቃ አምባገነኖችን ለፍርድ ለማቅረብ የተደረጉት ጥረቶች በበጎ የሚነሱ ተግባራት ናቸው ብለዋል ።
የHuman Rights watch ዋና ዳይሬክተር Kenneth Roth እንዳሉት ዩናይትድ ስቴትስ በእስካሁኑ የሰብዓዊ መብት አያያዟ ሰብዓዊ መብትን የማስከበርን ጉዳይ በተመለከተ ተዓማኒነትን አጥላች ። በዚህ የተነሳ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሸፈን የመሪነት ቦታ ሊይዙ የሚችሉት የአውሮፓ ሀገራት ነበሩ ። ሆኖም ግን በዚህ አቅጣጫ የአውሮፓ ህብረት በሁለት ሺህ ስድስት ያከናውናቸው ተግባራት ከሚጠበቀው በታች ሆኖ ነው የተገኘው ። ድርጅቱ በተጨማሪ አስቸክዋይ ትኩረት ያሻዋል ሲል የጠቀሰው የኢራቅን ወቅታዊ ሁኔታ ነው ። በዘገባው በኢራቅ በሀይማኖትና በፖለቲካ ልዩነቱ ክፍፍል ምክንያት ደም መፋሰሱ የመቀጠሉ አሳሳቢነት እንዲተኮርበትም ጠይቋል ። ሰሜን ኮሪያ በርማና ቱርክሜንስታን የህዝቦቻቸውን ክብር የነፈጉና መሰረታዊና ሰብዓዊ መብቶችንም የነሱ መንግስታት መሆናቸውን ያመለከተው ይኽው ዘገባ ኢራንና ኢትዮጵያንም የህዝባቸውን ድምፅ በማፈን ወንጅሏቸዋል ። የHuman Rights watch ዋና ዳይሬክተር ሚስተር Roth እንደተናገሩት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ወደ ባሰ ደረጃ ተሸጋግሯል ።
“በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ሁኔታዎች የኃሊት እየሄዱ ነው ። መንግስት የተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ዕንቅስቃሴ በኃይል አግዷል እኛን አሁን የሚያሰጋን በሶማሊያ ጦርነት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የምዕራባውያኑን ወዳጅነት ለማትረፍ ይህን እንደማምለጫ እንዳይጠቀሙበት እንሰጋለን ። ምዕራባውያኑም ከዚህ ቀደም መለስ በሀገራቸው በሚያካሂዱት አፈና ላይ የነበራቸውን ተቃውሞ እንዳይተዉ እንሰጋለን “
በኢትዮጵያ ከምርጫ ዘጠና ሰባት ጋር ተያይዞ በተነሳው ተቃውሞ ከታሰሩት ሰዎች በርካታዎቹ ቢለቀቁም እንደ Human Rights watch ምን ያህሉ እስር ቤት እንደቀሩ ግልፅ አይደለም ። ከዚህ በተጨማሪም መንግስት ከምርጫ ዘጠና ሰባት በኃላ በርካታ ታቃዋሚ ፖለቲከኞችን ጋዜጠኞችን እንዲሁም የሲቪል ማህበራት መሪዎችና አባላትን በአገር ክህደትና በዘር ማጥፋት ወንጀል ከሶ ማሰሩንም አንስቷል ። እንደ ሰብዓዊ መብት ተመልካቹ Human Rights watch በሀገሪቱ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት አፈናን አስመልክቶም እንደዘገበው መንግስት በእስር ላይ የሚገኙትን የዶር ብርሀኑ ነጋን መፀሀፍ ይዘው የተገኙ ግለሰቦችን እያዋከበ ነው ። ሚስተር Roth በኤርትራም ሁኔታው ተመሳሳይ መሆኑን ነው ያስረዱት
ድምፅ
ኤርትራም በተመሳሳይ ሁኔታ ቁጥጥሩ ያያለ ነው ። ኤርትራም አፋኝ መንግስት ሆና እንደቀጠለች ነው እናም እኛም እስካሁን በሁኔታዎች ላይ ምንም ዓይነት ማሻሻያዎች ሲደረግ አላየንም እንዳውም አንዳንዴ ወደኃላ እየተመለሰች ነው ።”
ሮዝ አክለውም በዓለማችን ከደረሱት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዋነኛው በምዕራባዊትዋ የሱዳን ግዛት በዳርፉር የተፈፀመው መሆኑን ነበር የተናገሩት ። እንደ Roth በዳርፉሩ ግጭት ተገድሏል ከሚባለው ቁጥሩ ከሁለት መቶ ሺህ ከሚልቅ ህዝብ በተጨማሪ ከሁለት ሚሊዮን ይበልጣል ተብሎ የሚገመት ያለውዴታው ተሰዷል ። በዓለም ዓቀፉ ፍትህ በኩል በአፍሪቃ በርካታ ለውጦች እየታዩ መሆናቸውን ሚስተር Roth አንስተዋል ። ባለፉት ዓመታት ቻርልስ ቴይለር ለሴራልዮን ፍርድ ቤት መሰጠታቸው ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው ። ያቻዱ አምባገነን መሪ ሂሴን ሀብሬ ለፍርድ እንዲቀርቡ የእሪቃ ህብረት ያሳየው ቁርጠኝነት ተወድሷል ። በቅርቡም የኢትዮጵያ መንግስት ዚምባብዌ በሚኖሩት በቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያም መፍረዱ በአጠቃላይ በአህጉሪቱ ሰብዓዊ መብትን ለማስጠበቅ ቁርጠንነቱ እየተጠናከረ መምጣቱን አመልካች ነው ብሏል Human Rights watch