1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰብዓዊ ቀውስ በማዕከላይ አፍሪቃዊቱ ሬፓብሊክ

ሰኞ፣ ሐምሌ 8 2005

በማዕከላይ አፍሪቃዊቱ ሬፓብሊክ ያማፅያን ቡድኖች የተሰባሰቡበት የየሰሌካ ህብረት የቀድሞውን ፕሬዚደንት ፍራንስዋ ቦዚዜን በመፈንቅለ መንግሥት አስወግዶ ሥልጣን ከያዘ ወዲህ ሀገሪቱ አሳሳቢ ሰብዓዊ ቀውስ ገጥሞዋታል።

https://p.dw.com/p/1974N
ምስል DW/Simone Schlindwein


የአውሮጳ ህብረት ለዚችው ንዑሷ ሀገር ችግርዋን ማቃለል ትችል ዘንድ የሚሰጠውን ርዳታ ለማሳደግ ወስኖዋል። የአውሮጳ ህብረት ለማዕከላይ አፍሪቃዊቱ ሬፓብሊክ ተጨማሪ ስምንት ሚልዮን ዶላር በመስጥት ከዓመቱ 2013 መጀመሪያ ወዲህ የሰጠውን ርዳታ ወደ 20 ሚልዮን ከፍ እንደሚያደርግ ሰሞኑን ይህችን ሀገር የጎበኙት የህብረቱ ዓለም አቀፍ ትብብር እና ሰብዓዊ ርዳታ ጉዳዮች ኮሚሽነር ክሪስታሊና ጊዮርጊየቫ ከጥቂት ቀናት በፊት አስታውቀዋል። ገንዘቡ ለምግብ እና ለመድሀኒት፣ ለንፁሕ የመጠጥ ውኃ እና ለመፀዳጃው ዘርፍ ይውላል።

አራት ሚልዮኑ የማዕከላይ አፍሪቃዊቱ ሬፓብሊክ ነዋሪ በወቅቱ የተመሰቃቀለ ሁኔታ የተነሳ ትልቅ ችግር ላይ መሆኑን፣ ከዚህም 1,6 ሚልዮኑ ባልተመጣጠን አመጋገብ የመሰቃየት ስጋት እንደተደቀነበት በምዕራብ እና በማዕከላይ አፍሪቃ በረሀብ አንፃር የሚታገል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አላ ኩቶም ገልጸዋል።
« ካለፉት ስድስት ወራት ፣ በተለይም ያማፅያኑ የሴለካ ህብረት ሥልጣኑን ባለፈው መጋቢት 2013 ከያዘበት ጊዜ ወዲህ በካር የጤናው፣ የመፀዳጃው ወዘተ አውታሮች አንድም ከሞላ ጎደል ወድመዋል ወይም ተዘረፈዋል፤ ሕዝቡም በማያስተማምነው የፀጥታ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚኖረው። ብዙዎች አሁንም ወደ ቀያቸው መመለስ በመፍራታቸው በየጫካው እንደተሰደዱ ይገኛሉ። »
የማዕከላይ አፍሪቃዊቱ ሬፓብሊክ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚደንት ሚሼል ጆቶጂያ በሀገሪቱ በመዲናይቱ ቦንግዊ ጭምር ፀጥታ ማስከበር አለመቻላቸው የርዳታ አቅርቦቱን አዳጋች እንዳደረገው አላ ኩቶ ቢገልጹም፣ ዓለም አቀፍ ርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ስራቸውን ሁኔታው በሚፈቅደው መጠን እያከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
« በሀገሪቱ የፀጥታው ሁኔታ ባያስተማምንም እየሰራን ነው። እኛ እና አንዳንድ ዓለም አቀፍ መያዶች ለምሳሌ በመዲናይቱ ቦንግዊ ከገበሬዎች ጋ የዘር መዝራቱን ጊዜ እንዳያሳልፉ የሚያስቸሉ ፕሮዤዎች አነቃቅተናል። ድንበር የማይገድበው የሀኪሞች ድርጅትም ክትባት የመስጠቱን እና መሰል ስራዎችን ያካሂዳል። »
ቀደም ባለ ጊዜ ዓለም አቀፉ ማህበረ ሰብ ይህችኑ ንዑስ ሀገር ችላ ብሎዋል በሚል ወቅሳ አሰምቶዋል። እአአ በ1960 ዓም ከፈረንሣይ ቅኝ አገዛዝ ነፃነትዋን ከተጎናፀፈች ወዲህ ቀውስ ባልተለያት በማዕድናቱ ወርቅ፣ አልማዝ፣ ዩሬንየም እና ነዳጅ ዘይት በታደለችው ማዕከላይ አፍሪቃዊቱ ሬፓብሊክ ውስጥ ካለፈው ታህሳስ ወዲህ የተከሰተው ውዝግብ በሀገሪቱ ወደ 206,000 ሰዎች ሲያፈናቅል፣ 550,000 ዎቹን ወደ ጎረቤት ሀገራት እስዲሰደዱ አድርጓል።

.
ምስል Getty Images
Symbolbild - Soldaten in afrikanischen Kriegsgebieten.
ምስል Getty Images

አርያም ተክሌ

መሥፍን መኮንን