1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰው ልጅ የኑሮ ዕድገት ደረጃና ኢትዮዽያ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 30 2003

የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ዩኤንዲፒ የሰው ልጅ የኑሮ ዕድገት መለኪያ በሚል የሚያወጣውን ሪፖርት ይፋ አድርጓል። ዘንድሮ የወጣው ሪፖርት የ40 ዓመት መረጃዎችን መሰረት ያደረገ እንደሆነ ድርጅቱ አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/Q2g7

ጤና፤ ትምህርትና የገቢ መጠን ላይ በባለፉት 40 ዓመታት ሀገራት ያሳዩትን ለውጥ በንጽጽር አቅርቧል። በመንግስታቱ ድርጅት የሰው ልጅ የኑሮ ዕድገት መለኪያ ሪፖርት ኢትዮዽያ የተሰጣት ደረጃ ዝቅ ያለ ቢሆንም ለውጥ ካሳዩ ሀገራት አንዷ በመሆን ተጠቅሳለች። በተለይም በጤናና በትምህርቱ ዘርፎች ዕድገት በማስመዝገብ ጥሩ ውጤት እንዳገኘች በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል። መሳይ መኮንን የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም ቃል አቀባይን አነጋግሮ ያዘጋጀው ዘገባ ቀጥሎ ይቀርባል።

ሪፖርቱ ኢትዮዽያን ከ168 ሀገራት 157 ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል። ይህ ከ1990 እ.ኤ.አ. ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣው የሰው ልጅ የኑሮ ዕድገት መለኪያ ደረጃ ሪፖርት በመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ ባንኪሙንና የኖቤል ተሸላሚው አማርቲያ ሴን በተገኙበት ነው ይፋ የሆነው። የአማዕቱ የልማት ግቦችን በመነሻነት ይዞ የየሀገራቱን የለውጥ ጉዞ በፊት ከነበሩበት እያነጻጻረ ያሳየውን ሪፖርት ዋና ጸሀፊው ዓለማችን የት እንዳለች ያመላከተሪፖርት ብለውታል። የሰው ልጅ የኑሮ ዕድገት መለኪያ ደረጃ ሪፖርት ከዚህ ቀደም ከወጣው የሚለየው የ40 ዓመታት መረጃዎች ላይ ተመርኩዞ የወጣ በመሆኑ ነው ይላሉ የመንግስታቱ የልማት ፕርግራም የሪፖርቱ ቃል አቀባይ ዊሊያም ኦርም ።

ድምጽ

ከቀደመው ሪፖርት የሚለየው ለመጀመሪያ ጊዜ በጣም ወደ ኋላ በመሄድ የ40 ዓመታትት መረጃዎች በመሰብሰብ የተዘጋጀ የሰው ልጅ የኑሮ ዕድገት መለኪያ ደረጃ ሪፖርት በመሆኑ ነው። የዛሬ 20 ዓመት ከወጣ በኋላ ይህኛው ሁለተኛ መሆኑ ነው። እ.ኤ.አ. ከ1970ዎቹ መጀመሪያ ዓመታት ከነበረው የሀገራት የኑሮ ደረጃ ጋር የሚያነጻጽር ሪፖርት ነው። ይህኛው ሪፖርት በዘመናዊ መልክ በተደራጀ የመረጃ አወቃቀር የተዘጋጀ ነው። በዚህኛው ሪፖርት ለማሳየት የተሞከረው በሀገራት መካከል ያለውን ደረጃ ወይም ልዩነት አይደለም። ጎረቤት በሆኑ አልያም በሀብታምና በደሀ ሀገራት መሀል ላየውንም ልዩነት አይደለም። ሀገራቱ የዛሬ 40 ዓመታት ከነበሩበት ደረጃቸው ጋር ነው የተነጻጸሩት።

ኢትዮዽያን በተመለከተ የተለያዩ ሪፖርቶች በተከታታይ ይወጣሉ። በቅርብ ይፋ ከሆኑት መሃል ኢትዮዽያ በድህነት ከኒጀር ከፍ ብላ በመጨረሻው ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ያመላከተው ይገኝበታል። አሁን የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም ሰሞኑን ያወጣው ሪፖርት ደግሞ ኢትዮዽያን የሰው ልጅ የኑሮ ዕድገት ደረጃ የተሻሻለባት በሚል ከቀዳሚዎቹ የአፍሪካ ሀገራት አንዷ አድርጓታል። ቃል አቀባዩ ዊሊያም ኦርም ኢትዮድያ ከዛሬ አርባ ዓመት ከነበረችበት ጋር ስትነጻጸር ለውጥ አሳይታለች ይላሉ።

ድምጽ

በዚህ የ40 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በሰው ልጅ የኑሮ ዕድገት ለውጥ መለኪያ መሰረት ኢትዮዽያ በዓለም ደረጃ ለውጥ ካሳዩት ሀገራት አንዷ ናት። ከዓለም የ11ኛ ደረጃ ማለት ነው። ኢትዮዽያ ብቻ አይደለችም። በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በፊት ከነበሩበት የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም ኃላፊ ሄለን ክላርክ ሪፖርቱ ሲወጣ በሰጡት መግለጪያ ዓለማችን ከዛሬ አርባ ዓመት በፊት ከነበረችበት ደረጃ በበዙ መስኮች የተሻለች ሆናለች ብለዋል። በጤናው፤ በኢኮኖሚውና በትምህርቱ በኩል በርካታ አወንታዊ ለውጦች ተመዝግበዋል ሲሉም ገልጸዋል ኃላፊዋ። ገቢን ታሳቢ ባላደረገው የሰው ልጅ የኑሮ ደረጃ ዕድገት ሪፖርት ዘርፍ ኦማን፤ ኔፓል፤ ሳዑዲ አረቢያ፤ ሊቢያ፤ አልጄሪያ፤ ቱኒዚያ፤ ኢራን፤ ኢትዮዽያ እና ኢንዶኔዢያ መሻሻል ያሳዩ ሀገራት ተብለው ከበፊት ደረጃቸው ጋር የተነጻጸረ በሚል ተቀምጠዋል። በገቢ በኩል በተሰጠው ውጤት ቻይና፤ ቦትስዋና፤ ደቡብ ኮሪያ፤ ሆንግኮንግ፤ ማሌዢያ፤ ማልታ፤ ሞሪሺየስ እና ህንድ ከፍተኛ ደረጃን አግኝተዋል። ኢትዮዽያን የተሻለ ገጽታ የሰጣት ሪፖርቱ አሁንም በዘርፈ ብዙ የድህነት ገጽታዎች የተጠቃች ሀገርም ሲል ይጠቅሳታል። የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም ቃል አቀባይ ዊሊያም ኦርም ድህነቱ እንዳለ አይካድም።ግን ለውጥም አለ ይላሉ።

ድምጽ

የሰው ልጅ የኑሮ ዕድገት ለውጥ መለኪያ ከጤና፤ ከትምህርትና ከገቢ ጋር በእኩል የሚታይ ማነጻጸሪያ ነው። እንደ ኢትዮዽያ የመሳሰሉ ሀገራት ከእዚህ አንጻር መሻሻል አሳይተዋል። በጤና በኩል በተለይ ጥሩ ውጤት ካሳዩት ሀገራት ኢትዮዽያ ዋንኛዋ ናት። የሰው ልጅ የዕድሜ ጣሪያ ከበፊት አንጻር የጨመረ መሆኑን እናያለን። በትምህርት ረገድ የመጀመሪያ ትምህርትን በማዳረስ አመርቂ ውጤት አስመዝግባለች። የትምህርቱ ዘርፍ ከዛሬ አርባ ዓመት አንጻር ሲታይ በብዙ እጥፍ አድጓል።ይሁንና ግን ኢትዮዽያ ከነበረችበት በጣም የከፋ ደረጃ አንጻር አሁን ያለችበትን በተለይም ከ1970ዎቹ ወዲህ በዓለም ደረጃ በፈጣን ሁኔታ እየተሻለች የመጣች ሀገር ናት። እንደእውነቱ ከሆነ ኢትዮዽያ በሰው ልጅ የኑሮ ዕድገት መለኪያ የተሰጣት ደረጃ በጣም ዝቅ ካለው ምድብ ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ያወጣው የሰው ልጅ የኑሮ ዕድገት ለውጥ ሪፖርት ኢትዮዽያን በተሻለ የለውጥ ደረጃ ቢጠቅሳትም በሪፖርቱ ከተገለጹት 168 ሀገራት የሰጣት ደረጃ 157ኛ ነው። ይህ ደረጃ አሁን የደረሰችበት ቦታ ከሌሎች ሀገራት ጋር ተነጻጽራ ያገኘችው ነው ይላሉ ቃለ አቀባዩ

ድምጽ

ደረጃው የሚሳየው በ2010 ሀገራቱ የሚገኙበትን ቦታ ነው። ይህም ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸሩ ማለት ነው። በተረፈ ኢትዮዽያን በተመለከተ የምናውቀው ነገር እንዳለ ነው። ድህነት በከፍተኛ ሁኔታ አለ። በጣም ደሀ ሀገር መሆኗን እናውቃለን። በገቢ ደረጃም በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በትምህርቱና በጤናውም ቢሆን በርካታ ችግሮች አሉ።

የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም የ40 ዓመት መረጃዎችን በማጠናቀር ባወጣው የሰው ልጅ የኑሮ ዕድገት ለውጥ ደረጃ ኖርዌይ በቀዳሚነት ተቀምጣለች። አውስትራሊያ፤ ኒው ዚላንድ፤ አሜሪካ፤ አየርላንድ፤ ሊህሽተን እሽታይን፤ ኔዘርላንድስ፤ ካናዳ፤ ስዊዲንና ጀርመን ከ2 እስከ 10 ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ኬኒያ 128፤ ሱዳን 154 እንዲሁም ጂቡቲ 147ተኛ ደረጃን ሲያገኙ ሶማሊያና ኤርትራ ግን በሪፖርቱ አልተካተቱም።

መሳይ መኮንን

አርያም ተክሌ